‘ብቸኛ’ የብሄር ማንነትና ‘ያልተፈጠረ ኢትዮጵያዊነት’ (የኖላዊ መልዐከድንግል ምላሽ ለፕ/ር መስፍን)

የማነ ናጊሽ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን›› የሚል ጽሑፍ ካተመ ከቀናት በኋላ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የከረረ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ (የሁለቱን ጽሑፍ ይህን ሊንክ ተጭነው ማንበብ ይችላሉ)

የመስፍንን ምላሽ ተከትሎ በተለያዩ ሰዎች አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፤ የሳቸው ምላሽ የየማነን ሀሳብ ከመተቸት አልፎ ሰብዕናውን ብሎም ማንነቱን የሚያጠቃ እንደመሆኑ የተሰጧቸው ምላሾችም በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይ ዝንባሌ ያላቸው ነበሩ፡፡

ኖላዊ መልዐከድንግል የሰጠው አስተያየት እንዲህ ይነበባል፡-

“ብቸኛ” የብሄር ማንነት እና “ያልተፈጠረ ኢትዮጵያዊነት”

ሰሞኑን በማንነት ሙግት መሪዎች የቀረበ ወግ—- “ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ሀሳብ “ያልተፈጠረ ድሪቶ” ሲሆን ንኡስ ማንነት ግን ከዚህ ድሪቶ ብቻዉን ተነጥሎ የሚገኝ ነው፡፡

በርግጥ ይህ የሀሳብ ፍጭት ቅጥ (pattern) እና ስነስርአት ባለዉ መልኩ እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም እኝህ ማበጣበጥ እና ማበሳጨት የማይሰለቻቸዉ መርዘኛ ፕሮፌሰር ከገቡበት በኋላ ለሳቸዉ የሚመች ቅርጽ እየያዘና በአስጸያፊ ስድቦች እየታገዘ መጥቷል። ካረጁ አይበጁ እንዳንላቸዉ ታሪክ ትንተናዉ ላይ በወጣትነታቸዉም በጅተዉ አያዉቁም (የእንጨት ሽበት ነዉ የእሳቸዉ)…እስኪ እድሜ አላስተምር ብሎ የከዳቸዉን ሰዉዬ ጉዳይ በሌላ ጊዜ ልመለስበት።

ለዉይይት ያህል…ሁለት ጥያቄዎች ላንሳ

1. …ለፕሮፌሰር ስንል ነዉ እንዴ ኢትዮጵያዊነትን የምናነሳዉ ወይም የምንጥለዉ?

2. ማንነታችንንስ ዘረኞች ለክተዉ የሚሰጡን ስጦታ እንዲሆን መፍቀድ አለብን?

ሽማግሌዉን በቀጥታ ለመስደብ ይሁን ለመገሰጽ፣ ወይም አድናቂዎቻቸዉን፣ ወረድ ሲልም መጥተዉበታል የተባለዉን አካባቢ ለማንቌሸሽ ነዉ መሰለኝ…ይኸዉ ሰሞኑን ደሞ….ብሄሮችን የሚያስተሳስር አገራዊ ማንነት የለም፤ ከኛ ዉጪ ያለዉ የማንነት ትርጉምም ቆሻሻ ነዉ፤ድሪቶ ነዉ ወዘተ የሚለዉ ሙግት ከፍ ባለ ጩኸት እና ድጋፍ ሰንብቷል! ይህ ብዙ የማያዛልቅ ጨዋታ እንዴት እንደሚቀጥል መገመት ባልችልም በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ። መቼም ቢሆን ብልግናን ብልግና አያስተካክለዉም፤ ጎጠኝነነትን ደሞ ጎጠኛ ሆኖ መታገል አይቻልም!

ሙግቱ ያነጣጠረዉ “ኢትዮጵያዊነት” የሚለዉን ሀሳብ ማሸማቀቅ እና ማንጓጠጥ፤ ትርጉሙንም ከፓስፖርት ጋር ከሚሰጥ እና ከሚቀደድ የአድራሻ ማስረጃነት በላይ ሰብእና የሌለዉ አርጎ ማጥላላት ላይ ነዉ። ከብሄር የዘለለ ማንነት የለም፤ ኢትዮጵያዊነት በሚባለዉ ነገር ካመንክበት ደሞ ድሪቶ ነህ ብሎ የራስን እምነት በሌሎች መብት ላይ ለመጫን መሞከር “ማንነት” ምርጫ መሆኑን መርሳት ነዉ።

ማንነታችንን እንደ ብዙህነታችን ሰፊ አርጎ የመተርጎም ነጻነት የሚሰጥ ህገመንግስት አለ! ነገር ግን ብዙህ የሆነ ማንነትን የመምረጥ መብት በህገመንግቱ መስፈሩን ተረድተዉ ነዉ የሚደግፉት ከምላቸዉ ሰዎች ሲመጣ እና ክልልተኛ ካልሆንክ እና እሱንም ብቻ ካላፀደክ አብረን አናወራም የሚል ሲጨመርበት፤ እንዴ..ኧረ እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸዉ ያስብላል!

በ Creative deconstruction እየተጠረበች እና እየተሰራች የነበረችዉ ኢትዮጵያ የት ገባች?

ንኡስ ማንነት ወሳኝ እና ሊቀር የሚችልም፤ የሚገባዉም አይደለም። አካባቢያዊ ማንነት አይኑርህ ማለት ቤተሰባዊ ማንነት አይኑርህ ማለት ነዉ! አካባቢያዊ ዝምድና በማንነት ዉስጥ ያለዉ ዉክልና ሰፊ በመሆኑ መኖሩ እና መበልጸጉ የሚገባ ነዉ። እዚህ ላይ ጥያቄ የለም!

ንኡስ (አካባቢአዊ፤ ክልልተኛ) ማንነት ዋናዉም እዉነተኛዉም እሱ ብቻ ነዉ ከተባለ ግን በጋምቤላ ያለዉ ጉዳይ አይመለከተኝም ማለት ነዉ (ነገሩ በግልጽ የሚታይ እና ቀጥተኛ ጉዳት በእኔ ላይ ካላመጣ)። ምክንያቱም ከአካባቢዉ ጋር ዉልደትም ሆነ ቁርኝት የለኝም። ከዚያ አዉራጃ፤ወንዝ እና ህዝብ ጋርም ትስስር የለኝም (የለም ባዬቹ እንዳሉት)፤ ኩታ ገጠም ብንሆንም እንኳን እኔን ከአንድ አኙአክ፤ሶማሌ፤ሀዲያ ወይም ከቀሩት 80 ብሄሮች ጋር የሚያደራርሰኝ ነገር የለም።

ህዝቦች ዉልደት ሳይኖራቸዉ አብሮነት የሚሰማቸዉ እና የጋራ አገር የሚፈጥሩት ከንኡስ ማንነት በላይ የሆነ ተዛምዶ ሊኖራቸዉ ከቻለ ብቻ ነዉ። እስከዛሬ የነበሩ የዉስጥ እና የዉጪ ችግሮች እና ወረራዎችን ማለፍ የቻለችዉ አገሪቷ በጂኦግራፊ ምክንያት በአጋጣሚ የተገነባች መጠለያ በመሆኗ አይመስለኝም። ይልቅስ የደም እና የባህል ትስስር ሳይወስነዉ በጋራ የሚቆጭለት እሴት እና የሚሞትለት የጋራ ማንነት በህዝቦቿ መሀከል በመኖሩ ነዉ!

ባይሆን ኖሮ ባለፉት መቶ አመታት ኢትዮጵያዉያን ከሚኖሩበት በሺዎች ኪሎሜትሮች ርቀት ሄደዉ ለምን “ለሀገር” ሞቱ? ነገስታቱስ ተራራ አቌርጠዉ ቌንቌቸዉን ከማይናገር መሬት ላይ ለምን በደርቡሸ ሰይፍ ተገደሉ? የተዋጉበትን መሬቱ አልወረሱም፤ ታድያ ለድንበሩ ለምን አንገታቸዉን ሰጡ?

ባድመ ስትወረርስ የአርባ ምንጭ፣ የጎጃም እና የድሬዳዋ ልጆች ለምን ወረራዉ ተመለከታቸዉ? ሎጂኩን ከተከተልን መጠለያዉ ከነሱ እርቆ በመገኘቱ የቄሳርን ለቄሳር ብለዉ መቀመጥ አልነበረባቸዉም?! የሚገርመዉ ሻእቢያም በወቅቱ የወረረን፤ጉዳዩ የትግራይ እንጂ የሌላዉ ህዝብ አይሆንም፤ ኢትዮጵያም ግዙፍ በሆነ የንኡስ ማንነት አጥር ተከፋፍላለች በሚል የስህተት ግምት ተማምኖ ነበር። የኢትዮጵያዉያንን የጋራ ሰብእና አሳንሶ ባይመዝነዉማ ጉልበት ያለዉን እና የጋራ ቁጭት አገንፍሎ የሚያወጣዉን ህዝብ በጤነኛ አእምሮዉ አይደፍርም ነበር። አገሪቷ እናንተ እንደምትሉት የሚተሳሰሩበት ሰብእና የሌላቸዉ የራሳቸዉን የተገነጠለ ንኡስ ማንነት ይዘዉ የተቀመጡ ብሄሮች መጠለያ ብትሆን ኖሮ እስከ አሁን ባልኖረች።

ንኡስ ብሄርተኝነት ችግር አይደለም፣ ተፈጥሮአዊ የሆነ እና መከበር ያለበት መብት ነዉ! አገራዊ ማንነትንን መጨፍለቅ እና መተካት ሲጀምር ግን ለአብሮ መኖርም ሆነ አብሮ ማደግ ከባድ የህልዉና ፈተና ይሆናል። በኤርትራ ወረራ እና አሁን ደሞ በአባይ ግድብ ዙሪያ በተለያዮ አገሮች ያሉ ጠባብ ተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን ደጋፊዎቻቸዉን ያሳመጹት ከንኡስ ብሄርተኝነት በላይ ለማየት ባለመፈለጋቸዉ ( ወይም የለም ብለዉ በማመናቸዉ ነዉ)። መነሻና መድረሻቸዉ ክልልተኝነት ብቻ በመሆኑ ለነሱ የሻእቢያ ወረራ የትግራይ ችግር ነበር፤ የአባይ ግድብ ደሞ በስልጣን ላይ ያሉት “ንኡስ አካላት” ጭቆናዉን የሚያስቀይሱበት ስልት ነዉ። የትኛዉም ሀሳብ እና እቅድ ለነሱ አገራዊ መልክ የለዉም። ክልላዊ ብቻ ስለሆኑ ከክልል ዝምድና አንጻር ይደግፋሉ፤ይቃወማሉ። ይህ በየአገሩ ባሉ “ኢትዮጵያዊያን” ዘንድ “ኢትዮጵያዊ” አጀንዳ በተነሳ ቁጥር ያለ እዉነታ ነዉ! ከንኡስ ማንነት በላይ ማየት ስለማይችሉም ነዉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እግር ስር ወድቀዉ የኢትዮጵያ መንግስትት የሚጥሉበት መሳሪያ እና ብር የሚለምኑት።

ከንኡስነት ዉጪ መንገድ የለም ከሆነ ግን ነገ የትኛዉንም ብሄራዊ ጉዳይ፤ አባይንም ጨምሮ “አገራዊ ጥቅም” በሚባሉ አጀንዳዎች ከታሪክና እና ከጋራ እሴት አንጻር መዝናችሁ ማቅረብ አትችሉም! ስለ አባይ ግድብ የምንጮኸዉ ከብሄራዊ ማንነት እና መብት አያይዘን እንጂ ግድቡ ሲያልቅ የሚገኘዉ ኤሌትሪክ በጋራ ስለሚያጓጓን አይደለም! እይታችን ከኤሌትሪክ በላይ የሆነ፤ለድርድር የማይቀርብ ለዘመናት የቆየ መብትን የማስከበር ህልም ላይ ነዉ።

በዚህ አተያይ ነገ እነ እከሌ ካይሮ ላይ ኢትዮጵያን አይደለንም ብለዉ ሰልፍ ወጡ፣ አስመራ ላይ ተሰባስበዉ ኢህአዴግን ለማዉረድ ተማማሉ የሚል ዜና ስትሰሙ በጠባብነት እንዳትፈርጇቸዉ! ከመዋለድ በላይ ትስስር እስከሌላቸዉ ድረስ አገራዊ ስሜት፣ አርበኝነት፤ብሄራዊ ጥቅም በሚሉ መመዘኛዎችም ልትከሷቸዉ አትችሉም። ትክክለኛዉ ማንነት ክልልተኛ ብቻ ነዉ የሚል ቡድን በጠባብ ንኡሳዊ ማእቀፍ የሚንቀሳቀስን ቡድን በምንም አጀንዳ በጭራሽ ሊከሰዉ አይችልም።

ሰፋ አርገን ካየነዉ…ኢትዮጵያ በንኡስ ማንነት ብቻ ሊኖሩባት የሚቻልባት አገር አይደለችም። የመንግስቷ አወቃቀር፣ የህዝቡ ዝምድና እና የአስተሳሰብ መስተጋብር፤ በድህነት ዉስጥ እንኳን ህይወት ያለዉ አዉራጃ እና ክልል ተሻጋሪ ማንነት አላት!

ንኡስ ማንነት ጎልቶ በወጣበት ባለፉት አመታት እንኳን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ያህል ድንበርህ፤ ታሪክህ፤ ማንነትህ፤ መለያህ፤እና ገለመሌህ ተነካ የሚለዉን ዘፈን ማዘፈን ግድ የሚያረግ ሁኔታ ዉስጥ ገብተናል። ይህ በንኡስነት አጥር መወሰን የማይቻለን ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመኖሩ በቂ ማሳያ ይመስለኛል።

በደህና ቀን ያጣጣልነዉ ኢትዮጵያዊነት በችግር ቀን ያሰባስበናል የሚል ተስፋን ለመቀበል ያስቸግራል!

********

* የፕሮፌሰሩን ምላሽ ተከትሎ በተለያዩ ሰዎች የተሰነዘሩትን ሀሳቦች በወፍ በረር የሚያስቀኝንን የከበደ ካሣን ጽሑፍ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ)

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories