* በ1936 ዓ.ም የተቋቋመው አየር ኃይል እስከ አሁን በ13 አዛዦች ተመርቷል
* ከውጊያ በረራና ማጓጓዝ ባሻገር ጥገናና ባለሙያ ስልጠና መስጫ ተሟልቶለታል።
* ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ግዳጅ (ሠላም ማስከበር) መሰማራት ጀምሯል
* በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

(በገለታ ገ/ወልድ)

* በ1936 ዓ.ም የተቋቋመው አየር ኃይል እስከ አሁን በ13 አዛዦች ተመርቷል
* ከውጊያ በረራና ማጓጓዝ ባሻገር ጥገናና ባለሙያ ስልጠና መስጫ ተሟልቶለታል።
* ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ግዳጅ (ሠላም ማስከበር) መሰማራት ጀምሯል
* በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለመከላከያ ኃይላችን ትክክለኛ ገጽታ እየተረዳን፤ ከጦርነት ባለፈ የልማት ኃይልና የሀገር ዋስትና መሆኑን እያረጋገጥን እንገኛለን። በቅርቡ የመከላከያ ዓመታዊ በዓል ላይ በቀረቡ አውደ ርዕዮችና ዶክመንተሪዎች የተመለከትነውን ሃቅ ማስታወስ ይቻላል። ለእዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ግን ከወር በፊት የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ለመጎብኘት የገጠመኝ ዕድል ነው። በወቅቱ የሥራ ኃላፊዎችን አናግሬ፣ የህትመት ውጤቶችን አገላብጬ ለሕዝብ ሊደርሱ ይገባቸዋል (ምስጢራዊ ያልሆኑትን) የሚባሉትን መረጃዎች ለአንባቢዎች ላካፍላችሁ ወድጃለሁ። እነሆ አዲስ ዘመን ስለተባበረኝ ሊመሰገን ይገባዋል።

ኢትዮጵያ የኩሩ ሕዝብና የጀግኖች ሀገር ነች ሲባል በግምት አይደለም። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረው የአርነትና ተጋድሎ ታሪካችን ምንጊዜም ስለሚዘከር ነው። የኢፌዴሪ አየር ኃይልም የሴክተሩን አርአያዎች አልዘነጋም። ኮ/ሌ በዛብህ ጴጥሮስን «የጀግንነት ተምሳሌት ከሆኑት የአየር ኃይል አብራሪዎች» በሚለው የታሪክ ማህደሩ መዝግቦት ተመልክቻለሁ።

እንደሚታወቀው ኮ/ሌ በዛብህ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ድንቅ የውጊያ አውሮፕላን አብራሪዎች አንዱ ነበር። በሰሜንና ምሥራቅ ኢትዮጵያ በነበሩ ውጊያዎች ተሠልፎ ሀገሩና መንግሥት የጣሉበትን ኃላፊነት በታላቅ ጀግንነት የተወጣ ቆፍጣና ተዋጊ ነው። በቅርቡ ሻዕቢያ በድፍረት ሀራችንን በወረረበት ወቅትም የሀገሩን ጥሪ ዳግም ተቀብሎ ሲዋጋ ነበር ሊማረክ የቻለው።

ከተቋሙ እንደተገለጸልን፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ የሚጀምረው ከ1936 ዓ.ም አንስቶ ነው። ከምሥረታው እስከ 1942 ዓ.ም በንጉሡ ቀጥታ አመራር በሲውዲናዊዎቹ ጄኔራል ሐርድና ካውንት ቮን ሮዛን (ኮሎኔል) አማካሪነት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። በኋላም ብ/ጄ ኮርት ሌን ድሃል (ስዊድናዊ) ጨምሮ እነ ሜ/ጄ አሰፋ አያና፣ ሜ/ጄ አበራ ወ/ማርያም፣ ብ/ጄ ዮሐንስ ወ/ማርያም፣ ብ/ጄ ታዬ ጥላሁን፣ ሜ/ጄ ፋንታ በላይ (ለረጅም ጊዜ)፣ ሜ/ጄ አምሃ ደስታ፣ ሜ/ጄ አለማየሁ አጎናፍር መርተውታል። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት፣ ሜ/ጄ አለምሸት ደግፌ፣ ሜ/ጄ ሞላ ሃ/ማርያም (አሁን በኃላፊነት ላይ ያሉ) እንዳስተዳደሩት ተዘግቧል።

Photo - Sukhoi Su-27 military jet of Ethiopian Air Force
Photo – Sukhoi Su-27 military jet of Ethiopian Air Force

የአየር ኃይልን ግቢ በጎበኘንበት ወቅት «አየር ኃይልና የበረራ ትርዒት» የሚል ጽሑፍ አግኝቼ ነበር። የኢፌዴሪ አየር ኃይል በንጉሡ ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገትና መሻሻል እያሳዬ ነበር። ለእዚህ ማሳያው የውጊያ ችሎታና የበረራ ትርዒት ላይ አስገራሚ ብቃት ያላቸው አብራሪዎች መታየታቸው ነበር። በ1960ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ የንጉሠ ነገሥቱ አየር ኃይል አብራሪዎች ብዛት ባላቸው አውፕላኖች የአየር ትርዒት ማሳየት የተለመደ ነው። በአንድ ወቅት ንጉሡ በክብር እንግድነት ሲገኙ አብረዋቸው የነበሩት የኬንያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ «የኢትዮጵያን ነፃነት በሚገባ የሚጠብቅና በቂ ዋስትና ያላችሁ ለመሆኑ ይህ ዓይነተኛ ምስክር ነው። ስለዚህም ዓይነ ሥውር ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያን ነፃነት ለመድፈር የሚመጣ ይኖራል ብዬ አላምንም» ማለታቸውን ሠነዱ ያስረዳል።

ታሪካዊው «የኢትዮጵያ ክንድ!» እንዲህ ያለ ዝና እያስመዘገበ ቢቀጥልም በወታደራዊው መንግሥት ዘመናት ስኬታማ ጉዞ የተራመደ አልነበረም። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት በሀገሪቱ በየቦታው ያለው ጦርነትና የአየር ኃይሉ አቅም ካለመጣጣሙ ባሻገር በመጀመሪያዎቹ የደርግ ዓመታት በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር- አየር ኃይል። በእዚህም ምክንያት እያሽቆለቆለ መጥቶ እንደነበረ በወቅቱ የነበሩ አዛዦች «በጥብቅ ምስጢርነት» በጻፉት ደብዳቤ ማስፈራቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ተጽፏል።

«… በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ባለው ውጊያ አብዛኛው ግዳጅ የሚከናወነው በአውሮ ፕላን ተሳትፎ አለዚያም በአውሮፕላን ብቻ ስለሆነ በአብራሪዎች ላይ የመሰላቸትና የመድከም ሁኔታ ይታያል። በመሠረቱ የውጊያ ዕቅድ የሚታቀደው ባለው አቅም ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት።…» ይላል ከ23 ዓመት በፊት ሜ/ጄ አምሀ ደስታ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር የፃፉት ደብዳቤ በአየር ኃይል (2004) መጽሄት ላይ ተጠቅሶ እንደ ተቀመጠው። ተቋሙ እንዲህ እየተዳከመ ባለበት ጊዜ ነበር የሥርዓት ለውጥ ተደርጎ ከ1986 ወዲህ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተለት።

