አዲስ አበባ | የቤት ፈላጊዎች አመዘጋገብ መመሪያ (ሙሉ ቃል)

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የቤት ፈላጊዎች ለምዝገባ ሲመጡ ማሟላት የሚገባቸዉን ቅድመ ሁኔታና የምዝገባ አፈፃፀም ስርዓት

1. መግቢያ

መዲናችን አዲስ አበባ በፈጣን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የምትገኝ መሆኗን በርካታ አብነቶችን በማንሳት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚሁ ፈጣን እድገት ጋር በተያያዘ በየደረጃው ባለው የአገልግሎት አሰጣጥና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና አስከትሏል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍም አስተዳደሩ የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየርና ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያካሄደው ግዙፍ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ስራ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

በከተማችን ከሚገኙ 387ሺ ነባር ቤቶች አብዛኛዎቹ ለመፍረስ የተቃረቡ በመሆናቸውና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ቤት ፈላጊ ነዋሪዎች በመኖራቸው ትኩረት የተሰጠው ተግባር ሆኗል፡፡Addis Ababa City

በመሆኑም እስካሁን ከ87ሺ በላይ ቤቶች ተገንብተው ከ435ሺ በላይ ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በያዝነው በጀት አመትም ከ95ሺ በላይ ቤቶች በፈጣን የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ በተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞች የሚገነቡ ቤቶች ለትክክለኛው ቤት ፈላጊና የመጠለያ ችግር ላለባቸው ዝቅተኛና መካከለኛ የከተማ ነዋሪዎች እንዲደርሱ ለማድረግ በአዲስ መልክ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም ህብረተሰቡ ለምዝገባ በሚቀርብበት ወቅት ሊያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችንና የፕሮግራሙን አጠቃላይ ይዘት ባጭሩ ከዚህ እንደሚከተለው ተዘርዝሮ ቀርቧል፡፡

2. የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ዓላማና መርሆዎች

2.1. ዓላማ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የሚካሄደው አዲስ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባና ነባሩን መረጃ ወቅታዊ የማድረግ ሂደት አሳታፊ፣ ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን በማድረግ የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግስት በተቀረጹት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል እንዲመቻችና ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ፡፡

2.2. መርሆዎች

2.2.1. ለሚካሄደው የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ህብረተሰቡን እንደየገቢ መጠኑንና አቅሙ ሊያሳትፍ የሚችል ስርዓት መከተል፣

2.2.2. ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊና ደረጃውን የጠበቀ ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት፣

2.2.3. የቤት ፈላጊዎች ምዝገባን ለህብረተሰቡ ተደራሽነት እንዲኖረው ማድረግ፣

2.2.4. ህብረተሰቡ ስለምዝገባው አካሄድ ግልጽ መረጃ እንዲደርሰው የማድረግ ሂደት መከተል፣

2.2.5. ምዝገባውን በዘመናዊ የመረጃ ስርአት የተደራጀ በማድረግ ተአማኒነት እንዲኖር ማስቻል፣

2.2.6. ተመዝጋቢዎችን ከባንክ ጋር በማስተሳሰር የቁጠባ ባህል እንዲዳብር የሚያስችል አሰራር መዘርጋት፡፡

3. የምዝገባ አፈጻጸም ስነ ስርአት

3.1. ለምዝገባ ብቁ ስለመሆን

ማንኛውም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነና፣

3.1.1. እድሜው ከ18 አመትና ከዚያ በላይ የሆነ፣

3.1.2. በከተማዋ ውስጥ ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ አመታት የኖረና እየኖረ ያለ፣

3.1.3. የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሆኖ ነገር ግን ለሁለት ተከታታይ አመታት በስራ ወይም በትምህርት ምክንያት ከከተማዋ ውጪ የኖረበትን ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ የሚችልና ማስረጃው በቦታው ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ወይም እንደሚቆይ በዝርዝር ማስረጃ ካቀረበ ለምዝገባ ብቁ ይሆናል፡፡

4. የምዝገባ መስፈርት

በተራ ቁጥር 3 ስር የተዘረዘሩት ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው ማንኛውም ተመዝጋቢ፣

4.1. የ10/90 ወይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች የቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች

4.1.1. በራሱም ሆነ በሚያስተዳድረው ቤተሰብ የሚገኝ በየወሩ ብር 187 መቆጠብ የሚችልና የግዴታ ውል መግባት ይኖርበታል፡፡

4.1.2. አነስተኛ ገቢ ያለው ስለመሆኑ ተቀጣሪ ከሆነ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የገቢ መጠኑና የገቢ ግብር ስለመክፈሉ የሚያሳይ ማስረጃ፣ ተቀጣሪ ካልሆነ ከሚሰራበት ተቋም/ድርጅት/ ስለገቢ መጠኑ ማስረጃ የሚያቀርብ በህዝብ መድረክና በተለያዩ አደረጃጀቶች በኮሚቴ እንዲጠራ ይደረጋል፡፡

4.1.3. በቅድሚያ የባንክ ቁጠባ የጀመረና ለዚህም የባንክ የቁጠባ ሂሳብ ደብተር ያለውና በምዝገባ ወቅት ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

4.2. ነባር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት የቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች

4.2.1. በ1997 ዓ.ም ቀደም ሲል በተካሄደው ምዝገባ ተመዝግቦ ስሙ በመረጃ ቋት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፣

4.2.2. በተጠባባቂነት እጣ ወጥቶላቸው ነገር ግን ቤቱ ሳይደርሳቸው ስማቸው ከመረጃ ቋት ውስጥ የተሰረዙ ተመዝጋቢዎች ስማቸው ከተጠባባቂዎች ዝርዝር ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

4.2.3. በተመዘገበበት መኖሪያ ቤት በቅድሚያ ለባንክ ቁጠባ መጀመሩን የሚያሳይ የቁጠባ ሂሳብ ደብተር በምዝገባ ወቅት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

4.3. በሚመዘገብበት መኖሪያ ቤት በቅድሚያ የባንክ ቁጠባ መጀመር ይኖርበታል፡፡

4.3.1. በሚመዘገብበት መኖሪያ ቤት በቅድሚያ የባንክ ቁጠባ መጀመር ይኖርበታል፣

5. የ10/90፣ የነባር አዲስ 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች የሚጠበቅባቸው የጋራ ግዴታዎች

5.1. በራሱም ሆነ በትዳር ጓደኛው ስም በከተማ ውስጥ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የሌለው ወይም ከዚህ በፊት ኖሮት በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሶስተኛ ወገን መብቱን ያላስተላለፈ ወይም ከዚህ ቀደም የኮንዶሚኒየም ቤት በእጣም ሆነ በልማት ተነሺነት ተጠቃሚ ያለመሆኑን ማረጋገጥ ግዴታ መግባት አለበት፡፡

5.2. በራሱም ሆነ በትዳር ጓደኛውና በሚያስተዳድረው ቤተሰብ የሚያገኘውን ጠቅላላ ወርሃዊ ገቢ በትክክል በማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

5.3. ባለትዳር ከሆነ በቤት ልማት አማራጭ ፕሮግራሞች በራሱም ሆነ በትዳር ጓደኛው ስም ከአንድ ጊዜ በላይ ያልተመዘገበ መሆኑን ማረጋገጥና ግዴታ መግባት ይጠበቅበታል፡፡

5.4. የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መሆኑን የሚያረጋግጥ ወቅታዊ የነዋሪነት መታወቂያ በምዝገባ ወቅት በአካል ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

5.5. ምዝገባው በሚካሄድበት ወቅት በአካል ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

5.6. ስለ ተመዝጋቢው ዝርዝር መረጃ እንዲሁም ሌሎች ፍላጎቱንና ግዴታዎቹን በተዘጋጁ ቅጾች አማካኝነት በአግባቡ ሞልቶ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

6. ለምዝገባ የሚያስፈልግ የቁጠባ መጠን፣

6.1. ለነባር 20/80

* ለባለ 3 መኝታ ቤት ብር 685

* ለባለ 2 መኝታ ቤት ብር 561

* ለባለ 1 መኝታ ቤት ብር 274

* ለስቲዲዮ መኝታ ቤት ብር 151

ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ በየወሩ በተከታታይ 5 አመት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡

6.2. በአዲስ 20/80

* ለባለ 3 መኝታ ቤት ብር 489

* ለባለ 2 መኝታ ቤት ብር 401

* ለባለ 1 መኝታ ቤት ብር 196

6.3. ለ10/90 የመጀመሪያ የቁጠባ መጠን ብር 187 ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሳይቋረጥ ለ2 አመታት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡

ማሳሰቢያ፡- ቁጠባው የሚከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወይም በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብቻ ነው፡፡

* በማንኛውም ሰአት ተመዝጋቢው የቆጠበውን ገንዘብ እንዲለቀቅለት ከፈለገ ባለው የባንክ አሰራር መሰረት የቆጣቢው ገንዘብ ተመልሶለት ከምዝገባ መሰረዝ ይችላል፡፡

* ማንኛውም ተመዝጋቢ የሚጠበቅበትን የቅድሚያ ቁጠባ መጠን ሙሉውን ወይም ከተቀጠመው ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን ላይ ቆጥቦ የመመዝገብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

* ማንኛውም ተመዝጋቢ ቤቱን በሚረከብበት ወቅት የቤቶች ወቅታዊ የማስተላላፊያ ዋጋ መሰረት ቢያንስ ቅድመ ክፍያን ያሟላ መሆን ይኖርበታል፡፡

7. የተከለከሉ ድርጊቶች

7.1. አንድ ተመዝጋቢ ካሉት የቤት ልማት ፕሮግራም ከአንድ ጊዜ በላይ መመዘገብ አይችልም፡፡

7.2. ባልና ሚስት ከሁለት በአንዳቸው ስም ከአንድ ጊዜ በላይ መመዝገብ ክልክል ነው፡፡

7.3. እድሜው ከ18 አመት በታች የሆነ ሰው መመዝገብ አይችልም፡፡

7.4. በራሱም ሆነ በትዳር ጓደኛው ስም ቤት፣ የቤት መስሪያ ቦታ ወይም የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚ የሆነ ሊመዘገብ አይችልም፡፡

7.5. ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ውጪ የሆነ ማንኛውም ሰው መመዝገብ አይችልም፡፡

7.6. በአስተዳደሩ ተዘጋጅተው ከሚቀርቡ ቅጾች ውጪ በሌላ ቅጽ/ፎርም/ መረጃን ሞልቶ ማቅረብ ክልክል ነው፡፡

7.7. ከዚህ ቀደም የኮንዶሚኒየም ቤት እድል ደርሶት በተለያዩ ምክንያቶች ቤቱን ያልተረከበ ሰው በነባሩ 20/80 ዳግም ምዝገባ ሊስተናገድ አይችልም፣ ነገር ግን እንደ አዲስ ለመመዝገብ አይከለከልም፡፡

8. የምዝገባ ቦታ ለሁሉም ፕሮግራሞች

በተመዝጋቢው የመኖሪያ ወረዳና በተቋማት ብቻ ይሆናል፡፡

9. የምዝገባ ጊዜ

በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በተከታታይ የሚገለጽ ይሆናል፡፡

10. ከምዝገባ ስለመሰረዝ

10.1. ማንኛውም ተመዝጋቢ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ያቀረበው ማስረጃ ወይም የሞላው ቅጽ የተሳሳተ ወይም ሃሰተኛ መሆኑ በመዝጋቢው አካል ወይም በህዝብ ጥቆማ ከተረጋገጠ የወንጀል ኃላፊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የተመዘገበውም ምዝገባ ይሰረዛል፡፡

10.2. ማንኛውም ተመዘጋቢ በየወሩ ሊቆጥብ የሚገባውን የገንዘብ መጠን ለተከታታይ 6 ወራት መቆጠቡን ካቋረጠ የቆጠበው ገንዘብ እንዲመለስ ተደርጎ ከምዝገባው እንዲሰረዝ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን ተመዝጋቢው በየወሩ ከሚጠበቅበት አነስተኛ የቁጠባ መጠን በላይ በአንድ ጊዜ የቆጠበ ከሆነ ቁጠባውን እንደሸፈነ ይቆጠራል፡፡ ተመዝጋቢው በማንኛውም ወቅት ከምዝገባ ተሰርዞ የቆጣበው ገንዘብ እንዲመለስለት ከጠየቀ ባለው የባንክ አሰራር መሰረት ገንዘቡ ሲመለስለት ከምዝገባ ይሰረዛል፡፡

10.3. በነባር 20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም ላይ በ1997 ዓ.ም ተመዝግቦ የነበረ መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት በድጋሚ ቀርቦ ያልተመዘገበ ከሆነ በራሱ ፍላጎት/ፍቃድ ከምዝገባ እንደተሰረዘ ይቆጠራል፡፡

10.4. ለ10/90 ፕሮግራም ከ187 ብር በላይ በወር የመቆጠብ አቅም እያለው በዚሁ ፕሮግራም የተመዘገበ አመልካች መረጃ በተገኘበት ጊዜ ከምዝገባ ይሰረዛል፡፡

**********************************

በሌላ በኩል ከኤጀንሲው የተገኝ መረጃ የ40/60 ቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን ወርሓዊ የቁጠባ ግዴታዎች እንደሚከተለው ይዘረዝራል፡፡

* ለባለ 3 መኝታ ቤት ብር 2453
* ለባለ 2 መኝታ ቤት ብር 1575
* ለባለ 1 መኝታ ቤት ብር 1033

በተጨማሪም የ40/60 ፕሮግራም ምዝገባ ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመረጡ ቅርንጫፎች ከነሀሴ 5 እስከ 17 የሚካሄድ መሆኑን እና የመንግስት ሰራተኞች ለነሱ ብቻ በተዘጋጀ የተለየ መመዝገቢያ ቦታ ምዝገባው የሚካሄድ መሆኑ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ከላይ ለ10/90ና 20/80 ፕሮግራም ተጠቃሚዎችከተቀመጡት ግዴታዎች አግባብነት ያላቸው ክፍሎች የ40/60 ተጠቃሚዎችንም እንደሚመለከቷቸው ይገመታል፡፡

Daniel Berhane

more recommended stories