መለስ ያተረፋት ሀገር ላይ ተቀምጦ መለስን ማማት

(ኖላዊ መላከድንግል)

—-1—-

መለስ ዜናዊ አስረስ እየተዘከረ ነዉ፤ በሙት አመቱ፤፤ ………በፌስ ቡክ ላይ እና በየሻይቤቱም ስሙን እያነሳን ስንጥል፤ ግማሾቹ ወደ ገነት ደጃፍ ነዉ ያንደረደረን ስንል የቀረነዉ ደሞ አገር የበታተነ ፤ታሪክ ያንኳሰሰ አምባገነን ነዉ በሚሉ እዉቀት አጠር ጽንፎች ላይ ቆመን እኛም አመት ሞላን።

ከዚህ ሁሉ አድካሚ ንትርክ በኋላ እንኳን መለስ የተረከባት አገር ምን ነበረች፣ ምን አልምቶ ምን አጠፋ፣ የስራዉ ፍሬ እና አደጋዉስ ምንድነዉ፣ ኢህአዴግስ አንድ ሀሙስ ቀረዉ እየተባለና መሪዉን አጥቶ እንዴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ቻለ፣ ጥንካሬዉ ያለዉ ይህ አድር ባይ እና ነዉጠኛ ዲያሲፖራ ፖለቲከኛ እንደሚለዉ ጦር ሰራዊቱ ላይ ነዉ? የሚሉ ለድምዳምያችን ወሳኝ የሆኑ ነጥቦች አሁንም ልክ እንደባለፈዉ አመት በክርክሩ የሉም። እነደዉ ዝም ብሎ ስሜት ይዞ መንገላታት ነዉ…..! መለስን እንደ ሰይጣን ከሚያወግዙት ዉስጥ ብዙሀኑ አንድነትን አዳሟል፣ አገር የሚገነጥል ህገ መንግስት አጽድቋል እና ዴሞክራሲ የሌለበት ስርአት ገንብቷል የሚሉ ዋና መከራከሪያዎችን የሚያቀርቡ ናቸዉ። እነዚህን ተደጋጋሚ በመለስ ላይ የሚቀርቡ ሀዘኖችን ወደኋላ እንመልከት!Ethiopian PM Meles Zenawi

ለነገሩ መጥላትም ማምለክም ነዉር የለዉም፤ ሰዋዊ ባህሪ ነዉ። ችግሩ ያለዉ ለአገር ያለንን እይታ እና ተግባር በሚወስን ነገር ላይ ጠንቃቃ አመክንዮ የጎደለዉ ድምዳሜ አደገኛ መሆኑ ነዉ። በ1983 የነበረችዉ ኢትዮጵያ የመበተን አደጋ በግልጽ የተጋረጠባት፣ በርካታ የታጠቁ እና የተከፉ ቡድኖች በብሄር ተደራጅተዉ የነበሩባት እና ኢኮኖሚ ያልነበራት ኢትዮጵያ እንደነበረች ረስቶ ታላቋን አገር አዳከመ ክርክር የትም አያደርስም።

የኦነግ እና ኦብነግ ነዉጥ ብቻዉን ይቺን ሀገር እንደ ሀገር መቀጠሏን የማይሆን ነገር ሊያረጉት ይችል ነበር። ያንን አስቸጋሪ የፖለቲካ ድሪቶ በጥንቃቄ ይዞ ወደመረጋጋት ያሻገራት መለስ ነዉ። በሰኔ 1983 መንግስት ለመመስረት ጥሪ ሲደረግ የቀረቡት ቡድኖች በሙሉ ( ዛሬ እንደ አመቺነቱ የአንድነት ካባ እየደረቡ የሚቀርቡትን ጨምሮ) በብሄር የተደራጁ ነበሩ። አንድም እንኳን ከፌደራል ስርአት ዉጪ በሆነ ቅርጽ እንተዳደር የሚል ሃሳብ ይዞ የቀረበ አልነበረም። እናም የፌደራል ስርአቱን ሊበራል ከሆነ ህገ መንግስት ( በተነፃፃሪ ከግራ ዘምም ፓርቲ የማይጠበቁ በርካታ መብቶች የሚሰጥ) ጋር አጣምሮ ሁሉንም አሳታፊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን ያረጋጋ መንግስት መርቷል።

ያኔ መለስ በጥንቃቄ ያተረፋት አገር ላይ አሁን ተቀምጦ ታሪክ አበላሸ አገሬን በተናት ምናምን…..ምንም መሰረት የሌለዉ ነዉ። ያስገምታል!

ኢትዮጵያ ነበረችበትን የመከፋት እና የጭቆና አገዛዝ ዜጎች ልክ ነዉ ባሉት መንገድ ተደራጅተዉ ታግለዋል! ያን ደሞ ማንም ለምን እንዲህ አሰባችሁ፤ ወይም ተደራጃችሁ ሊላቸዉ እይችልም። መፍትሄዉ በመግባባት፤ በእኩልነት፤ እና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እየተፈጠረ እንዲመጣ የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱ ላይ ነዉ። ለዘመናት የቆዩ መቋሰሎችን ለመፍታትም ብቸኛዉ መንገድ ይሄዉ ነዉ። ይህን በማድረጉ ሂደት ጉልህ ጥፋቶች በየቀኑ ቢኖሩም በመሰረታዊ ሃሳብ፤ በተቋማት፤ በህግ እና በስተዳደራዊ መዋቅር ደረጃ ግን አካሄዱ ትክክለኛ ሆኖ ቆይቷል፣ አሁንም ነዉ! ወደተሻለ ነገር መቀየር እስከሚኖርበት እና ለዉጡም ህዛባዊ ድጋፍ ማግኘት እስከሚችልበት ግዜ ድረስ።

አንቀፅ 39ም ቢሆን እገነጠላለሁ የሚል ቡድን የሚኖረዉን ተቀባይነት የሚቀንስ እንጂ የሚጨምር እና ልገንጠል የሚል ሁሉ ተሰልፎ የሚመጣበትን ሁኔታ አልፈጠረበት። ዋናዉ ችግር ከድህነት መላቀቅ፣ መልካም አስተዳደር ( ዴሞክራሲ ከባህል ጋር የሚዳብር ነዉ፣ advocacy እና ቁርጠኝነት አስፈላጊ ቢሆኑም ወሳኝ አይደሉም)፣ የፍትህ፣ እና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማሟላት አስተዳደራዊ ብቃት እና የለዉጥ ዝግጁነት ነዉ። ይህ አመለካከት ደሞ ከነችግሮቹም ቢሆን የብዙሃኑ ኢትዮጵያዊን ድጋፍ አለዉ! ለዚህ ነዉ ኢሕአዴግ እየመራ የሚቀጥለዉ። ለተወሰነዉ ባይጥምም!

ስለዚህ መለስ በመሰረታዊ ደረጃ የሰራቸዉ ነገሮች የሚታዩ ሲሆኑ የቀየራቸዉ ደሞ አገሪቱን ለማራመድ በግድ መቀየር የነበረባቸዉ ናቸዉ። የማይካዱ በርካታ ስህተቶች በአስተሳሰብ፣ በፖሊሲ እና በአፈፃፀም በየቀኑ አሉ። እነሱን መለየት እና ማስተካል ነዉ እንጂ በመለስ ላይ መከራከር ብዙ እርባና የለዉም። የሰራዉን ሰርቶ አልፏል! ታሪክ ይፈርደዋል! ይልቅስ ተቃዋሚ የምትባሉት ምን ተሰርቷል፣ ለምን ተሰራ፣ለምን እና እንዴት ደሞ እንቀይረዉ የሚለዉ ገብቷችሁ ወደ ጨዋታዉ ብትገቡ ጥሩ ነዉ። ያልተረዳችሁትን ልትታገሉትም ልትቀይሩትም አትችሉም። መለስ የቻለዉን አርጓል! የቀረዉ የኛ ነዉ!….

—-2—-

ከዚህ በላይ ያለውን ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት በፌስቡክ ላይ ካተምኩት በኋላ በርከት ያሉ አስተያቶች እና ስድቦች ደርሰዉኛል። የኔ ጽሑፍ ዋና ማጠንጠኛ የነበሩት <መለስ ኢትዮጽያን የተረከበበት ሁኔታ ምን ነበር> እንዲሁም <በፌደራል መዋቅር እና በርካታ መብቶችን በሚሰጥና በሚያስጠብቅ ህገመንግስት የአገሪቱን አንድነት ጠብቆ አሻግሯል> የሚሉ ነጥቦች ነበሩ፡፡ ሆኖም የተለያዩ ጥያቄዎችን ላነሱ ሰዎች ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ የሚከተለውን አክያለሁ፡፡

የእኔ ጭብጥ መለስ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ የታዮ በርካታ ችግሮች የሉም የሚል አይደለም። ሊሆንም አይችልም! የመሰረታዊ መዋቅሩ ዉጤት የሆኑ እና ሌሎችም ችግሮችም ከመጀመሪያዉ ጀምሮ አሉት። ኤርትራዉያን ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበራቸዉ ያልተገባ ሚና፤ ፌደራሊዝም ቅራኔን በሚፈጥሩ እና ህገ መንግስታዊ መብቶችን በሚጥሱ ሁኔታዎች አሰራር ላይ መዋሉ፤ ተደራሽ ያልሆነ እና በሙስና የተጨማለቀ አስተዳደር ወዘተ ወዘተ….አሉ! እኔ ያልኩት እነዚህ ሁሉ ከባድ ችግሮች አገሪቱ ከተሰራች በኋላ የምንነጋገርባቸዉ ናቸዉ፤ ምክንያቱም መለስ የተረከባት አገር ከድህነቷ በላይ በአደገኛ ሁኔታ ላይ በታጠቁ ሀይሎች ይዞታ ስር የነበረች ሰለነበረች አንድነቷን ለመጠበቅ ያደረገዉ ነገር ልክ እና በወቅቱ አማራጭ ያልነበረዉ ነዉ የሚል ነዉ። አለቀ! ይህ ቀላል ሎጂክ መሰለኝ።

የለም…..እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ከተግባራዊነት አንጻር የተሻለ ነበር፣ ይቻልም ነበር በሉኝና እንቀጥል። በመሰረቱ….ሁሉንም ነገር ወደኋላ ተመልሶ ማየት ቀላል ነዉ! እያንዳንዱ የተደረገ ነገርም አሁን ላይ ሲታይ በተሻለ መንገድ ሊደረግ ይችል ነበር የሚለዉ ነገር ደስ ቢልም ከአባባል ባለፈ ተግባራዊ አይመስለኝም! Hindsight is not necessarily the best guide to understanding what really happened. The past is often as distorted by hindsight as it is clarified by it የሚለዉ አባባል ምናልባት እዚህ ጋር ይጠቅመን ይሆናል።

የትኛዉም ጠንቃቃ መሪ ከሁኔታዎች ጋር ሲጋፈጥ እና ጊዜ በማይሰጥ ዉስብስብ እና የተጠላለፈ ችግር ዉስጥ ሲገባ ነገ ከነገ ወዲያ አንዳንዶችን ሊያስከፋ የሚችል ቢሆንም እንኳን አገሪቷን ማስቀጠል የመጀመሪያ ስራዉ ነዉ የሚሆነዉ። ይሄ ለሁሉም ይሰራል! ሌላ መሪ በዚያ ሁኔታ እራሱን አግኝቶ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ የሚያሰደስቱ ዉሳኔዎች ይኖሩታል ካላችሁኝ እንግዲህ ዉይይቱ አስቸጋሪ ይሆናል።

ስለዴሞክራሲ የተነሳዉ ደሞ መነሻዉን ካለመረዳት ይመስለኛል! ግንባታዉንም ሆነ ዉድቀቱን በተመለከተ አንዱን ወገን ተጠያቂ የሚያረግ ወቀሳ ፈፅሞ አልቀበለዉም! ስለየትኛዉ ሰላማዊ ተቃዋሚ ነዉ የምናወራዉ? የምርጫዉ ዉጤት እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር 10,000 ሰዉ ይዘን ቤተመንግስት እንገባለን የሚሉ መሪዎች አልነበሩም እንዴ እንቅስቃሴዉን ይመሩ የነበሩት? የህግ እና የፖለቲካ እምነት ሊፈጥር የሚችል አካሄድን በግልጽና እና ሳያወላዉል የተጓዘ የትኛዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ነዉ ባለፉት አመታት የነበረዉ? የመለስ መንግስት ተቃዋሚን በበጎ ያይ ነበር የሚል የዋህነት ባይኖረኝም አብዛኛዉ ተቃዋሚ እንደ አመቺነቱ ሰላማዊም አመጸኛም እየሆነ የኖረ እና አሁንም ከዚያ ወጥመድ ያልወጣ ነዉ። በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ከዚህ ንጹህ ናቸዉ።

የዴሞክራሲ ሂደት የኢኮኖሚ አቅሙ የዳበረ እንዲሁም ከሰላም ፤ ከመረጋጋት እና ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ትርፍ የሚያገኝ (እነዚህ ከሌሉ ብዙ ጥቅም የሚያጣ) ህዝብ ሲፈጠር ይህ ህዝብም ስለ መብት ያለዉን ግንዛቤ ቀስ በቀስ ትእግስት፣ ድርድር እና ግዴታ ከሚባሉ እሴቶች ጋር ማዋሀድ ሲችል የሚመጣ አመለካከት እና አኗኗር ነዉ። እዛ ላይ ያልደረሰ ማህበረሰብ ደሞ ይህን በአግባቡ መተግበር ያልቻለ መንግስት እና ተቃዋሚ ባይኖሩት ብዙ የሚገርም እይደለም። እንዲያዉም በመጀመሪያዎቹ 15 አመታት ጥሩ የሚባል እድገት ነበረዉ ብዬ አስባለሁ። ከ97 በኋላ ያለዉ መቀጨጭ ግን የሚያሳዝን እና የሚያሸማቅቅ ነዉ፤ የጸረ-ሽብር ህጉም አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ባይኖረዉም ህገ መንግስቱን የሚሸረሽር አደጋ ግን አለዉ። ባጠቃላይ ጉድለቱ የሚያስቆጭ ቢሆንም (ዴሞክራሲ በprinciple ላይ መቆም አለበት ስለሚባል) ዴሞክራሲያዊ በሮች አገርን ወደብጥብጥ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ዉስጥ ሊከቱ የሚችሉ አደጋዎችን እየታገሱ ስለማይቀጥሉ በሩ እየጠበበ መምጣቱ የሂደቱ ልምድ በሌላቸዉ አገሮች ዉስጥ ተፈጥሮአዊ ይመስለኛል!

ነገሩን ለመጠቅለል ….. የአንድ መሪ ተግባር ምዘናዉ በዙሪያዉ ካሉት ብቻ ተወዳድሮ አይደለም። ከተነሳበት ሁኔታም ጭምር ነዉ! መጀመሪያ ከየት ተነሳን የሚለዉን እንይና ኬንያና ጋና የት ሄዱ እና ለምን በለጡን በሚለዉ ላይ እየተወቃቀስን እናወራለን! ይህ ሁለተኛ ደረጃ ጨዋታ ነዉ። ከሌሎች ጋር ያለንን ሁኔታ ለማወዳደር በመጀመሪያ ሁላችንም ቤት የምንለዉ ነገር መኖር ነበረበት፤ መለስ ይህንን ቅደም ተከተል ያለዉ የቤት ስራ ነዉ የሰራዉ የሚል ነዉ የኔ ጨዋታ! ስለዚህ ንጽጽሩ ከታች ጀምሮ ወደጎን ቢሄድ ልክ ይሆናል ለማለት ነዉ።

ሰዎች ላልሰሩት ነገር የሚወቀሱ ከሆነ ለሰሩት ቢመሰገኑ ለህዝብም ጥሩ ማስተማሪያ ይሆናል እንጂ ችግሩ አይታየኝም። ይህን እንዳናደርግ እንቅፋት የሆነብን ደሞ ፅንፈኝነት ነዉ፤ በሁሉም በኩል!

*************

* The author, Nolawi Melakedingel, is a consultant on media and political affairs and a guest writer in this blog. He can be reached at [email protected]

Guest Author

more recommended stories