የተሳሳቱ ዘገባዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዙሪያ (ዮናስ ቢራቱ)

የተጠለፈውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ (በረራ #ET_702) በተመለከተ ሰሞኑን እጅግ በርካታ የተምታቱ መረጃዎች ሲሰራጩ ሰንብተዋል። ከድጋፍ እና ተቃውሞ ባሻገር አንዳንድ ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ስለ አየር መንገዱ የሚሰጡት አስተያየት ደግሞ ከመጋነን ባለፈ ስህተትም ጭምር ነው።

መረጃ የሚፈልጉ ሚዲያዎች በቀጥታ የአየር መንገዱን ሃላፊዎች ማነጋገር ሲገባቸው በተቃራኒው ስዎችን በመጠየቅ ተጠምደው ከርመዋል።

ይህንን ለማለት ያበቃኝ የኢሳት ጋዜጠኛ የሆነው ፋሲል የኔዓለም አንዲት “በተጠለፈው አውሮፕላን ወደ ጣሊያን ተጉዣለሁ” ያለች መንገደኛ አነጋግሮ ያስተላለፈው ፕሮግራም ነው።

ሴትዮዋ የተጠለፈው አውሮፕላን ሮም ላይ ማረፉን ተናግራለች። ከዚህም በማስከተል <<ጠላፊውን ረ/አብራሪ ሮም ተርሚናል ከእኔ ጋ ወርዶ ሻንጣውን ሲጠብቅ አይቼዋለሁ፤ እንዲያውም በጣም የተጨነቀ ይመስል ነበር>> ብላለች። አውሮፕላኑ ግን ሮም ላይ አላረፈም ነበር። እሷ በተመሳሳይ ቀን የተሳፈርችበት አውሮፕላን የተጠለፈው ሳይሆን ቦይንግ 757 የተባለ ሌላ አውሮፕላን ነበር።

ይህንን መረጃ የነገረን እራሱ ፋሲል ሲሆን ይቅርታ አልጠየቀም። ይህን መረጃ ለህዝብ ማስተላለፉ የተወሰነ ብዥታ ፈጥሯልና ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት። አውሮፕላኑ ሮም አለማረፉን ወደ ሮም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመደወል በቀላሉ ማጣራት ይቻል ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደህንነት ሰራተኛ ነኝ የሚል እንግዳ ኢሳት ላይ በማቅረብ ኢንተርቪው አድርጎ ነበር። በዚህ ኢንተርቪው ላይ የተጠየቀው ሰው የማያውቀውን መረጃ ሲተነትን እንደ ትክክለኛ መረጃ አምኖ ለህዝብ ማስተላለፉ ተገቢ አይደለም። ሰውዬው የሚያወራው ጉዳይ ቀንድ እና ጭራ የለውም። የአንድ ወገን መረጃ ከማቅረብ የአየር መንገዱን ሃላፊዎች ወይም ደግሞ ሌሎች የሚያውቁ ሰራተኞችን መጠየቅ ተገቢ ነበር። ይህ ግለሰብ በርካታ ሃሳቦችን ያነሳ ሲሆን በሁሉም ነገሮች እውቀት እንዳለው በማስመሰል እንደ ዶቅዶቄ ሲንደቀደቅ መስማት ያሳፍራል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰሞኑን በጣም የማከብረው ሌላ ጋዜጠኛ ወዳጄ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ <60% የሚሆኑት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ከአንድ መንደር የተሰበሰቡ ናቸው> ብሎ ጻፈ።

ይህ መረጃ ስህተት ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ በተደጋጋሚ ከሚከሰስባቸው ነገሮች አንዱ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም የትግራይ ተወላጅ መሆኑ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ አየር መንገዱን ከአራት በላይ ሃላፊዎች መርተውታል። የዘር ተዋጾቸውን ለመግለጽ ሃረሪ (አደሬ)፤ አማራ፤ ኦሮሞ እና ትግራይ ናቸው።

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ከ25 አመት በላይ አገልግሏል። በትምህርቱም የማስተርስ ዲግሪ (በአስተዳደር) አግኝቷል። ስውዬውን በቅርብ የሚያውቁት እንደሚናገሩት እጅግ ታታሪ ሰራተኛ ነው ይላሉ። በአስተደዳር በኩል ሰራተኛን የማያከብር እና ትምክተኛ እንደሆነ ብዙዎች ያሰምሩበታል። መቼም የሰውዬውን የአስተዳደር ብቃት አንስቶ መፈተሽ ተገቢ ሲሆን የትግራይ ተወላጅ ነው ብሎ ማቅረብ ግን ፈጽሞ ተገቢ አይመስለኝም። በእርግጥ በትግራይ ተወላጅነቱ እንደተሾመ ብዙዎች ይስማማሉ። ሆኖም ግን ለቦታው አይመጥንም ብሎ የሚሟገት ሰው አልገጠመኝም።

