የታሪካዊ የውኃ ዋስትና ወይስ የታሪካዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መብት አጀንዳ?

አሁን የአረቦቹ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጥገኞች ነን። በእውቀትና በሥራ ሳይሆን ከነዳጅ የተገኘ ሃብታቸውን ለመቀላወጥ ያልሆንላቸው ነገር የለም። ድንግል የእርሻ መሬታችንንና የተፈጥሮ የምግብ ምርታችንን የገበያ ዋጋ ለመወሰን አቅማችን በወረደ የገበያ መድረክ ይነጥቁናል። በአለማቀፍ መድረክም ድህነታችን ባመጣብን ጣጣ የእነርሱን ፍላጎት በትክክለኛ ሚዛን ላይ አስቀምጠን እንዳንደራደር አድርገውናል፡፡ ለውኃ  ልማታችን ብድር እንዳናገኝ የዘጉብንን በር ማስታወሱ በቂ ነው። መሪዎቻችንን ገና ከናስር አገዛዝ ጀምሮ በየመድረኩ በመስደብና በማዋረድ እንደፈለጉ ያለስጋት ቀጠናውን ይምነሸነሹበታል። ባለፈው ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ላይ ሞከሩት የተባለው የዛው ልምዳቸው ውርስ አካል መሆኑ ነው። 

እንግዲህ ህዳሴ ግድብ የዚህ ሁሉ ግዞታቸው በማያዳግም መልኩ የሚያበቃበት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ አውቀውታል። በእርግጠኝነት የተገነዘቡትና የሚይዙ የሚጨብጡትን ያጡት ግን አባይ ሲፈስበት የነበረውን መንገዱን የማይናወጥ የህዳሤው መሰረት እንዲቆምበት ገለል ብሎ መፍሰስ የጀመረ እለት ነበር። የተከፈተ በራቸውን እንኳን ዘግተው ሚስጢራቸውን ማውራት እስኪሳናቸው ነበር ያበዱበት።  የሚገርመው ኢትዮጵያ ይህንን የወቅቱን የግብፅ ህጋዊ መሪዋና ወሳኝ ሰዎቿ ተጠራርተው በግብፅ መንግስት ህጋዊ ቴሌቪዥን ሲያሴሩባት ‘ይህ ሤራ የግብፅ መንግስት አቋም መሆኑን አዲስ አበባ ያለውን የግብፅ ኤምባሲ ጠየቀች’ የሚለው ዜና ነበር። 

ህዳሴ ግደብ እርካሽ የኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ባለማቋረጥ በቀጠናው ለማዳራስ እረጅሙን ጉዞ  ባጭሩ ያስጀምራል። በዚህም ብዙ ትላልቅ የአለማችን የኢንዱስትሪ ካምፓኒዎች ገፍና ያልተነካ ገበያ ወዳለበት አፍሪካ ለመድረስ ቅርንጫፍ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ኢትዮጵያ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ምናልባት ባላጋንን በጥቂት አመታት ውስጥ እነዱባይን ከአሸዋነት ወደ አለማቀፍ የንግድ ቀጠናነት የቀየረውን እድል መሻማቱም አይቀሬ ነው። ተፈጥሮአዊ የግብርና ምርቶቻችንን ወደ አረብ በርካሽ ከማጋዝ የኃይል አቅርቦታችንን  እና በገፍ እየተማረ ያለ ትውልዳችንን ተጠቅመን በእራሳችን ሀገር አቀነባብረን በኩራትና በኢትዮጵያዊ ማንነት ደረጃ ለእነርሱ ልናቀርብ ነው። አቅርቦታችን የገበያ ፍላጎትን፣ የገበያ ፍላጎቱ አቅርቦታችንን እያጠያየቀና እያመጋገበ እድገታችን ከአዙሪት ሰንሰለቱ ምህዋር ተመንጭቆ ወጥቶ ወደማይመለስበት አለማቀፋዊ የትስስር ምህዋር አስወንጭፎ ሊያቀላቅለን ነው።

ይህ ትንታኔዬ የማይዋጥላችሁና ይህን ሂደት ብታምኑበትም ላለንበት የፖለቲካና ሰብአዊ መብት ኃላቀርነት እንደመደራደሪያና መከራከሪያነት የያዛችሁ ወገኖቼ  “እና ታዲያ ምን ይጠበስ ወያኔው?” ትሉኝ ይሆናል። (ህዳሴ ግድብ እንዴት ያለንበትን የሰብዐዊና ፖለቲካዊ ኃላቀርነት ለመቅረፍ አስተዋጾ እንደሚያደርግ ወደፊት በሰፊው ለማብራራት እሞክራለሁ)። እናማ ህዳሴና መሰል የደሃ አንጀት ታስሮ የሚሰሩ ሃገራዊ ሥራዎች ለግብፆቹና ለአረቦቹ ታሪካዊ ውኃ ተኮር የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መብታቸው ላይመለስ  ሊያከትምባቸው ነዋ። (የሚገርመው ግብፅና ሱዳን ገና ድሮ እራሳቸውን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ሲያወጡ እኛን በነበርንበት የእንግሊዝ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትነት የመግዛቱን ውርስ እስከ አሁን ይዘው መቆየታቸውና በዚህ በሰለጠነ ዘመን ከዚህ ግዛታቸው ላለመውረድ ድርቅ ማለታቸው ነው)።

ህዳሤ ግድብ እንዴት ላይመለስ ይህንን ታሪካዊ መብታቸው እንዲያከትም ያደርጋል? ለዚህ መረጃ አስዋን ግድብ ያመጣውን ለውጥ ማሰቡ ብቻ በቂ ቢሆንም በህዳሤ ግድብ አንጻር ትንሽ ልበል።

ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች ከተሟሉ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው በጣም የሚፈለጉበትና የሚኮሩበት ሥራ ሊበዛላቸው ነው፤

* እኛ ወደነርሱ በግርድና እነርሱ ወደኛ ለግብርና የሚመጡበት ሰፊ መንገድ ሊጠብ ነው፤

የኛ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የኃይል አቅርቦት ገበያ ከነዳጅ ገበያቸው ጋር ስለሚገዳደር በየዘርፉ የመደራደርና የመወሰን መብታችን ከነርሱ እኩል ሊሆን ነው፤

* አንዲት ዜጋችን እንኳን የፈላ ውኃ ቢደፋባት ወይንም ኩላሊትዋን ብትዘረፍ ኢትዮጵያ በአፋጣኝ የአረብ ሃገራትን አምባሳደር ህጋዊ ጫና ያለው ጥያቄ ልትጠይቅ ካልሆነም ከሃገሩዋ ልታባርር ነው፤

* የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን የሚዘልፍ የአረብ ባለስልጣን አፍ አደብ ሊገዛ ካልሆነም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዱላ ቅጣት ሊከተለው ነው።

እናማ የ‹‹ታሪካዊ የውሀ ደህንነት›› መፈክራቸውን ወደ የ‹‹ታሪካዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት›› አጀንዳ የሚተረጉም የዲፕሎማሲ መዝገበ ቃላት አያስፈልግም ትላላችሁ?

አንዳንዴ የሚመጥን መከራከሪያ መምረጥ ሁሉንም አሸናፊ ለሚያደርግ ድርድር ቅመም ነው።

********

Sisay Demeku

more recommended stories