ለበእውቀቱ ስዩም:-እውን የድሮው ኢትዮጵያዊነት የመዋጮ ነበርን?

(ጆሲ ሮማናት)

በእውቀቱ ስዩም ኢትዮጵያ የብሄርተኝነት ሃይማኖት ክፉኛ ያሰጋታል ይለናል፡፡

ሰሞኑን ጃዋር መሃመድንና ሌሎች “ብሄርተኛ” ብሎ የፈረጃቸውን መልሶ ለመሞገት “የዘመኑ መንፈስ” ብሎ በጻፈው ጽሁፍ የዘመኑ “ታሪክ ከላሾች” እንደሚሉት ኣሁን የምናያት ኢትዮጵያ “በኣማራ ባህላዊ ስርጭት እና በኣማራ ፖለቲካ የተገነባች” ሳትሆን የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ግንኙነት ስብጥር ነች ይከራከራል ፡፡ የኢትዮጵያ ኣገራዊ ማንነት መገለጫ የኣማራ ባህላዊ ማንነት ሳይሆን ኦሮሞም ኣማራም ትግራዩም እየተዋጉም ኣብረው እየሰሩም ባህል እየተወራረሱ የፈጠሩት ነገር ነው በማለት ኣንዳንድ ጥቃቅን የቃላት መወራረስን እንደ ምሳሌ ኣድርጎ ኣቅርቧል፡፡

ውድ ወንድማችን በእውቀቱ፣ ኣይናቹሁን ጨፍኑና እመኑኝ ካላለን በስተቀር የኢትዮጵያ የባህል መለዮ የኣማራ-ትግራይ ባህል እሴቶችን ብቻ የያዘ እንደነበር ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የኦሮሞው የሲዳማው የጋምቤላው ኣሊያም የሶማሌው ባህል እንደ ኣገራዊ ባህል የተወሰደበት ጊዜ ኣልነበረም፡፡ ለመቶ ኣመት ያህል ተሰርቶበት ያጨነገፈው ፕሮጀክት ኣገሪቷን በኣንድ ቋንቋ ኣንድ ሃይማኖትና ባህል ለመቅረጽ ነበር – ያ ባህል ደግሞ በእውቀቱ እንደሚለን “የመዋጮ ባህል” ሳይሆን የኣማራ-ትግራይ ባህል ነበር፡፡ ሌሎቹ ብሄረሰቦች በፖለቲካም በባህልም የጎላ ተሳትፎ ኣልነበራቸዉም – ወደዛ ራሳቸውን ካልጠቀለሉ በስተቀር፡፡

በእውቀቱ፡- በጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራ “ተክለኢየሱስ” የሚል የክርስትና ልጅ ተሰጥቶት በእንክብካቤ “በጠጅና በስጋ” እንዳደገና በመጨረሻም እስከ የንጉሱ “ጸሃፌ ትእዛዝ” ለመሆን እንደበቃ ይነግረናል፡፡ በተመሳሳይም የሸዋው ምርኮኛ ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ ኣድጎ “ሃብተጊዮርጊስ” በሚል ስመ-ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ሚኒስትር እስከ መሆን ደርሷል ይለናል፡፡

ታዲያ ለባህልና ማንነት ኣፈና ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ምን ሊኖር ይችላል?

በእውቀቱ ለማሳየት ከሞከረው በተቃራኒ ነገሮ ዋቅጅራ እና ቆሴ ዲነግዴ የባህል መወራረስ ኣብነት ሳይሆኑ የባህልና የማንነት ጭቆናው ሰለባዎችና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ነገሮ ዋቅጅራ በዋቅጅራነቱ፣ ዲነግዴም በዲነግዴነቱ ማስተናገድ የሚችል/ፈቃደኛ የሆነ የፖለቲካ ባህል ኣልነበረም፡፡ በፖለቲካው መንደር ተቀባይነት ለማግኘትና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመሳተፍ (ጸሃፌ ትእዛዝና የጦር መሪ ለመሆን) ስማቸውን ወደ “ተክለኢየሱስ” እና “ሃብተጊዮርጊስ” መቀየር ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ምን ሊመጣ ነው ?

ውድ በእውቀቱ፡- በብዙ ኣገሮች ላይ እንደሆነው ሁሉ ወደድንም ጠላንም በውዴታም ሆነ በግዴታም ኣንድ ኣገር ሆነናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ከመበታተንና ከመለያየት ይልቅ ኣብረው ተከባብረው ቢኖሩ ለሁሉም የተሻለ ነው፡፡ ከመገንጠል የሚጠቀም ማንም ወገን ኣይኖርም የሚለው ያስማማናል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን የድሮውን ታሪክና ጭቆና በመካድ ሳይሆን ያለፈውን ጥፋት እንደ ጥፋት ኣምነን ኣዲስና ሁሉም ሊኮራባትና የኔ ናት ሊላት የሚገባ ኢትዮጵያ በመፍጠር ብቻ ነው፡፡

‹‹ኣልተጨቆናችሁም ነበር›› ብሎ ማለት በነሱ ቦታ ሆኖ ችግሩ ካለማየት የመጣ ችግር ነው፡፡ ኣዎ ኢትዮጵያ ኣንድነቷን ጠብቃ እንድትቆይ የድሮ መገለጫዋ ሳይሆን ኣዲስና ኣካታች የሆነ መገለጫ ያስፈልጋታል፡፡ የድሮው መገለጫ ባህሏ “በመዋጮ” የተገኘ ሳይሆን ከተወሰነ ኣካባቢ ብቻ የተቀዳ ነበር፡፡

*************
The author Jossy Romanat in a co-blogger in this blog. He is a social scientist residing in Canada and can be reached at [email protected].

Jossy Romanat

more recommended stories