በተመሳሳይ ላለፉት አስር አመታት የአብራሪዎችን ክፍል የመሩት ሁለት ካፒቴኖች የትግራይ ክልል ተወላጆች ናቸው። የመጀመሪያው ካፒቴን ተስፋዬ አምባዬ ሲሆን ለረጅም አመት በአብራሪነት ያገለገለ እና የማስተርስ ዲግሪም የነበረው ሰው ነበር። አሁን ያለው ሃላፊ ደግሞ ካፒቴን ደስታ ዘሩ ይባላል። ካፒቴን ደስታ ሲኒየር ካፒቴን ሲሆን ስራውን በተገቢው መንገድ የሚሰራ ሃላፊ መሆኑን የሚያውቁት ይመሰክራሉ። በነገራችን ላይ የአብራሪዎች ሃላፊ መሆን የሚወደድ ስራ አይደለም። አንደኛ ከበረራ እና ከጥቅማ ጥቅሞቹ ያለያያል። ሁለተኛ ከብዙ ስዎች ጋር ያጋጫል።

እንግዲህ በአየር መንገድ ውስጥ ካሉት በርካታ የሃላፊነት ቦታዎች ውስጥ ሁለቱን የትግራይ ተወላጆች ተሹመውባቸዋል። ይህንንም የተለያዩ ሰዎች ለፖለቲካ ትርፍ ለማዋል ሲሞክሩ ማየት ያሳዝናል። ሰዎቹ ችሎታ ያላቸው ከሆኑ ቢሾሙ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው? ችግር የሚሆነው ምንም ችሎታ ሳይኖራቸው ስልጣንን ለማስጠበቅ ተብሎ የተሾሙ እንደሆነ ነው።

ይህ ሲባል ግን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በትውልድ ላይ የተመሰረተ ሹመት በሚገባ ያውቃል። ሆኖም አየር መንገድን በተመለከተ የሚናፈሱት መረጃዎች ሃሰተኛ መሆናቸውን ከውስጥ አዋቂዎች ለመረዳት በመቻሉ ብቻ ነው።

ሌላው በደሞዝ እና በአስተዳደር ሰራተኞችን ይጎዳል ይባላል። ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ሲወዳደር ክሱ እውነት ቢሆንም ከኢትዮጵያ የመንግስት ድርጅቶች አንጻር ግን ነገሩ ስህተት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት መስሪያ ቤቶች ከሁሉም በተሻለ ነጻነት እና አንጻራዊ ምቾት ያለበት መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ማንም ያውቃል።

ከጥቂት አመት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ የሆነው ሰራተኞቹ አንጻራዊ ክብር ሰለሚሰማቸው እና በፍቅር ለራሳቸው እንደሚሰሩ አሰበው ስለሚተጉ ነው የሚል ጥናት የሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ አውጥቶ ነበር።

ሰሞኑንም ይሄው ጋዜጣ <<የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ነው፤ አሜሪካን አገር ካሉ ብዙ አየር መንገዶች የሚስተካከል ጥራት ስላለው ከጠለፋው በኋላ እንኳን በዚህ አየር መንገድ መብረራችንን አናቆምም>> ሲል ዋና አዘጋጁ ምስክርነቱን ጽፏል።

ሌላ ደግሞ ኒዎርከር ጋዜጣ ላይ አስተያየቱ የጻፈ ተሳፋሪ እንዲህ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

<<I took ET 702 a few weeks ago , and I can express my gratitude for an excelent service on board, gentle and competente crew, and very helpfull and a kind Ethiopian behaviour. … just leave Etiopian Airline out of this!>>

እንግዲህ ረዳት አብራሪው ለምን እንደጠለፈ ምክኒያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ …

በመንግስት ሰዎች “እብድ” እንደሆነ የሚነገረው ፕሮፓጋንዳ በጣም የሚያሳፍር እና አየር መንገዱን የሚጎዳ እንጂ ጥቅም የሌለው ነው።

በቃዋሚዎችም እንዲሁ ጀግና ለማድረግ እና ከዚህም የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ያሳፍራል።

ይህ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ኔልሰን ማንዴላ የመሰከሩለት አየር መንገድ፤
ይህ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አስከትሎ አለምን የሚዞር አየር መንገድ፤
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ሳይከሽፍ የኖረ አየር መንገድ ቢወድቅ የሚጠቀመው ማን ይሆን?

በመጨረሻም

ይህ አየር መንገድ ብዙ ችግሮችን ያለፈ ድርጅት ነው። በደርግ ጊዜ መንግሱቱ ሃይለማሪያም አየር መንገዱን <ትንሿ ካፒታሊዝም በኢትዮጵያ> ብሎ ይጠራው ነበር ይላሉ። ይህም የሆነበት ምክኒያት አንቶኖቭ አውሮፕላኖቹን ከራሺያ ለመግዛት መንግስቱ ግፊት ሲያደርግ ካፒቴን መሃመድ በአስደናቂ ሙግት የአሜሪካ ቦይንግ እንዲገዛ መንግስቱን በማሳመናቸው እና አንቶኖቭም ከመንገደኛ አውሮፕላን ገበያ መውጣቱን ተከትሎ ነበር። በዚህም ምክኒያት መንግስቱ ሃይለማሪያም አየር መንገድ በራሱ እንዲተዳደር ትቶት ነበር። በኢህ አዴግም ይህ ነጻነት የቀጠለ ሲሆን አየር መንገድ ታክስ እንዳይከፍል እና የመንግስትንም ድጎማ እንዳይጠይቅ መለስ ዜናዊ ቃል ገብቶ ነበር።

አሁንም ቢሆን ይህ አንጻራዊ ነጻነት ካልቀጠለ አየር መንገዱ ይወድቃል። በውጤቱም ሁሉም ዜጋ ይጎዳል። ቢያንስ ኩራታችንን በማጣት እንጎዳለን። አበቃሁ።

*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories