‹በኢሳት ላይ የቀረበው ዘገባ በጣም የተሳሳተ ነው› – የጠላፊው ታላቅ ወንድም

ኢሳት የተባለው የዲያስፖራ ሚዲያ የኢትዮጲያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ቁጥር 702ን ጠልፎ ጄኔቭ ያሳረፈው ኃይለመድህን አበራን አስመልክቶ ያስተላለፈው ዘገባ ከእውነት የራቀ መሆኑን ቤተሰቡ ገለጸ፡፡

በዶ/ር ብርሀኑ ፓርቲ ‹‹ግንቦት 7›› አመራር እና የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ኢሳት በዛሬው ዕለት ባቀረበው ዘገባ፤ በውጭ ሀገር ነዋሪ የሆኑ የጠላፊውአክስት ነኝ ባይ ሴትዮ በማቅረብ ጉዳዩን ‹‹አማራን ነጻ የማውጣት›› ትግል አድርጎ አቅርቦታል፡፡

ሴትዮዋ ኃይለመድህን በአየር መንገዱ ከመቀጠሩ በፊት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ እንዲሁም በአየር መንገዱ የአንድ-አምስት አደረጃጀት እንዳለ እንደነገራቸው በማውራታቸው ስለጠላፊው ጋር ሆነ ስለአጠቃላይ ጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ላይ ጥርጣሬ የፈጠረ ሆኗል፡፡

ሴትዮዋ ‹‹ኃይለመድህን መንግሰትን በመቃወም በፌስቡክ ላይ ይጽፍ ነበር›› በሚል የተናገሩትንም የሥራ ባልደረቦቹ እና የፌስቡክ ጓደኛ የነበሩ ሰዎች ያጣጣሉት ሲሆን፤ ልጁ በፌስቡክ ላይ እምብዛም ተሳታፊ እንዳልነበር፣ ፖለቲካዊ ነገር እንደማይጽፍ እንዲያውም የፌስቡክ ገጹም ከተዘጋ ወራት እንደተቆጠሩ ለሆርን አፌርስ ገልፀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ለሆርን አፌርስ በስልክ አስተያየት የሰጡት የጠላፊው ታላቅ ወንድም ተወልደመድህን አበራ፤ ‹‹በኢሳት ላይ የቀረበው ዘገባ በጣም የተሳሳተ ነው›› ብለዋል፡፡

አክለውም ሚዲያዎች ከያቅጣጫው – ከአውቃለሁ ባይ የተገኘ ወሬን ከማውጣት እንዲቆጠቡ ተማጽነዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከሱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንደሌለን መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ አሱ የሚፈልገውን ሳናውቅ ብዙ ለመናገር ያዳግተናል፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር ጉዳዩ ፖለቲካዊ አይደለም፣ ኢኮኖሚያዊ አይደለም›› ብለዋል፡፡

የጠላፊው ወንድም ለግዜው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም፤ ከቤተሰቡ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ ለአሉባልታ በር እንደሚከፍት በመግለጽ ለሰጠናቸው አስተያየት በሰጡት ምላሽ የቤተሰቡን አስተያየት(position) በመግለጫ መልኩ አዘጋጅተው እንደሚልኩ ቃል ገብተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና – ኢምፔሪያ ሆቴል አካባቢ የሚገኘው የኃይለመድህን ቤት ላይ ትላንት ወንድሞቹ በተገኙበት በፖሊስ ብርበራ ማካሄዱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ስለብርበራው ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት አልተሳካልንም፡፡

የ31 ዓመቱ ኃይለመድህን አበራ በባህርዳር ከተማ ተወልዶ ያደገ፤ በከተማው በመጋቢት 28 ትምህርት ቤት እና በባህርዳር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በከፍተኛ ውጤት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደገባ፤ ከ4ኛ ዓመት ትምህቱን አቋርጦ ገብቶ በኢትዮጲያ አየር መንገድ እንደተቀጠረ እና ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን ሆርን አፌርስ-እንግሊዝኛ የጠለፋው የዕለቱ ዕለት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ዘግየተን እንደተረዳነውም የወላጆቹ ተቀዳሚ መኖሪያ በደቡብ ጎንደር ዞን ደልጊ በተባለ አካባቢ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡

በሌላ በኩል ልጁን በቅርበት እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች ‹‹የአዕምሮ ሁኔታው የተጋጋ አልነበርም›› በሚለው ዘገባ ላይ ጥርጣሬያቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ‹‹እስከምናውቀው ድረስ ከአንድ የተሳካለት ወጣት የተለየ ባህርይ ያልነበረው፣ መኪና መንዳትና ቪዲዮ ጌም የሚወድ ነበር›› ብለዋል፡፡(በዚህ ነጥብ ላይ በስፋት የምንመለስበት ይሆናል)

*******

Daniel Berhane

more recommended stories