ኦሮሞ የUN አባል አይደለም እንዴ? ትግራይስ፤ ወላይታስ?

(ከበደ ካሣ)

ከሰሞኑ የፌስ ቡክ ጓደኛችን እንደርታ መስፍን <የሀገር ፍቅር> በሚል ርዕስ መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ እኔም ፅሁፉን ስለወደድኩት ሼር አደረግሁት፡፡ ታዲያ የፌስቡክ አለምን ከተቀላቀለ 5 አመት ከ4 ወር ቢሆነውም እስካሁን <ለአቅመ ሼርንና ፖስትን ልየታ> ያልደረሰ አንድ ፀሃፊ /ግርማ ካሳ ይባላል/ ፀሃፊው እኔ መስዬው እንዲህ ሲል ትችቱን ጀመረ፡፡

<<ከበደ ካሳ የሚባሉ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ግለሰብ “አንዳንድ ሰዎች «ብሄር?» ተብለው ሲጠየቁ «ኢትዮጵያዊ» እያሉ የሚመልሱት፣ የራሳቸዉን ማንነት የኢትዮጵያ ማንነት አድርገው ያስቀመጡና በራሳቸው ማንነት የሌሎቹን ለመጨፍለቅ የሚያልሙ – የቅዠት ታንኳ ቀዛፊዎች ናቸው…. ተዛብታችሁ ሌላንም ለማዛባት ለምትፈልጉ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጂ ብሄር አይደለም። ኢትዮጵያ ሃገር እንጂ የአንድ ሕብረተሰብ ክፍል መለያ አይደለም።” የሚል አባባል ፌስቡክ ላይ ለጥፈው አነበብኩ>>

አቶ ግርማ በዚህ የእኔ ባልሆነ ፅሁፍ መነሻነት ልቤ እስኪጠፋ ቀጠቀጠኝ፡፡ እሱ የእኔ መስሎት የተቸውን ከእንደርታ መስፍን ሀተታ የተቀነጨበ አንቀፅ ሙሉ በሙሉ የምደግፈው በመሆኑ እኔም ለተሰነዘረብኝ ጥቃት ይህን ረጅም የመልሶ ማጥቃት ፅሁፍ አዘጋጀሁ፡፡ ልብ በሉ፤ የቅራኔያችን መነሻ የሆነው ነጥብ <ብሔር ሲጠየቁ ኢትዮጵያዊ እያሉ መመለስ የራስን ማንነት በሌሎች ላይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጅ ብሔር ስላልሆነ> ‘ማለቴ’ ነው፡፡

የአቶ ግርማ ዋነኛ የመከራከሪያ ነጥብ <ብሔር> የሚለው ቃል በተለያዩ ቋንቋዎች ያለው ትርጉም ነው፡፡ የእንግሊዘኛ ትርጉሙን ያስቀድምና እንዲህ ይላል፡፡ <<ብሄር በእንግሊዘኛ ኔሽንስ ማለት ነዉ>>፡፡ ኔሽን ማለት ደግሞ ሀገር ማለት ስለሆነ ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው ሲል ይደመድማል፡፡ መዳረሻው ደግሞ አንድ ግለሰብ ብሔሩን ሲጠየቅ የተጠየቀው ሀገሩን ስለሆነ <ኢትዮጵያዊ ነኝ> ቢል ትክክል ነው የሚል ነው፡፡

ወደ ግዕዝ ቋንቋ ያቀናናም ሌላ የሚደግፈውን ነጥብ እንዲህ ሲል ያነሳል፡፡

<<«ብሄር» የሚለዉን ቃል የመጀመሪያ አመጣጥ ስንመለከት ከግእዝ የተወሰደ እንደሆነ እንረዳለን። ትርጉሙም በግእዝ አገር ማለት ነዉ>>፡፡

አቶ ግርማ ካሳ ለትርጉሙ ትክክለኛነት እንደማረጋገጫ ያቀረበው ቀጣዩ ምሳሌ ይልቅ ትኩረትን ይስባል፡፡ <<«ዩናይትድ ኔሽንስ» ስንል የተባበሩት መንግስታት (የተባባሩት አገሮች) ማለታችን ነዉ ። እንደሚገባኝ ኢትዮጵያ እንጂ፣ ኦሮሞ፣ ወይንም፣ ትግራይ ወይንም ወላይታ የተባበሩት መንግስታት አባል አይደሉም>> ይላል፡፡ እኔ የምለው ደግሞ ትግራይ የተመድ /UN/ አባል ካልሆነ፤ ኦሮሞ የተመድ አባል ካልሆነ፤ ጉሙዝ የተመድ አባል ካልሆነ፤ አፋር የተመድ አባል ካልሆነ፤ … ወዘተ የተመድ አባል ካልሆኑ ማን ነው ታዲያ የተመድ አባል የሆነው? አቶ ግርማ <የኢትዮጵያ ተራሮች፤ ወንዞችና ሸለቆዎች> እንደማይለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው፡፡ ሰው ከሌለ ሀገር አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ያለችው እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ስላሉ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የተመድ አባል የሆኑት እነዚሁ ብሔሮች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

አቶ ግርማ የእንግሊዝኛና የግዕዝ ትርጉምን መሰረት አድርጎ ያቀረበው መከራከሪያ ግን አስቀድሞ ግምት ውስጥ ያላስገባቸው ወይም ያልመለሳቸው ሌሎች ጥያቄዎች አሉ፡፡
1. በዚች ሀገር ውስጥ 76 ያክል ብሔሮችና ብሔረሰቦች አሉ፡፡ /የእነዚህን መኖር እሱም አልካደም፤ ቢያንስ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግራይ፤ ወላይታ፤ ሲዳማ… የሚባሉትን በዚህ ፅሁፉ የተለያዩ ቦታዎች ጠቃቅሷል/፡፡ ታዲያ ብሔር ማለት ሀገር ነው ካለ 76 ሀገር ነን ማለት ነው?
<አዎ፤ 76 ቦታ ከፋፍሎ ኢሕአዴግ ነው ባለብዙ ሀገር ያደረገን> እንዳትልና እኚያ በፆም ወቅት እንቁላል በጧፍ ሲጠብሱ ተይዘው “ሰይጣን ነው ያሳሳተኝ” ያሉትን መነኩሲት ተረት እንዳልተርትብህ፡፡ ሰይጣኑ ከች ብሎ “ይችን አይነት አጠባበስማ እኔ ራሴ ያለ ዛሬ አላውቃትም” እንዳለው ሁሉ ኢሕአዴግም <እንዲህ አይነት የቃል ትርጓሜ ሰጥቼም ሰምቼም አላውቅም> ማለቱ አይቀርም፡፡ ይሄው እጅ ከፍንጅ <<ብሔር ማለት ሀገር ነው>> ስትል የተያዝከው አንተው ነህ፡፡

2. ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው ካልክ ሀገር ማለትም ብሔር ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቃላት በአንተ ትርጉም መሰረት አቻ ስለሆኑ፡፡ ግን አቶ ግርማ እስካሁን ሀገርህን/ ዜግነትህን ስትጠየቅ ብሄርህን ተናግረህ ታውቃለህ? ኢትዮጵያን እንጅ አማራነትህን እንደማትጠራ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ብሔር ማለት ሀገር ከሆነ ብሔርህ ሲጠየቅ <አማራ> ማለትን ጠልተህ <ኢትዮጵያዊ> ማለት የመረጥክበት ምክንያት ታዲያ ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ የማነሳው ሁለቱን ቃላት አመሳስለህ ሳለ ብሔርን ጥለህ ኢትዮጵያዊነትን ያነሳህበት ምክንያት ግልፅ ስላልሆነልኝ ነው፡፡

እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ያነሳሁት አቶ ግርማ ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው ስላለ በራሱ አገላለፅ ልሞግተው ብዬ እንጅ ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው ወደሚለው አመለካከት ወርጄ አይደለም፡፡

ብሔር ማለት በህገ መንግስቱም ላይ እንደሰፈረው ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልዉና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የስነ-ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክአ ምድር የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡

ይህ ጉዳይ በሶሻል ሚዲያው መነጋገሪያ ከሆነ ጀምሮ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ ብስራት ተሾመ ነው፡፡ ብስራት በፌስቡ ገፁ ያሰፈረው ብሔር አንድን የህብረተሰብ ክፍል ከሌሎቹ የሚለየው የማንነቱ መገለጫ ወይም መታወቂያው መሆኑን ነው፡፡ ይህም እንደ ቋንቋ፤ ባህል፤ ሃይማኖት፤ ስነልቦና፤ ወዘተ… ያሉ እሴቶች መስተጋብር እንደሆነ ገልጧል፡፡

ገዳ ገናሞ በሚል ፌስቡክ አካውንት ላይ የወጣ ፅሁፍ ደግሞ የጋራ ጠባይ፤ የኑሮ ዘዴ፤ የጋራ ታሪክና የተለዩ እምነቶችም ይህንኑ ማንነት የሚያዳብሩ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ በነዚህ እሴቶች ላይ የተመሰረተው ማንነት አንድን ግለሰብ፤ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ከሌሎቹ እንዲለይ ያደርገዋል ይላል፡፡
ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ /ግልፅ እንዲሆንለት ለሚፈልግ ሰው/ የሀገርንና የዜግነትን ትርጉምም ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሀገር ማለት በአንድ የተወሰነ/የተከለለ ቦታ የሚኖሩና በመንግስት አስተዳር የሚመሩ ሉዓላዊ ህዝቦችን የያዘ ፖለቲካዊ ፍጥረት ነው፡፡ ዜግነት ደግሞ በዛ በተወሰነ/በተከለለ ቦታ የሚኖሩ፤ በዛ ሀገር ህግ መሰረት የተደነገጉ መብቶችንና ጥቅሞችን የማግኘት ስታተስ ያላቸውን ሰዎች የሚያመላክት ነው፡፡

ስለሆነም አማራ፤ ሲዳማ፤ ሽናሻ፤ ጋሞ… ወዘተ የሚባሉት የብሔር ስም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ እነዚህን ብሔሮችና ብሔረሰቦች አቅፋ የያዘችው ሀገር ስም ነው፡፡ በዚች ሀገር የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ ደግሞ የየራሱ ማንነት ያለው ሲሆን የጋራ የሆነ የኢትዮጵያዊነት ዜግነትም ይኖረዋል፡፡ ለዛም ነው ዜግነት ሲባል ኢትዮጵያዊ የሚባለው፡፡ አንድ ሰው ዜግነቱን ሲጠየቅ ብሔሩን እንደማይጠራ ሁሉ /አለመጥራቱም ትክክል ነው፤ ምክንያቱም የተጠየቀው ስለተወለደባት ወይም ስለሚኖርባት ስትል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና ሌሎች ጥቅሞችን /rights and privileges/ ያጎናፀፈችውን ሀገር ስለሆነ/ ብሔሩን ሲጠየቅም ኢትዮጵያዊ ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተጠየቀው እሱን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚለየውን ማንነት /identity/ ስለሆነ ነው፡፡

ከዚህ ተነስቶ ማለት የሚቻለው ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፤ ቋንቋዎች፤ ባህሎች፤ ሃይማኖቶችና የተለያየ ስነ ልቦናዊ አንድነት ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ ስለሆነች የአንድ ህብረተሰብ ክፍል ማንነት /Identity/ ልትሆን አትችልም ነው፡፡ ይህን ነጥብ ለማጠናከር በዚሁ ፅሁፍ ስር የተሰጠን አስተያየት ልጥቀስ፡፡ ራማቶሃራ በሚል ስም የሚታወቅ ፌስቡከር እንዲህ ሲል አስተያየቱን አስፍሯል፡፡

“ጎበዝ እውነት እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ብሎ አገር እንጂ ብሄር ከቶ ሊኖር አይችልም፤ በእርግጠኝነት አንድ ሰው አገሩን መቀየር ይችላል፤ ብሄሩን ግን በፍፁም መቀየር አይቻለውም፡፡ በዚህ ስሌት ከሄድን ኢትዮጵያዊ ዜጋ የነበረ ሰው ህጋዊ በሆነ መንገድ አሜሪካዊ፤ ካናዳዊ፤ እንግሊዛዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ዜግነቱን የቀየረው ግለሰብ ምንም አገሩን (ዜግነቱን) ቢቀይር ብሄሩ ግን አብሮት እስከ እለቱ ሞቱ የሚቆይ የእርሱነቱ መገለጫ ስለሆነ ሊቀይረው አይቻለውም”

ራማቶሃራ ያነሳው ሃሳብ ማለትም ብሔርና ዜግነት ያላቸው የመቀየር እና ያለመቀየር ጉዳይ ሌላው የሁለቱን ጉዳዮች ልዩነት የሚያሳይ ነው፡፡ የማነ ነጋሽ ይህን ጉዳይ በሚከተለው መልኩ ነው በምሳሌ ያብራራው፡፡

“ኢትዮጵያዊነት እንደእኛው አይነት የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ወገኖች ወደውና ተስማምተው የሚያስሩት ቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳን ደግሞ ውል ነው፤ ሲፈለግ ይታሰራል ሳይፈልግ ሲቀር ይፈርሳል፡፡ ሌላም ውል ሊታሰር ይችላል፡፡ እየሰፋም ከሄደ በአገሮች መካከል ህብረት ይፈጠራል፤ አንድ አህጉር፣ አንድ አለም እያለ ይቀጥላል፡፡

ይኼው ኅብረት ግን እኛ ጋር ተጣብቆ የሚኖርበት ግዴታ የለም፡፡አዲስ ሀገር፣ አዲስ ዜግነት ይፈጠራል፤ አዲስ ማንነት ግን አይፈጠርም፡፡ በአሁኑ ግዜ በኤርትራ የሚገኙት ተጋሩ(ትግራውያን) በቃ ተጋሩ ናቸው፡፡ አትዮጵያውያን ነበሩ፤ ዛሬ ግን አይደሉም፤ አንድ ውል አፍርሰው ሌላ ውል መስርተው ይኖራሉ፡፡ በአገራችን ያሉት ዓፋሮችም ሆኑ ሶማልያውያንም አንዲሁ፤አሁን የገቡት ውል ካልመሰላቸው አፍርሰው አዲስ ውል ሊያስሩ ይችላሉ፡፡ ሌላ ሀገር፣ ሌላ ዜግነት እንጂ ሌላ ማንነት ግን አይኖራቸውም፡፡ ዜግነታቸው ከአገር አገር የሚቀያይሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ነው፤ማንነታቸው ማንም አይነካውም፡፡”

ብስራት ተሾመ በጠቀስኩት ፅሁፉ ላይ ኢትዮጵያዊነት እንደ ማንነት/ብሔር ሊቆጠር ይችላልን? ሲል ጥያቄ ያነሳል፡፡ የሰጠውም ምላሽም እንዲህ የሚል ነው፡፡

“እኔ አይችልም ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም ማንነት/ብሄር መመሳሰልን ይጠይቃል፡፡ ሊገለፁ የሚችሉና በሌላው ሊታወቁ የሚችሉ የጋራ እሴቶች መኖርን ግድ ይላል፡፡ ግን ኢትዮጵያውያን አንድ አይነት አይደሉም፡፡ ሁላችንንም አንድ የሚያደርገን መታወቂያ ወይም መገለጫ የለንም፡፡ ማንነት ማለት ስለ ቋንቋ፤ ስለ ባህል እና ስነልቦናዊ አንድነት ነው፡፡”

በነገራችን ላይ አሁን አሜሪካ ወይም ሌላ ሀገር ዜግነቱን ቀይሮ የሚኖር ሰው ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስረው አንድ ሀረግ አለ፤ ብሔሩ፡፡ አቶ ግርማ ኢትዮጵያዊነት እንጅ ብሔር ብሎ ነገር የለም ብሎ ሲደመድም ዜግነታቸውን ቀይረው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱ ሰዎችን ማንነት እየካደ መሆኑን አልተረዳውም፡፡ ቢረዳውማ ቢያንስ በሱ መሰል ትምክህተኞች ላይ እንዲህ አይነት ደባ ባልፈፀመ ነበር፡፡

አቶ ግርማን <<ትምክህተኛ>> ስል ትንሽ ሽክክ፤ ስቅቅ አላችሁ አይደል፤፤ ጠላታችሁ ይሳቀቅ፡፡ እኔም ወድጄ አይደለም፤ ግድ ሆኖብኝ ነው፡፡ ግርማ ለብሔሮች ያለውን ንቀት በዚች ቁራጭ ፅሁፉ ላይ እንኳን ለጉዳዩ የማይመጥኑ ቃላትን በመጠቀም አሳይቷል፡፡ ጥቀስ ካላችሁኝ፤ <<ኦሮሞኛ ተናጋሪው ከአማርኛ ተናጋሪው ተደባልቋል>>፤ <<ከንባታዉ ከሃዲያዉ …ሁሉም ተበራርዟል>>፤ <<የዘር ሳጥን>> የሚሉት አገላለፆች ግርማ ሆን ብሎ በፅሁፉ የተጠቀመባቸው ናቸው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ትምክህተኝነት ከየት ይምጣላችሁ?

ለነገሩ ከእኔም በባሰ ግርማንና መሰሎቹን የሚተች ሌላም ፅሁፍ በአንድ ብሎግ ላይ ከሰሞኑ አንብቤያለሁ፡፡ ቀጣዩን አንቀፅ በማንበብ ብቻ ፀሃፊው ምን ያህል በመረረ አነጋገር ይህን ብሔርን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አንድና ያው አድርጎ የማቅረብ አመለካከት እንደኮነኑት መረዳት ይቻላል፡፡

<<ኢህአዴግ የዘረጋው አስተዳደራዊ መዋቅር ይሄ የብሄር- ብሄረሰቦችን የማንነት ጥያቄ በተንሸዋረረ አይኑ ያይና በደነቆረ ጆሮ ይሰማ የነበረውን ሰርዓት ለመጨረሻ ግዜ ሲያስወግደው፤ እነዚህ ‘የብሄር ማንነት’ ጥያቄ ሲነሳ “ኢትዮጲያዊ ነኝ” የሚሉት ደግሞ በተወገደው ስርዓት የታወሩና የደነቆሩ የከተማ አፈ-ጮሌዎች ናቸው>>

ራሱን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ብቸኛ ጠበቃ አድርጎ የቆለለው የትምክህት ሃይል በአንድነት ካባ ስር ሊደብቀው የሚሞክረው አመለካከት ተቀባይነት እንዲያገኝለት የሚጠቀምበት ንግግር ብሔርተኝነት <ኢትዮጵያዊነትን ያላላል>፤ <ኢትዮጵያዊነትን ያጠፋል> የሚል ነው፡፡ ዋለልኝ ይህንን አመለካከት ያኔ በ1960ዎቹ በገዥው መደብ የሚመራና ሳይፈልጉ በተቀበሉት የዋህ ተከታዮቹ የሚናፈስ የውሸት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት /fake Ethiopian Nationalism/ ብሎት ነበር፡፡ መልኩን ቢቀይርም አሁንም ድረስ ይዘቱ ያው የሆነውን ይህንን አመለካከት ለመረዳት ኖላዊ መልዓከድንግል ፌስቡክ ላይ ያሰፈረውን ፅሁፍ በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

“ንኡስ (አካባቢያዊ፤ ክልልተኛ) ማንነት ዋናዉም እዉነተኛዉም እሱ ብቻ ነዉ ከተባለ ግን በጋምቤላ ያለዉ ጉዳይ አይመለከተኝም ማለት ነዉ (ነገሩ በግልጽ የሚታይ እና ቀጥተኛ ጉዳት በእኔ ላይ ካላመጣ)። ምክንያቱም ከአካባቢዉ ጋር ዉልደትም ሆነ ቁርኝት የለኝም። ከዚያ አዉራጃ፤ ወንዝ እና ህዝብ ጋርም ትስስር የለኝም (የለም ባዬቹ እንዳሉት)፤ ኩታ ገጠም ብንሆንም እንኳን እኔን ከአንድ አኙአክ፤ ሶማሌ፤ ሀዲያ ወይም ከቀሩት 80 ብሄሮች ጋር የሚያደራርሰኝ ነገር የለም።”

ማንም ሰው ይህን ፅሁፍ ከመሞገቱ በፊት ፀሃፊው የረገጣቸውን ፅንፎች ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡ ማንም ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን ፖለቲከኛ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ ብሔራቸው ብቻ ነው ሊል አይችልም፡፡ በወጣ ገባነት የተሞላው የ3000 አመት ታሪካችን፤ ለመላው ጥቁር ህዝብ ያበረከትነው የነፃነት ተምሳሌት፤ ዘውዳዊና አምባገነናዊ ስርዓቶችን ለማስወገድ ያደረግነው ትግል፤ ወዘተ… የጋራ ማንነቶቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ማንነቶቻችን ከማንም በላይ የምንጠቀመው በልዩነታችን ውስጥ በአንድነት ስንኖር መሆኑን ይመክሩናል፤ የአንዳችን እድገት የሌላችንም ሃብት መሆኑን፤ የአንዳችን ቁስል የሌላችን ህመም እንደሆነ ይነግሩናል፡፡

በ1997 የምርጫ ወቅት ተቃዋሚዎች /አሁን እንዲህ እንደ አሜባ ሊበጣጠሱ/ እንደሰበኩን የምንከተለው <<ትግራይ እስክትለማ ሌላው ይድማ>> መርህ ሳይሆን ሁላችንም በጋራ እንልማ በሚል መርህ መሆኑ በተግባር የታየውም በዚህ በልዩነት ውስጥ በተመሰረተ ጠንካራ አንድነታችን የተነሳ ነው፡፡ ሻዕቢያ በሰሜን በኩል ሀገራችንን በእብሪት ሲወር የደቡቡ፤ የምዕራቡ፤ የምስራቁና የመሀል ሀገሩ ወጣቶች ወደ ሰሜን የተመምነው /ልብ በሉ፤ <የተመሙት> አላልኩም/ ጥቃቱ ኢትዮጵያችን ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ስለተረዳን ነው፡፡ ከብተና አደጋ ወጥተን በማያቋርጥ እድገት ውስጥ የገባነው በዚህ በልዩነት ውስጥ በተመሰረተ ጠንካራ አንድነታችን የተነሳ ነው፡፡ በጋራ ክንዳችን ድህነትን መደቆስ መቻላችን እንኳን የእኛን ኢትዮጵያዊነት ሊያላላ ቀርቶ ሌሎች አብረውን ቢኖሩ መልካም እንደሆነ እንዲመኙ ያስቻለ ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ እንኳን የራሷ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመገንጠል ጥያቄ ሊያነሱባት ቀርቶ የቀደሙት ንጉሶቻችን ቆራርጠው የጣሏቸው ግዛቶች ሕዝቦች ሳይቀር አብረዋት ቢሆኑ ለነሱ መልካም እንደሆነ የሚመኟት መሆኗን ካለፈው 23 አመት ተጨባጭ ልምዳችን መረዳት ያልቻለ ሰው ዋጋኩሱ ዶት ኔት ድረ ገፅ ገብቶ ፕሮፌሰር አሊ ካሊፍ ጋሊድ ከዩንቨርሳል ቲቪ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ይዘት ማንበብ ይችላል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ጋዜጠኛ የማነ ነጋሽ <ኢትዮጵያዊነት እንደእኛው አይነት የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ወገኖች ወደውና ተስማምተው የሚያስሩት ቃልኪዳን እንጂ በራሱ ማንነት አይደለም> በሚል ያወጣውን ፅሁፍ ተቃውመው በዚሁ ሰሞን ባሰፈሩት ፅሁፍ እንዲህ ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› በማለት፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹There is no identity called Ethiopian.›› ተብሎ ሊተረጎም ነው፤ እንግዲህ ይህ አወቀች፤ አወቀች ሲሏት መጽሐፉን አጠበች እንደተባለችው ሴትዮ፣ ወይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ እንትን ይለቀልቃል! የሚባል ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በትግርኛ የጻፈው ሰው የአለማወቁ አዘቅት ዓለምን በሙሉ የሚያናጋ መሆኑን አልተገነዘበም፡፡”

ለእኝህ ፕሮፌሰር ያስጨነቃቸው ኢትዮጵያዊያን ብሔረተኝነትን እንዴት እየኖሩት ነው የሚለው ሳይሆን በውጭ ሀገር የሰሙን ምን ይሉናል የሚለው ነው፡፡ አረፍተ ነገሩን ከትግርኛ ወደ አማርኛ፤ ከአማርኛ ደግሞ ወደ እንግሊዘኛ ለመተርጎም መጣራቸው ይህን ጭንቀታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም እሳቸውን ባስጨነቃቸው በዚሁ <ውጭዎቹ ምን ይላሉ?> በሚለው ጉዳይ ላይ ተንተርሶ ማስረዳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሌላ ቦታ ብሄድ <ያልበላኝን ለምን ታክልኛለህ?> እንዳይሉ ብዬ ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ከእኔ በተሻለ አለም ስለ ኢትዮጵያ ምን እንዳለና ምን እያለ እንደሆነ ለመስማት እድሜያቸው አግዟቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው እርሳቸው ኢትዮጵያ በንጉሱና በደርግ መንግስት ስትመራ ‘የበኩላቸውን ሚና’ ተጫውተዋል፡፡ ስለሆነም የማወራላቸው ስለኖሩባት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሻራቸውን ስላሳረፉባት ጭምር ነው፡፡

እኛ የምናውቀው አለም ኢትዮጵያን የድህነትና ኋላቀርነት ተምሳሌት፤ በርስ በርስ ጦርነት የምትነድ፤ ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም ያጣች፤ እጆቿ ሁልግዜ ለስንዴ ልመና የተዘረጉ አድርጎ በመገናኛ ብዙሃኑ የሳላትን ኢትዮጵያን ነው፡፡ አሁን ይሄው ሚዲያ ተመልሶ የሚነግረን በአለም ፈጣን እድገት ውስጥ ካሉ ጥቂት ሀገሮች ተርታ የተሰለፈች፤ ከራሷ አልፋ ለአለም ሰላም እጇን የዘረጋች፤ በአለም መድረክ አፍሪካን መወከል የቻለች በጥቅሉ በለውጥ ባቡር ላይ የተሳፈረች ሀገር መሆኗን ነው፡፡ ስለሆነም አለም ሲያወራው የሚያሳፍረን ፕሮፌሰሩ የኖሩበት ቁልቁል የተንደረደርንበት የታሪካችን ክፍል እንጅ በማንነታችን ኮርተን በልዩነታችን ውስጥ የመሰረትነው ጥብቅ አንድነት ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡

በርግጥ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኛ መሆን በድሮ ስርዓቶች ናፋቂዎችና የነሱ የሃሰት ጭምብል በጋረዳቸው ሰዎች ሊያሰድበን ይችላል፡፡ ግን ስድባቸው የግል ማንነታቸውን ከማጋለጥ ባለፈ ዛሬን ወደኋላ ሊመልሳት አይችልም፡፡ ሎካል ዲስክ ሲ በሚል የፌስ ቡክ ገፅ ላይ እንደሰፈረው “ከልክ ያላለፈ የብሄራዊ ማንነታችን ክብርና ፍቅር እውነተኛ ሀገራዊ ማንነት ለመገንባት ይረዳናል እንጂ ጠባብና ዘረኛ ሊያስብል አይገባም። ሀገራዊ ማንነት የምንፈጥረው ብሄራዊ ማንነታችን ለመጨፍለቅ ሳይሆን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ነው”።

የህገመንግስታችን የመጀመሪያው አንቀፅ የሚያስቀምጠውም በፍቃዳችንና በፍላጎታችን ላይ የተመሰረተ አንድነት የመፍጠር ግባችንን ነው፡፡

“እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፤ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፤ የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፤ በነፃ ፍላጎታችን ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል፡፡” ነው የሚለው፡፡

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝን የአቶ ግርማ ካሳን ፅሁፍ የመጨረሻ አንቀፅ ሳነብ ግለሰቡ ብሔርን መጥራት ነቀርሳ የሆነበት ከልቡ ሳይሆን የሆነ ሳይወድ በግድ የተጫነበትን አመለካከት ስለተሸከመ መሰለኝና አዘንኩለት፡፡ ለምን ብትሉኝ የመጨረሻዋ አንቀፅ እንዲህ ትላለችና ነው፡፡

<<ኢትዮጵያ አንድ ወጥ አይደለችም። የተለያዩ ባህሎችን፣ ቋንቋዎች፣ በአጭሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች ያሉባት አገር ናት። ቢራቢሮዎችና አበባዎች የተለያዩ ቀለማቶቻቸው ዉበታቸው እንደሆነ የኢትዮጵያም ዉበቷ ብሄረሰቦቿ ናቸው>>

አይይ ግርማ፤ የጅህን ይስጥህ እንጂ ምን እልሃለሁ፤ ይችን አንቀፅ መጀመሪያ ላይ ብታመጣት ኖሮ እኮ እኔና አንተም እንዲህ አንነዛነዝም፤ አንባቢንም አናሰለችም ነበር፡፡

በመጨረሻም ለማታውቁኝ አንባቢዎቼ አንድ ነገር ልበል፡፡ ብሄሬ አማራ፤ ዜግነቴ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

********

Kebede Kassa

more recommended stories