የአሁኑ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄ ሞላ ኃይለማርያም እንደሚገልጹት ቀደም ብሎ በውጫዊ ገጽታው ታላቅነቱ ሲወራለት የነበረው አየር ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ በመምጣቱ የበረራ ትምህርት ቤቱን ወደ መዝጋት ተቃርቦ ነበር። አሁን ግን ዋናው ልማት የሰው ኃይል እንደመሆኑ በአዲስ ካሪኩለም፣ ጀግንነትና ብቃት ባላቸው መምህራንና በግብአት ተሟልቶ እንዲደራጅ ተደርጓል። በመሆኑም ከራሳችን ሠልጣኞች አልፎ በአሁኑ ደረጃ አለ የተባለ ወታደራዊ የበረራ ማሰልጠኛ ለመሆን እየሠራ ነው።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል በታሪክ ከሚጠቀስበት ተግባር አንዱ ዓለም አቀፍ ግዳጅ (የሠላም ማስከበር ሥራ) ነው። በእዚህ መሠረት በ1960 ዓ.ም በአራት ኤፍ 86 አውሮፕላኖች በፍላይት ደረጃ ኮንጎ ዛየር በተደረገው የሠላም ማስከበር ሥራ ላይ መሳተፉ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በመቀጠል በአቭዬሽን የሰላም ማስከበር ዩኒት የተላከው በ2000 ዓ.ም ወደ ዳርፉር ሱዳን (UNAMID) ሲሆን በአምስት ሚ- 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ከተሟላ የጥገና አቅምና የድጋፍ መሣሪያዎች ጋር ነው። ከእዚያም በኋላ በUNግዳጆች በመሰማራት በአብየና ሩዋንዳ የሎጅስቲክና ጦር ማዘዋወር ግዳጆችን በብቃት እንደተወጣ የሥራ ኃላፊዎች ያብራራሉ።

የአየር ኃይል የአቬዬሽን ጥገና አቅሙ መጐልበትም በጥንካሬ የሚነሳ አቅም ነው። ምንም እንኳን የጥገና ተቋሙ ከ1921 ጀምሮ በውጭ ሀገር ዜጐች ጭምር አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም 1970ዎቹ ገደማ መዳከም አሳይቷል። በተለይ «የሶቬዬት ኅብረት ትጥቆች ወደ ሀገራችን መግባታቸውን ተከትሎ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ብልሽት ሳያጋጥማቸው ውጭ ሀገር ልኮ ማሠራት እየተለመደ ነበር።» ይላሉ ለረጅም ዓመታት በተቋሙ የሠሩ የክፍሉ አንዳንድ ኃላፊዎች።

ከአየር ኃይል የወጣ የፅሑፍ መረጃ እንደሚያስረዳውም በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የውስጥ ጥገና አቅም በመዳከሙ የማይሠሩ አውሮፕላኖች በዝተው ነበር። ለምሳሌ ከነበሩት 48 ሚግ 21 አውሮፕላኖች መካከል ለውጊያ ዝግጁ የነበሩት 6 ብቻ ነበሩ። ከእዚያ ውድቀት ወዲህ የሻቢያን ወረራ ለመቀልበስ የተደረገውን ርብርብ አዛዦች በኩራት ይናገሩታል። «ዴሞክራሲያዊ ቅንጅት በተግባር የታየበት ውጤታማ ወቅት» በማለት።

«ከአየር ኃይል የጥገና ማዕከል ባሻገር ዛሬ በደጀን አቬዬሽን የሚሠሩ (የሚጠጉኑ) አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ከሀገር አልፈው እንደ ሱዳን አንጎላና ደቡብ ሱዳንን ጭምር እያገለገሉ ነው» ሲሉ አስጐብኚአችን ሻምበል ሚካኤል የገለጹልን ደግሞ በጥገና ላይ ያሉ አውሮፕላንና ሄሊኮፕተሮችን በጐበኘንበት ወቅት ነበር። በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የአውሮፕ ላንና ሄሊኮፕተር ሞተሮችና ክንፎችን እንዲሁም የውስጥ ክፍሎች በጥራት ይጠገናሉ። «የኦቨር ሆል» ጊዜ ገደብ የማራዘም ሥራ የሞዲፌኬሽንና የፈጠራ ሥራዎች ይከናወናሉ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሲቋቋም የነበሩት የአየር ምድቦች የማዕከሉን ደብረ ዘይት ምድብ ጨምሮ በአሥመራ በድሬዳዋና በሐረር ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ መቀሌና ባህርዳር ተጨምሮ አሁን በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫ የአየር ምድቦች ተቋቁመዋል። በእዚህም ሀገሪቱን ከማንኛውም የአየር ጥቃት የሚጠብቅ የ24 ሰዓት ተጠንቀቅ ያለው አቅም እንደሆነ የሥራ ኃላፊዎቹ ያስረዳሉ።

የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠ/ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ በቅርቡ ከመከላከያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መከላከያ እየፈጠረ ላለው ጥንካሬና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ሕዝባዊ ሽግግር፣ አየር ኃይል የራሱ የጐላ ድርሻ አለው ብለዋል ፤ በቀጣይም የአየር ክልላችንን በአስተማማኝነት ከመጠበቅ ባሻገር ሁለንተናዊ አቅም ለመገንባት ከምንጊዜውም በላይ የወትሮ ዝግጁነቱን ማረጋገጥ እንደሚ ጠበቅበትና ተቋሙ ከሪፎርሙ ወዲህ ባደረጋቸው ትላልቅ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በበረራውም ሆነ በጥገናው ዘርፍ የራስ አቅምን ይበልጥ ለማሳደግ መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአየር ኃይል የማዕከል ምድቡ ግቢ (ቢሸፍቱ) ሞቃታማ ቢሆንም አረንጓዴ የሞላበትና ጽዳት የማይለየው ነው። የምድቡን የጥገና የሥልጠናና መሰል ክፍሎች ለመጎብኘት (ደጀንም የሚጎበኝ በቅርበት ያለ የጥገና ማዕከል ነው) የሚሄድ ሰው በርካታ የፎቶ የሥዕልና ቻርት መረጃዎችን ይመለከታል። በአንድ ግድግዳ ላይ የተመለከትኩት «አየር ኃይል በውጭ ሀገር ኃላፊዎች ሲጐበኝ» የሚለው ርዕስ ታዲያ ትኩረትን ይስባል።

ከእንግሊዛዊቷ ንግሥት ኤልሳቤጥ ጀምሮ የቤልጅየሙ መሪ በኋላም እነ ፊደል ካስትሮ፣ የጋናው መሪ ጆሪ ሮሊንግ የኮንጐው ሞቡቱ ሴ ሴ ሴኮ መጎብኘታቸውን ያመለክታል። የቀድ ሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜ የነበሩ የሀገሪቱ የተለያዩ መሪዎች ጉብኝቶች የሥልጠና ምርቃቶችና ንግግሮችም በታሪክ ማኅደር ተይዘዋል።

በአንድ ወቅት ስመገናና የነበረው የአየር ኃይላችን በመሐል መዳከም ቢታይበትም ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ድንቅ ግስጋሴ እያስመዘገበ ነው። የበረራ አቅሙን ወቅቱ እስከደረሰበት ቴክኖሎጂ በማሳደግ ያለውን ነባር አቅም (ሀብት) በመጠንና በጥራት በማሻሻል የሰው ኃይሉን በስፋት በማልማት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ሀገራዊና ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነቶቹ ባሻገር በማኅበራዊ ዘርፍም እየተንቀሳቀሰ ነው።

በስፖርቱ ዘርፍ አየር ኃይል አንጋፋው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ጨምሮ በርካታ አትሌቶችን አፍርቷል። በእግር ኳስ ስፖርትም አየር ኃይል ስም ያለው ክለብ የነበረውና እስከ አሁንም የቀጠለ እንደሆነ ይታወቃል። በአካባቢ ጥበቃና የልማት ሥራዎች ረገድ በተለይ የአየር ምድቦች በሚገኙበት አካባቢ ካለው ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራም እንደሆነ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ።

በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) አየር ኃይል አካባቢ ያገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ለተቋሙ ያላቸው ፍቅር አባባሉን ያረጋግጣል። «አየር ኃይልና ደብረዘይት ተነጣጥለው አይታዩም። በስፖርት በአካባቢ ልማትም ሆነ በአደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት አየር ኃይል ሲንቀሳቀስ እንደራሳችን ተግባር ነው የምንቆጥረው» ይላሉ፡፡ የበረራ ምድቡ ደስታም ሆነ ኀዘን እንደቅርብ ጎረቤት የሚሰማን ጎረቤታሞች ነን በማለት ያስረዳሉ።

ቀደም ሲል የአየር ምድቡ ከከተማ ዳርቻ የተሠራ ቢሆንም አሁን በከተማዋ መስፋት አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች ተጠግተውታል። አንዳንዶች «የአውሮፕላንና ሄሌኮፕተር ድምጾች ዘወትር ቢጮኽም ስለለመድነው አይሰለቸንም። ደግሞ ብዙዎቻችን የወታደር ልጆችና ቤተሰቦች ስለሆንን እንደሕይወታችን አንድ አካል ቆጥረነዋል» በማለት ይናገራሉ።

ከተቋሙ መስፋፋትና መጠናከር ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚጠቀሙ፣ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ሕይወታቸውን መምራት የጀመሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም አየር ኃይልን ይበልጥ የኩራታቸው ምንጭ ማድረግ ችለዋል።

በአጠቃላይ አንጋፋው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከትናንት እስከ ዛሬ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ እነሆ እዚህ ደርሷል። ዛሬ በታሪክ አጋጣሚ ወደሌላ የድል ምዕራፍ የሚያሸጋግረው ደረጃ ላይ መድረሱን ከላይ «በወፍ በረር» ለመነካካት ተሞክሯል። የጽሑፉ መቋጫ ለማድረግ የፈለኩት ግን በፊት በረራ ሠልጣኞች የምረቃ መጽሔት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በተናገሩት አባባል ነው።

«መንግሥታችን በቀየሰው ትክክለኛ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ጐዳና ባደረግነው ርብርብ ለተከታታይ ዓመታት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ድል እያስመዘገብን እንገኛለን። በእዚሁ ፈጣን የዕድገት ጉዞችን የሰላማችንና የልማታችን ፀር የሆኑት ኃይሎች የመጨረሻ ክስመታቸውን የሚያበስር መሆኑ በመገንዘባቸው ግስጋሴያችንን ለመቀልበስ የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ በወሰኑበትና በተግባር በተንቀሳቀሱበት ወቅት መከላከያችን ሰላማችንን በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይህን አኩሪ ተጋድሎ ከፈጸሙት የመከላከያ ተቋማት ውስጥ አንዱ አየር ኃይላችን መሆኑ ይታወቃል።

በቀጣይም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱንና የሀገሪቱን የአየር ክልል ከውጪ ወራሪ ኃይሎች በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ ለአጠቃላይ የምድር ኃይሉ የቅርብ አየር ድጋፍ ተኩስ የመረጃና ትራንስፖርት ድጋፍ ለማድረግ የሀገሪቷ ሕዝቦች የሚገጥማቸውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ለመታደግ እንዲሁም ሀገራችሁ የምትሰጣችሁን ማንኛውንም ተልዕኮ ለመወጣት በዕውቀት በአቅምና በጀግንነት ዝግጁ ሆናችሁ እንደም ትቀጥሉ እምነቴ የፀና ነው»

የሚል ነበር። እኛም ይሄንኑ የአደራ ቃል እያስታወስን ጽሑፋችንን ቋጨን።

***********

* Originally published on Addis Zemen, on May 21, 2013, titled “የአየር ኃይል በራሪ ክንፎች authored by Geleta Gebrewolde.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories