ኢሳትን ተው በሉት! (ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን)

Highlight: ኢሳት (ESAT) እንደተቋምነቱ ዘገባውን ማስተላለፉ “ጤና-ቢስነቱ”ን የሚያሳይ ነው የሚመስለኝ፡፡ እኔ የማውቀው የኦሮሞ ህዝብ “ጉዲፈቻ” የሚባል እጅግ የረዥም ዘመን አዙሪ ባህል እንዳለው ነው፡፡ እንጂ ህፃናትን ለገደለ የነበዘ ወታደር “ሲያመልክ” አይደለም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብም ቢሆን ያኛው ብሄር ነፍሶ ገዳይ ያመልካል የሚል ዕምነት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡

——

(ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን)

እውነት ቤት ስትሰራ
ውሸት ላግዝ ካለች
ጭቃ ከረገጠች
ምስማር ካቀበለች
ቤቱም አልተሰራ
ዕውነትም አልኖረች (ጌትነት እንየው)

ከ150 ዓመት በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ዜና መዋዕል ዘጋቢ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አለቃ ዘነብ “መፅሐፈ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” በተሰኘው ድርሰታቸው እንዲህ የሚል ድንቅ አባባል ከትበው ነበር፡-

“…አስተካክሎ ከማይናገር መልዕክተኛ የማለዳ ወፍ ትሻላለች፤ ምነው ቢሉ መንጋቱን በትክክል ትናገራለች፡፡”

ይህ የአለቃ ዘነብ አባባል ሁለት ነገሮችን አጉልቶ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ መልዕክት ወይም መልዕክተኛውን፡፡ በሌላ አነጋገር አስተካክሎ የመናገርን እና ያለመናገርን ጥቅም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የእኔም የዛሬ ፅሁፍ ዋንኛ ጉዳይ ይኸው እውነት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ዛሬ በማነሳው ፈትለ-ነገር (theme) ብዕሬ የሚያነጣጥረው ኢሳት (ESAT) በተባለው የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ላይ ነው፡፡ ለጥቂት ወራት ያህል፤ ራሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ልሳን ነኝ ብሎ በሚመፃደቀው ኢሳት ላይ ምንም ዓይነት ሃሳብ ላለመሰንዘር

ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ለምን? በዚሁ በአውራምባ ታይምስ ድረ-ገፅ ለአንባቢያን ባቀረብኳቸው ፅሁፎች የተነሳ የተናደዱ ጥቂት የኢሳት አድናቂዎች በፌስቡክ የግል መልፅክት ሳጥኔ ብቅ እያሉ ነዘነዙኝ፡፡ ጥቂቶች በዛቻ፣ ጥቂቶች በ”ከዳተኝነት” እና በ“ወያኔ አዳሪነት” ሊፈርጁኝ ሞከሩ፡፡ ጥቂቶች “ኢሳት የፃድቃን ማህበር ስላልሆነ ቢሳሳትም እንድተወው” መከሩኝ፡፡ እኔም በዛወርቅ አስፋው የዘፈነችውን “የማነሽ ይሉኛል የማን ልበላቸው” የሚለውን (የአለምፀሐይ ወዳጆ ግጥም) እያንጎራጎርኩ፣ ኢሳት ቢሳሳትም ምንም ላለመናገር ራሴን አቀብኩ፡፡ ዛሬ ግን…

ዛሬ ግን ትዕግስቴ አለቀ፡፡ ተሟጠጠ፡፡ እናም ኢሣት (ESAT) ራሱ የማነው? ለማለት ቆረጥኩ፡፡ “ኢሳትን ተው በሉት!” ለማለት ብዕሬን አነሳሁ፡፡ ዘመድ፣ ወገን፣ ዘር፣ ብሔር፣ ደጋፊ፣ ሀገር ካለው ይመከራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ “ኢሳትን (ESAT) ተዉ በሉት!”

ሁለት

“ኢሳት (ESAT)ን ተዉ በሉት!” ለማለት ብዕሬን ያነሳሁት ካለበቂ ምክንያት አይደለም፡፡ በቂ፣ ከበቂ በላይም የሆነ አስረጅ ይዤ ነው፡፡ ሁሉንም አስረጅዎቼን ልዘርዝር ካልኩኝ ጊዜም ቦታም አይበቃኝም፡፡ እናም አንድ ጉዳይ ብቻ ልጥቅስ፡፡ በባህርዳር በባህርዳር ከተማ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ፡፡

ኢሳት (ESAT) ይህንን አሳዛኝ ዜና እንዴት ዘገበው? ለምን ዘገበው? ዓላማው ምንድነው? ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ ሰው፣ ጤናማ መልስ የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ነኝ የሚለው ኢሳት (ESAT)ን “ጤነኝነት” ትጠራጠራላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡

ለማንኛውም ኢሳት (ESAT) ግንቦት አምስት ቀን 2005 ዓም ስለባህርዳሩ አሰቃቂ ግድያ የዘገበውን በከፊል እንመልከት፡፡ እነሆ፡-

“…እሁድ ግንቦት 4 ቀን 2005 ዓም ከምሽቲ 2 ሰዓት ከ45 ደቂታ ላይ የሁለት ዓመት ህፃንን ጨምሮ 17 ሰዎችን በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 11 ወይም በተለምዶ አባይ ማዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በግፍ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ አባል ማንነት እና የገደለበትን ምክንያት በውል አለመታወቁን ተከትሎ የተለያዩ መላምቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

ወታደሩ ድርጊቱን የፈፀመው አንድ ያፈቀራት ወጣት ከእሱ ጋር ለመቀጠል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው የሚል አስተያየቶች ቢሰሙም በሌላ በኩል ደግሞ ግለሰቡ የሌላ ብሔር ተወላጅ በመሆኑ ጥላቻውን ለመግለፅ በሚል የፈፀመው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡…”

ይህንን የኢሳት (ESAT) ሙሉ ዘገባ ማረጋገጥ የፈለገ ሰው ድረ-ገፁን ገለጥ አርጎ መቃኘት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ የሆነ ሆኖ ከላይ የቀነጨብነውን ጤና-አልባ የኢሳትን (ESAT) ዘገባ ብቻ ተመርኩዘን “ትንንሽ” ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለመሆኑ ይህንን የኢሳት (ESAT) ዘገባ የዘገበው ሰው ጋዜጠኛ ነው? ከሆነ አፍራለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ አራት ነጥብ የተባለ ሥርዓተ ነጥብ ለማግኘት “ከባሌ እስከ ቦሌ” የሚያደክመን ምን አይነት ጋዜጠኛ ቢሆን ነው?

የዜና የመጀመሪያ አንቀፅ በመላምት መሰረት ላይ የሚመሰረተው ከመቼ ጀምሮ ነው? ቀድሞ ነገር “መላ ምት” ብሎ ነገር ምን አመጣው? ለምን ዓላማ ነው “መላምት” ያስፈልገው?… ወዘተ፡፡ እንደ እኔ፣ እንደኔ የኢሳት (ESAT)ን ጤና አልባነት ለመረዳት እነዚህን ተራ ጥያቄዎች ብቻ ማንሳት ብቻ በቂ ነው፡፡ ጠንከር ጠንከር የሚል ጥያቄ ካነሳንማ ጉዳዩ ሌላ ነው የሚሆነው፡፡ ብቻ በ”መላ” የሚፃፍም፣ የሚነገርም ዜና የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡

ሦስት

እኔ፤ ኢሳት (ESAT) በመረጃ ዕጦት ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል የተመሰረተ ተቋም መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ እንጂ ሌላ “የመናጫ” ምንጭ እንዲሆን አይመስለኝም፡፡ ከዘር እና ከዘረኝነት ለላቀ ከፍ ላለ ዓላማ፣ ለሐገርና ለሕዝብ ጥቅም የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ነበር የሚገባኝ፡፡ (ከላይ የጠቀስነውን የኢሳትን ዘገባ 2ኛ አንቀፅ ልብ ብለው ያንብቡ) ሆኖም ለሃገር ጥቅም የሚተጋ ተቋም ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ኢሳት (ESAT) “ትሻል ቀርቶ ትብስ” እንዲሉ ነው የሆነብኝ፡፡ ያሳዝናል!! ያሳፍራል!!

ይህ የኢሳት ዜና ምን ፈጠረ? ነው ዋናው ጥያቄው፡፡ እጅግ ልብ የሚያደማውን፣ የሕፃን ልጅን ህይወት ሳይቀር የቀጠፈውንና ለአፍታ እንኳ ሲያስቡት የሚዘገንነውን ግድያ ዘንግተን፣ “በዘር ምርመራ” ላይ እንድናነጣጥር፣ ከሰብዓዊነት እሳቤ ርቀን በዘር ፖለቲካ እንድንናቆር ነው ያደረገው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ በግድያው ማግስት በየማህበራዊ ድረ-ገፁ የተሰነዘሩ ሃሳቦችን ማየት ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ ቁርቋሶ መነሻ ኢሳት (ESAT) መሆኑ ነው የሚያሳዝነው፡፡ በዚህ የኢሳት (ESAT) ዜና የተነሳ በተነሳው ቁርቋሶ ያዘኑ እና የተናደዱ ዜጎች ብዙ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ Soli የተባለች ትንታግ ፀሐፊ ኢሣት ከላይ በጠቀስነው መልኩ ወሬውን ባራገበው ዕለት አመሻሽ በፌስቡክ ገጿ ላይ የፃፈችውን ለአብነት መጥቀስ ግድ ነው፡፡ እነሆ፡-

“… የባህርዳሩ ግድያ ልብ ይነካል፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይስጥ፡፡ እንዲህ ዓይነት ያልታሰበ ክፋት ይመጣል ብለው መች አሰቡ፡፡ ከግድያው በላይ ፖለቲካው ላሳሰባቸውም ነፍስ ይማር፡፡ ይህ ፌስ ቡክ ላይ ያየሁት ፖለቲካ፣ ልባችንን አጥተን በዘር ፖለቲካ ተጠልፈን ልንቀር እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡

ገዳዩ የትግራይ ብሔር ተወላጅ እንዲሆን የተመኙና የፃፉ እና ጉዳዩን ወደ ዘር ፖለቲካ የሳቡትን ሳስብ አፈርኩ፡፡ ገዳዩን በግልፅ ለማስቀመጥ ያህል ውስጡ ምንም ፖለቲካ የሌለው አንድ የዞረበት ግለሰብ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ….ቀኑን ሙሉ ሲደረግ የዋለው የብሔር ማጣሪያ ግን ወይ የእኛ አገር ብሎ አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ አንዳንድ ቀን እንኳ ብሔሩን ትተነው እንደሰው እናስብ እስቲ፡፡”

በእርግጥም የቴሌቪዥን፣ የሬድዮ፣ የድረ-ገፅና የሌሎችም መገናኛ ዘዴዎች ባለቤት የሆነው “ትልቁ ”ኢሳት (ESAT) የባህርዳሩን ግድያ ከብሔር ጋር ለማጣበቅ መሞከሩ ያሳዝናል፡፡ “ትልቁ” ተቋም “የትንሽ ትንሽ” ሲሆን ማየት በእርግጥም ያሳፍራል፡፡

አራት

“እውነት ቤት ስትሰራ
ውሸት ላግዝ ካለች
ጭቃ ከረገጠች
ምስማር ካቀበለች
ቤቱም አልተሰራ
ዕውነትም አልኖረች…”

የሚለውን የጌትነት ግጥም ለፅሁፌ መንደርደሪያነት የተጠቀምኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ አበው እና እመው ነገሮች ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲሆንባቸው “የባሰ አታምጣ” የሚሉት ለካ፤ ወደው አይደለም፡፡

ኢሳት ESAT ግን በባህርዳሩ ግድያ ዙሪያ ከቀደመው ዘገባ የባሰ “ደንባራ” ዘገባ ከማቅረብ አልተቆጠበም፡፡ ይህንን ዘገባ ያቀረበው ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓም ነው፡፡ “በባህር ዳር የተፈፀመው እንቆቅልሽ እስካሁን አልተፈታም” በሚል ርዕስ ካቀረበው ዘገባ አሁንም ጥቂት እንቀንጭብ፡፡ እነሆ፡-

“በባህር ዳር 17 ሰዎችን በጥይት አርከፍክፎ በግፍ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ አባል ፍቃዱ ናሻ ጋር በተያያዘ ግድያው ሲፈፀም በዝምታ ተመልክታችኋል በሚል 10 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ታስረዋል፡፡ የገዳዩ የቀድሞ ፍቅረኛም ድርጊቱ ከተፈፀመበት ቀን አንስቶ በህግ ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ ታውቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ ትላንት የተጎጂ ቤተሰቦችን አነጋግረዋል፡፡

የተጎጂ ቤተሰቦች ለጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ ‹ገዳዩ ወታደር የተቀበረበት ቦታ ይታወቅልን፤ አለበለዚያ ለኦሮሚያ ክልል ተላልፎ ከተሰጠ አማራን የገደለ እየተባለ ግለሰቡ እንዲመለክ ይሆናል› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ገዳዩ የተቀበረበትን ቦታ መንግስት ይፋ ለማድረግ አልፈለገም፡፡…”

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ዘገባ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አሸማቃቂ ነው የሆነብኝ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ዜናውን የዘገበውን ሰው ጤነኝነት ነው የተጠራጠርኩት፡፡ ዜግነቱን ጭምር፡፡ እውነት ይኼን ዘገባ የፃፈው ወይም የዘገበው ሰው ኢትዮጵያዊ ነው? ከሆነ የኢትዮጵያዊ ሕዝብ ባሕል፣ ዕምነት፣ ስነልቦና ወዘተእንዴት ጠፋው? ወይስ ከሃገር መውጣት እነዚህን የኢትዮጵያ ህዝብ ነባራዊ ማንነቶችንም ከህሊና ያወጣል?

የኢዮጵያዊነት ሥነ ልቦና የትም ሆነ የት የሚዘነጋና የሚረሳ አይመስለኝም፡፡ እንደዛ ከሆነ የትኛው ብሔር ነው አንድን ጨካኝ፣ ህሊና ቢስ እና አረመኔ ነፍሰ ገዳይን የሚያመልከው? ካለምንም ርህርራሄና ይህ ነው የሚባል ዓለማ የሌለውን ነፍሰ ገዳይ የማምለክ ልማድ በምድረ ኢትዮጵያ የታየው መቼ ነው? ወዘተ እንዲህ ዓይነቱን ዘገባ መፃፍ በራሱ የጤና አይደለም፡፡ ኢሳት (ESAT) እንደተቋምነቱ ዘገባውን ማስተላለፉ “ጤና-ቢስነቱ”ን የሚያሳይ ነው የሚመስለኝ፡፡

እኔ የማውቀው የኦሮሞ ህዝብ “ጉዲፈቻ” የሚባል እጅግ የረዥም ዘመን አዙሪ ባህል እንዳለው ነው፡፡ እንጂ ህፃናትን ለገደለ የነበዘ ወታደር “ሲያመልክ” አይደለም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብም ቢሆን ያኛው ብሄር ነፍሶ ገዳይ ያመልካል የሚል ዕምነት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡

የባህርዳሩ ተጠቂ ቤተሰቦችም ጥያቄውን በዚህ መልኩ አላነሱም፡፡ ከዳይሪክተር ጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ (ወርቅነህ ገበየሁ የጄኔራልነት ማዕረግ እንደሌላቸው ኢሳት ልብ ይበል) ጋር በአካል ተገኛኝተው የተወያዩ በግል “የማውቃቸው” ሰዎች በስልክ እንደነገሩኝ የተጎጂ ቤተሰቦች “ያኛው ብሄር ነፍሰገዳይን ያመልካል” የሚል ቃል አልወጣቸውም፡፡

ኢሳት በ“መላ” መስራት አለበት እንዴ? ከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት “መላ” የሚለውን ቃል “ባዶ የነበረውን በአንድ ነገር መላ፣ አብዝቶ ጨመረ” ሲል ነው ፍቺ የሚሰጠውን፡፡ ልብ በሉ ባዶ የነበረውን ሞላ ነው የሚለው ትርጉሙ፡፡ በጎደለ ሞላ እንኳ አይደለም፡፡ ኢሳት እንዲህ የሌለውን እየሞላ ወሬ የሢያናፍሰው ለምን ዓላማ ነው?

ደግሞስ የዚያ ነፍሰ ጨካኝ ነፍሰገዳይ አስከሬን የሚሰጠው (ከተሰጠ) ለኦሮሚያ ክልል ነው እንዴ? ለቤተሰቦቹ እንጂ፡፡፡ ኧረ ከመቼ ነው የሞተ ሰው አስከሬን ለክልል የሚሰጠው? የሞተ ሰው ሁሉ ሲቀበር “የክልሉ” ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ነው እንዴ? ወይስ ተራ ነፍሰ-ገዳይ በኦሮሚያ “ይመለካል” ያለው ማነው? ሌላው ቢቀር ይህን ዜና የሚያነቡ እና የሚሰሙ የብሔሩ ተወላጆች ምን ይሰማቸዋል አይባልም እንዴ? …

በዚህ ዜና ላይ ብዙ ብዙ ነገር ማለት ይቻል ነበር፡፡ መተው ነው የሚሻለው፡፡ ምንም ጥቅም በሌለው ጉዳይ ላይ “መሟዘዝ” ምንም ጥቅም ስለሌለው ነው “ኢሳትን ተው በሉት” የምለው፡፡

በመጨረሻ

ይህንን ፅሁፍ እየከተከብኩ ሳለ ድንገት ዓይኔን ወደመፅሐፍ ሰንዱቄ ወረወርኩ፡፡ እናም ዓይኔ “የነፃ ጋዜጠኝነት መማሪያ መፅሐፍ” የሚል መፅሐፍ ላይ አረፈ፡፡ አሜሪካ ኤምባሲ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ክህሎት ለማሳደግ ባዘጋጀው የጥቂት ቀናት ኮርስ ላይ ተገኝቼ ያገኘሁት መፅሐፍ ነው፡- የዛሬ 2 ዓመት ገደማ፡፡ እናም ይህንን ፅሁፍ ለመደምደም መፅሐፉ በመግቢያው ላይ ያሰፈረውን ዓቢይ ቁምነገር መዋስ ወደድኩ፡፡ እነሆ፡-

“…በ20ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ በአሜሪካን ሃገር ያለው ኮሚቴ ኦፍ ኮንሰርንድ ጆርናሊስትስ የተባለው ቡድን ባደረገው ጥናት ጋዜጠኞችን ስለሙያቸው ባህርይ ሲጠይቅ አንድ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ይኸውም ‹የጋዜጠኝነት ዋና አላማ በነፃ ሕብረተሰብ ውስጥ ዜጎች ኑሯቸውን የሚያስችላቸውን ትክክለኛና አስተማማኝ መረጃ መስጠት ነው› የሚል ነው፡፡

ይኼ ዕውነታ ሁሉችንንም ያስማማናል ብዬ አምናለሁ፡፡ አዎ “ትክክለኛና አስተማማኝ መረጃ መስጠት ነው› የማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ሚና፡፡ እንጂ እንዲህ ያደረገው ያኛው ብሔር ነው፤ እንዲያ ያደረገው ያደረገው ያኛው ብሔር ነው እያሉ የተዛባና ልዩነትትን የሚፈጥር መረጃ በመስጠት አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ኢሳትን ተው በሉት የምለው፡፡ በነፃ መገናኛ ብዙሃንነት ስም መረጃን ማዛባት እና በሕዝብ መሃል ልዩነትን ማስፋፋት ፣ “በእውነት ስም የውሸትን ምስማር ማቀበል” ነው የሚሆነው፡፡ እናም እባካችሁ ኢሳትን “ጭቃ አትርገጥ” በሉት፡፡ ኢሳትን ተው በሉት!!

የረሳሁት

ከወራቶች በፊት ወደባህር ማዶ የመረሸ አንድ የቅርብ ወዳጅ አለኝ፡፡ ይኼ ወዳጄ የሙያ አጋሬም ነው፡፡ አንድ ቀን በፌስቡክ መስኮት አገኘሁት፡፡ ወደሃገር ቤት እመለሳለሁ ካለበት ጊዜ የበለጠ እዛው ባህር ማዶ መሰንበቱ ትዝ አለኝና አንድ ጥቃቄ ሰነዘርኩለት፡- “እንዴት ነው በዚያው ኢሳት ገባህ እንዴ?” የሚል፡፡ መቼም ከሃገር የወጣ ጋዜጠኛ ኢሳት ለመግባት ከልካይ የለውም በሚል እሳቤ ነው፡- ጥያቄውን የሰነዘርኩት፡፡ ጥቂት የሙያ አጋሮቼን ከሃገር እንደወጡ ያየኋቸው እዛው ኢሳት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ጥያቄውን የሰነዘርኩለት ወዳጄ ላቀረብኩለት ጥቃቄ የሰጠኝ ምላሽ እንዲህ የሚል ነው፡- “ምነው፣ ምነው? ኢሳት ከምገባ፣ እሳት ውስጥ ብገባ ነው የሚሻለው!”

ይህ የወዳጄ ምላሽ አልገረመኝም፡፡ የባህር ማዶው ክራሞቱ ከእኔ የበለጠ ኢሳትን በየቀኑ ለመከታተልና ለመታዘብ ሰፊ ዕድል ያለው ነውና፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ኢሳት በዚህ መልኩ ትዝብት ሥር እንዲወድቅ አልፈልግም፡፡ ቢያንስ የማደንቃቸውና በሙያውም ያረቁኝ የቀድሞ የሙያ አጋሮቼ አሉበት፡፡ በነዚህ የቀድሞ አጋሮቼ ሥራ መኩራት እፈልጋለሁ፡፡ አዎ ኢሳት ተመራጭና ተወዳጅ የሕዝብ ልሳን እንዲሆን እሻለሁ፡፡ ቢሆን ደስ ይለኛል እንጂ አይከፋኝም፡፡ የምከፋበትም ምክንያት የለም፡፡ ህዝባዊና ሃገራዊ ጠቀሜታ እንዲኖረውም እመኛለሁ፡፡ ነገር ግን አያያዙ አላማረኝም፡፡ ስለዚህ ነው ደግሜ ደጋግሜ “ኢሣትን ተው በሉት” የምለው፡፡ ግዴላችሁም “የእኔ ብላችሁ” ተው በሉት! ከአሁኑ አርሙት እንጂ አታጥፉት!!

አበቃሁ!!

************

Source: Awramba Times, May 21, 2013.

Daniel Berhane

more recommended stories