[መነበብ-ያለበት] ፕ/ር ሃይሰም ማሃዎዲ እና ዶ/ር ናስር ኣላም ከናይል ቲቪ ጋር ያካሄዱት ውይይት፡፡

(በሙሉነህ ቶለሳ)

የግብጽ የአሌክሳንደሪያ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሃይሰም ማሃዎዲ እና የግብፅ የቀድሞ ውሃ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር ናስር ኣላም ከናይል ቲቪ “ላይቭ ዊንዶስ” የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም ላይ (ከጋዜጠኛ ዲና ሁሴን) ጋር ያካሄዱት ውይይት፡፡

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- እንደሚታወቀው ከኢትዮጵያው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ችግሮች እየተጋረጡብን ነው፤ የኃይል እጥረት ሊያጋጥመን ነው፣ የግብፅ የናይል ውሃ ድርሻም ከ55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሊቀንስ ነው። እናም የግብፅ ሕዝብ ለከፋ ማህበራዊ ምስቅልቅል እየተጋለጠ ነው። በርግጥ የግብፅ መንግሥት ለድርድር በሩን ክፍት ማድረጉን አስታውቋል። ይሁን እንጂ እነርሱ እስካሁን በግትር አቋማቸው እንደፀኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አካሔድ በወዲያኛው ወገን ከተሰናከለ በቀጣይ ማድረግ ያለበትን መወሰን አለበት። የሱዳን መንግሥ ትም ወደኢትዮጵያ ወግኗል፤ ይህ ደግሞ ግብፅ ብቻዋን እንድትቆም አስገድ ዷታል። ኢትዮጵያ የ1959ኙን ስምምነት ጥሳለች። ያን በግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን…

«ኢትዮጵያ የለችበትም። ግብፅና ሱዳን ብቻ ናቸው የተፈራረ ሙት» (ተጠያቂው አረሟት)። እሽ እሱንም ቢሆን እየጣሰች ነው። እና እስኪ የውሃ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ነው ወይንስ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው? ግብፅ ይህን ጉዳይ ጊዜ ሳትሰጥ ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መውሰድ የለባትም?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- በፍጹም ግብፅ ከኢትዮ ጵያና ሱዳን ጋር የጀመረችው ድርድር መቀጠል ነው ያለበት። በቅድሚያ ግብፅን ሊያሳስባት የሚገባው የኢትዮጵያ ግድብ መገንባት ሳይሆን የውሃ ድርሻዋ መጠን ነው። የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት የግብፅን የውሃ ድርሻ ይቀንሰዋል ወይንስ ይጨምራል የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ተጠንቶ ሙያዊ ትንታኔ ተሰጥቶበት መታወቅ አለበት። ከሃይድሮሎጂካል ኢንጂነሪንግ ሳይንስ አንፃር ሲታይ የግድቡ መገንባት የአባይ ውሃ ፍሰት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው በሦስት ምክንያቶች ነው። አንደኛው ከግድቡ በሚተነው ውሃ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከግድቡ ወደ መሬት ሊሰርግ በሚችለው ውሃ ነው። እነዚህ ሁለቱ ብዙም ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አይደሉም። ሦስተኛ ውና ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው ምክንያት የመስኖ እርሻ ከተስፋፋ ነው።

በሌላ በኩል የግድቡ መገንባት የጥቁር አባይ ውሃ ፍሰትን የሚጨምርባቸው ሳይንሳዊ ምክንያ ቶችም አሉ። ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ በተጨ ባጭ ሱዳንን ከጎርፍ ይከላከላል። ሱዳንን ከጎርፍ መከላከል ማለት ደግሞ ግብፅና ሱዳን የሚካፈሉ ትን የውሃ መጠን ይጨምራል።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- እኔ አላምንም ይህ የውሃ ድርሻቸውን ይቀንሳል እንጂ በምን ተዓምር ሊጨምር ይችላል?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- ይኸውልሽ… ቅድም እንዳልሽው እ.ኤ.አ በ1929 ስምምነት መሰረት ከሱዳን ጋር ስንካፈል የነበረው 52 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን ነበር። ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ በ1959 ስምምነት መሰረት ውሃው ወደ 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጨምሯል። ከ30 ዓመት በፊት ያልነበረው 32 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ከየት የመጣ ይመስልሻል? ከየትም የመጣ አይደለም። ሱዳን በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ ከመጠቃቷ ጋር ተያይዞ የሚባክነው ትርፍራፊ ውሃ ሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ወደሚሰርገው ትልቁ ወንዛችን ናይል ዴልታ ሊገባ በመቻሉ ነው። እናም ሱዳንን በአግባቡ ከጎርፍ መከላከል የውሃ ብክነትን ስለሚቀንስ ግብፅና ሱዳን የሚጋሩትን የውሃ መጠን ይጨምራል ማለት ነው። ለእዚህ ነው የህዳሴው ግድብ መገንባት የውሃ ድርሻችንን ይጨምራል የምልሽ።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች በዚህ በግድቡ ጥራት ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ሚሊዮን ጊዜ ገልጸውታል። ግድቡ ድንገት ቢፈርስ ደግሞ የአደጋው ሰለባ ሱዳን ናት። ሱዳን ይህንን እያወቀች የግድቡን መገንባት መደገፏ ከምን የመነጨ ነው?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- ሱዳን የግድቡን መገንባት የምትደግፈው ለምንም አይደለም። ስለሚጠቅማት ብቻ ነው፡፡ በኢንጂነሪንግ የአንድ ፕሮጀክት ሥራ የሚወሰነው ጥቅሙና ስጋቱ ተመዝኖ ነው። ሱዳን በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ ትጥለቀለቃለች። ያ ማለት ደግሞ በግድቡ ግንባታ የሚቀርላት የጎርፍ አደጋ ግንባታው ከሚያሳድርባት ስጋት በልጦ ተገኝቷል ማለት ነው።

ሱዳንን በየዓመቱ በጎርፍ እንድትጥለቀለቅና የዜጎቿን ሕይወት እንድታጣ የሚያደርጓት ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሁለት ትላልቅ ወንዞች ናቸው። ጥቁር አባይና አክባራ(ባሮ መሆኑ ነው) ናቸው። እነዚህን ሁለት ወንዞች ተከትለው በ700 ኪሎ ሜትር ውስጥ የተመሰረቱት የሱዳን ከተሞች ለዘመናት በክረምት ጎርፍና በበጋ ድርቅ ሲመቱ ኖረዋል። አሁን ግን ይህ አደጋ ያለው ጥቁር አባይን ተከትለው ባሉት ከተሞች ላይ ብቻ ነው። ምክንያ ቱም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2009 በአክባራ ተፋሰስ ላይ ግድብ ገንብታ ለች። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአክባራ ወንዝ ፍሰት መደበኛ ሊሆን በመቻሉ ከወንዙ ጋር ተያይዞ ጎርፍም ሆነ ድርቅ ሱዳንን እያጠቃ አይደለም። ስለዚህ ሱዳን የግድቡን መገንባት ብትደግፍ ምክንያታዊ ናት።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስት ራችን ሱዳን በተወሰነ መልኩ ገለልተኛ መሆኗን ገልጸው ነበር። ይህን መግለጫ እንዴት ተመለከቱት? እውነት ሱዳን ገለልተኛ እየሆነች ነው? ወይንስ ይበልጥ ከኢትዮጵያ ጋር መወገኗን እየገፋችበት ነው?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- አሁን እኛ ልናተኩር የሚገባን በሱዳንና ኢትዮጵያ መተባበር ላይ አይደለም። ከሁለቱ ሀገር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እንዴት ተባብረን መሥራት እንችላለን በሚለው ላይ ነው ማተኮር ያለብን። ከእነርሱ ጋር መተባበሩ ነው እኛን የሚያዋጣንም የሚጠቅመንም።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ምን አይነት ትብብር? ከእነ ርሱ ጋር በምን መልኩ ነው ተባብረን መሥራት የምንችለው?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- በብዙ መልኩ፤ በብዙ መልኩ መተባበር እንችላለን። ለምሳሌ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ተባብረን መሥራት እንችላለን። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ይህን ግድብ እየገነባች ያለችው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው። ግድቡ እየተገነባ ያለው በጣም ዝቅተኛ በሆነ ስፍራ ነው። የእዚህን ግድብ ውሃ ለመስኖ ማዋል ብትፈልግ ውሃውን ወደ ከፍታ ቦታ ፓምፕ ማድረግ ይጠበቅ ባታል። ይህ ደግሞ ፈጽሞ አዋጭ አይሆንም።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- አዎን የመስኖ ሚኒስትራችንም በቅርቡ ይህን ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- አዎን ልክ ነው። የእኛ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም በበኩሉ ግድቡን የሚገነባው ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት መሆኑን አስታውቋል።

እኔም ለእዚህ ነው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግብፅ የውሃ ድርሻ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም የምለው። ብዙዎች ስለግድቡ መጠን ይጨነቃሉ። እንደባለሙያ ሆነሽ ካሰብሽው ግን ይህ አሳሳቢ አይደለም። ምክንያቱም የግድቡ የመያዝ አቅም ሳይሆን ሊያሳስበን የሚገባው በግድቡ የተያዘው ውሃ የሚውልበት አገልግሎት ነው። ግድቡ መቶ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዞ ኃይል በማመንጨቱ ሳይሆን እኛን የሚጎዳን አንድ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዞ ለመስኖ መዋሉ ነው። በፊት ግድቡን ለመገንባት ሲያስቡ 600 ሜጋ ዋት የማመንጨት ሃሳብ ነበራቸው። አሁን ግን የግድቡን ውሃ የመያዝ አቅም በመጨመር የሚያመነጩትን ኃይል 6000 ሜጋ ዋት ለማድረስ እየሠሩ ነው። ስለዚህ የግድቡን መጠን መጨመራቸው የሚያመነጩትን ኃይል ከፍ ከማድረግ ያለፈ ሌላ ግብ የለውም።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- እርሶ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ መሥራትን እንደ መፍትሔ እያስቀመጡ ነው። ኢትዮጵያ ግን ለውይይት በሯን ክፍት አላደረገችም። ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጉዳዩን እንዲያጠና ስትጠየቅም ፈቃደኛ አይደለችም። ታዲያ እርሶ የሚሉት የጋራ መግባባት እንዴት ይመጣል?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- ውይይቶች እኮ እየተካሔዱ ነው። ምናልባት የነበረውን መልካም የጋራ ውይይትና መግባባት ያደፈረሰው እዚህ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በተገኙበት በምስጢር የተደረገው ውይይት ይመስ ለኛል።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- እሱኮ ከግብፅ ሀገራዊ መግባባት በፊት የተከሰተ ነው። በርግጥ በአጋጣሚ በቀጥታ ስርጭት አየር ላይ ውሏል። ግን ኢትዮጵያን ግትር አቋም እንድትይዝ ያደረጋት ይህ ነው ብዬ አላምንም።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ይቅርታ ፕሮፌሰር ሃይሰም፤ የቀድሞ የግብፅ ውሃ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር ናስር ኣላም በስልክ መስመር ላይ ናቸው::

(ጋዜጠኛዋ ከዶክተር ናስር ኣላም ጋር የስልክ ውይይት ጀመረች።)

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ከዚህ በፊት የግብፅ መስኖ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውይይት መግባባት ላይ ካልደረሰ ግብፅ የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ትጠይቃለች ብሎ ነበር። እስኪ ይህን ሃሳብ ያብራሩልኝ?

ዶክተር ናስር ኣላም፡- በቅድሚያ ፕሮፌሰር ሃይሰም ባነሱት ነጥቦች ላይ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ። የአሜሪካም ሆነ የግብፅ ፕሮፌሰሮች የህዳሴው ግድብ መጠን በግብፅ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አረጋግጠዋል። የአስዋንን ግድብ እንደሚያደርቅ፣ በሀገራችን የውሃ እጥረትን እንደሚያስከትልና ግብፅን ለከፋ አደጋ እንደሚዳርጋት እነዚሁ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

በሌላ መልኩ የህዳሴ ግድቡ መጠን መጨመር የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅምም ከ60 በመቶ ወደ 30 በመቶ እንደሚያወርደው ተደርሶበታል። የመስኖ አገልግሎትንም በተመለከተ ኢትዮጵያ በአካባቢው በመስኖ የሚለማ መሬት አላት። እናም ውሃውን ለመስኖ አገልግሎት የማትጠቀምበት ምንም ምክንያት አለ ብዬ አላስብም።

ወደ ጥያቄሽ ስመለስ ድርድሩን በተመለከተ እ.ኤ.አ የ1959 እና የ1929 ስምምነቶችን ብቻ አትመልከቱ። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1902 በአፄ ምኒልክ ዘመን በጥቁር አባይ ላይ ግድብ ላትገነባ ከግብፅ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ብቻ ሳይሆን እ.ኤ.አ በ1993 የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቀድሞ ፕሬዚዳንታችን ሆስኒ ሙባረክ ጋር ባደረጉት ስምምነት ሁለቱም ሀገራት ከውሃ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ አንዱ ሌላኛውን ላይጎዳ ተፈራርመዋል። እናም ኢትዮጵያ የ1902ቱንም ሆነ የ1993ቱን ስምምነት እያከበረች አይደለችም።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- በዩጋንዳ በተፈረመው የኢንቴቤ ስምምነት መሰረት ከግብፅና ሱዳን በስተቀር ሌሎቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ሊጠቀሙበት ተፈራርመዋል። ይህ ምናልባት ግብፅን በራስ ወደ መወሰን መብቷ (ቬቶ ፓዎር) ይወስዳት ይሆን?

ዶክተር ናስር ኣላም፡- የኢንቴቤው ስምምነት በስድስት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል ተፈርሟል። ግብፅ፣ ሱዳንና ኮንጎ አልፈረሙም። ስለዚህ ስምምነቱን ያልፈረሙት ሀገራት በስምምነቱ ለመገዛት አይገደዱም። ከዚህም ባሻገር ስምምነቱ ገና በየሀገራቱ ፓርላማ ስለሚጸድቅ ተግባራዊ አልሆነም። ስምምነቱም ቢሆን ማንኛውም የላይኛው ተፋሰስ ሀገር በውሃው ላይ ፕሮጀክት ሲገነባ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገር ማሳወቅ እንዳለበትና መጉዳት እንደሌለበት ይደነግጋል።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ማንኛውም ተራ ሰው በቀላሉ መረዳት እንደሚችለው ግድቡ እየተገነባ ያለው አስተማማኝ በሆነ መልከዓምድር ላይ አይደለም። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ዶክተር ናስር ኣላም፡- ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ካሰማሯቸው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን ውስጥ አንዱ ጀርመናዊ ግድቡ የሚገነባበት መሬት አፈሩ የመናድ ባህሪ ያለው መሆኑን አስጠንቅቆ ነበር። እናም ኢትዮጵያውያን ይህን ከግንዛቤ አስገብተው ይሁን አይሁን አላውቅም። ምክንያቱም ግድቡን በመገንባት ላይ ስላሉ።

ሌላው በውይይታችሁ ያላነሳችሁት ዋነኛ ነጥብ አለ። በርግጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሱዳንን ከጎርፍ በመከላከል የተወሰነ ጥቅም ያስገኝላት ይሆናል። ይሁን እንጂ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትተባበር ያደረጋት የኢኮኖሚ ጥቅም ሳይሆን ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያ ባሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ቀንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በሁለቱ ሱዳኖች መግባባት የመሪነቱን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች። ደቡብ ሱዳንንና ሱዳንን የሚለየው ድንበር በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እየተጠበቀ ነው። ኢትዮጵያ በዳርፉር ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሰፊ ሥራ እየሠራች ነው። ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን መንግሥትና አማጽያንን አለመግባባት ለመፍታት ወሳኙን የአስታራቂነት ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ ሶማሊያን ለማረጋጋት በሚሠራው ሥራ ውስጥም ግልህ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። በአንፃሩ ግብፅ ግን በዚህ አይነት ተልዕኮ ውስጥ የለችበትም። ለእዚህ ነው የሱዳንና የኢትዮጵያ ስምምነት ይበልጥ ወደ ፖለቲካው ጥቅም ያጋደለ ነው የምለው።

(ጋዜጠኛዋ ወደ ፕሮፌሰር ሃይሰም ትመለሳለች።)

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ዶክተር ኣላምን አመስግኜ ወደ እርሶ ልመለስና ፕሮፌሰር ሃይሰም፤ እንደተባለው በርግጥ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲዋንና ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሟን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተች መጥታለች። በአንፃሩ ግብፅ በሙባረክ መንግሥት ዘመን ከአፍሪካ ተለይታ ነው የቆየችው። በናስር ዘመን በኢትዮጵያ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት እያለ ማለትም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ለግብፅ የነበራት ክብርና በሁለቱም ሀገራት መካከል የነበረው የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ነበር። አሁን ግን የኃይል ሚዛኑ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እየመሰለ ነው። ግብፅ ይህንን የኃይል ሚዛን ማስተካከል የለባትም ይላሉ?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- ኢትዮጵያ በጥቁር አባይ ላይ ግድብ ለመገንባት ያሰበችው እ.ኤ.አ በ2011 አይደለም። ከ1958 ጀምሮ ነው ስትሰራበት የቆየችው። ግድቡ የግብፅንና የሱዳንን የውሃ ድርሻ ይቀንሳል የሚባለው በፖለቲካዊ ቋንቋ ነው። በርካታ ግብፃውያን እንደእዚያ ያስባሉ። ግድቡ በምን ያክል መጠንና እንዴት የውሃ ድርሻችንን ይቀንሳል ብለሽ ስትጠይቂያቸው ግን ተጨባጭ ማስረጃ የላቸውም። ይቅርታ አርጊልኝና እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም። ከሳይንሱ አንፃር ነው እየነገ ርኩሽ ያለሁት። በሳይንሱ ከሄድሽ ግን ግድቡ ሲገነባ የሚለቀቀው የውሃ መጠን እንደ ከዚህ ቀደሙ ክረምት ብቻ መሆኑ ቀርቶ በመደበ ኛነት ክረምት ከበጋ ይሆ ናል፣ ጎርፍና ደለልንም ይቀንሳል፣ የውሃ ብክነት አይኖርም። ያ ደግሞ የውሃ ድርሻችንን በእርግጠኝነት ይጨምራል።

ሌላው ሊታወቅ የሚገ ባው በ1993 በኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ሚስተር ሙባረክ መካከል የተደረገው ፊርማ ውል አለመሆኑን ነው። ሁለቱም ሀገራት የተፈራረሙት አንዱ ሀገር ሌላውን ላለመጉዳትና በጋራ መሥራትና ማደግ ላይ ያተኮረ የመግባቢያ ሰነድ ነው።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- እንደሚ ባለው ኢትዮጵያ በኢኮ ኖሚ ዕድገት ላይ ትገኛ ለች። ለእዚያ ደግሞ ተጨ ማሪ ኃይል ያስፈልጋት ይሆናል። ለመሆኑ ለእ ዚህ መሰል ፕሮጀክቷ ድጋፍ ፊቷን ወደ በለጸጉ ሀገራት እንደነአሜሪካና እስራኤል አዙራ ይሆን? እነዚህ ሀገራትስ በአፍሪካ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ኢትዮጵያን የሚረዱበት ምክንያት ይኖር ይሆን?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- አዎን ጣልቃ የሚገቡበት ምክንያት አላቸው። በኪዮቶ ስምምነት መሰረት የበለጸጉ ሀገራት የካርቦንዳይኦክሳይድን ልቀት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመደገፍ ቃል ገብተው ፈርመዋል። ይህ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ ታዳሽ ኃይል በመሆኑ ኢትዮጵያን ቢደግፉ ምክንያታዊ ናቸው። ለምሳሌ እኛ ዛፋራና ወንዝ ላይ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ገንብተናል። የኪዮቶውን ስምምነት መሰረት በማድረግ ይህን ፕሮጀክታችንን ፈንድ ያደረገችን ኖርዌይ ናት። እናም በዚህ መርህ መሰረት እነዚህ ሀገራት ለኢትዮጵያም ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ።

እስራኤልና አሜሪካም ኢትዮጵያን ቢደግፉ ከፖለቲካ አንፃር ሳይሆን የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ከሚሠራው ሥራ አንፃር ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ይህን ግድብ ለመገንባት ካሰበችባቸው እ.ኤ.አ 1950ዎቹ ጀምሮ እነዚህ ሀገራት አልረዷትም። ዛሬ ግን እስራኤልና አሜሪካ የኢትዮጵያን ፕሮጀክት ቢደግፉ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ውሃ ለመቀነስ ሳይሆን ዓለም ያለችበት የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት ተጨባጭ ሁኔታ ስለሚያስገድዳቸው ነው።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- ብዙ ሰዎች የታባን የግልግል ተሞክሮ እያነሱ ግብፅ የካበተ የግልግል ተሞክሮ አላት፤ እርሱን ለምን ተግባራዊ አታደርግም ይላሉ። የእርሶስ ሃሳብ ምንድን ነው?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- በፍጹም፤ እርሱ በምንም መንገድ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም። ያ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ከመሰረቱ ማበላሸት ነው የሚሆነው። ሊሰመርበት የሚገባው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ግብፅ የሚገባውን የጥቁር አባይ የውሃ መጠን የሚጨምር መሆኑ ነው። ካስታወስሽ ከ1999 እስከ 2002የክረምት ወራት ግድባችን እጅግ ከመጠን በላይ ሞልቶ ለአደጋ ተጋልጦ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግብፅ በቢሊዮኖች ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት ውሃ በተሽካ ባህረ ሰላጤና በሜዲትራኒያን ባህር ለመልቀቅ ተገድዳ ነበር። የኢትዮጵያ ግድብ መገንባት ከዚህ መሰል አደጋ እንደሚታደገን ሊታወቅ ይገባል።

ሌላው ግብፅ ከሱዳንና ኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት የመግባቢያ ቋንቋ ሳይንሳዊ ቋንቋ መሆን አለበት። አትራፊ የምንሆነው በዚህ ከሄድን ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ግድብ በብዙ መልኩ ሦስቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚ ያደርጋል። ለምሳሌ እዚህ ካይሮም ሆነ አሌክሳንድሪያ ቀን ቀን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ እጥረት አለብን። ማታ ደግሞ መላ ግብፅ ውስጥ ከፍተኛ የኃይል ብክነት ይታያል። ስለዚሀ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር ከቻልን እዚህ ማታ ላይ የሚባክነውን ኃይል ለኢትዮጵያ እየላክን ቀን ላይ የሚከሰተውን እጥረት ደግሞ ከህዳሴው ግድብ በሚመነጨው ኃይል መሸፈን እንችላለን። የግብፅ የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ በ700 ሜጋ ዋት እየጨመረ ይገኛል። ይህ ደግም በየዓመቱ የሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ እያስወጣን ነው። ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ በመዘርጋት በህዳሴው ግድብ በሚመነጨው ኃይል መጠቀም ብንችል ይህን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪያችንን ማስቀረት እንችላለን። እናም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት አማራጫችን ሊሆን ይገባል።

ጋዜጠኛ ዲና ሁሴን፡- አንዳንድ የግብፅ የመስኖና የውሃ ኤክስፐርቶች ግብፅ ፊቷን ወደ ሌሎች አማራጮች መመለስ አለባት ይላሉ። ለምሳሌ እንደነጎንገሌ1፣ ጎንግል 2 ፣ ሻል ማሻል፣ አህለል ካዝል እና የመሳሰሉ ሌሎች ወንዞችን ገድባ የውሃ አቅሟን የማጎልበት ዕድል አላት ይላሉ። እዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው ?

ፕሮፈሰር ሃይሰም ማሃዎዲ፡- በ1983 የጎንግል ካናልን ግንባታ 75 በመቶ አድርሰን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ግንባታ በደቡብ ሱዳን በነበረው ጦርነት ምክንያት ተቋርጧል። በተመሳሳይ መልኩ በባህር ጋባል ላይም ተመሳሳይ ፕሮጀክት በማካሄድ የውሃ ድርሻችንን የማሳደግ ዕድል አለን። ይህም ቢሆን ታዲያ ሊሳካ የሚችለው ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር መተባበር ከቻልን ብቻ ነው።

***********

Daniel Berhane

more recommended stories