የተፈረካከሰ ርዕዮተ-ዓለም እስረኛው “መድረክ” በመፍረስ ዋዜማ ላይ

(ዮናስ)

የመድረክ መንገራገጭ – እንደመነሻ

በምርጫ 2002 ዋዜማ ላይ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በጠራ ፖሊሲና ፕሮግራም ሳይሆን በጠላቴ ጠላት ዓይነት በአንድ አዳር ለመወዳጀት የቻሉት የመድረኩ አባል ፓርቲዎች አመራር አካላት ፍላጎት ሥልጣን ነበርና መድረኩ በምርጫ 2002 ሲሸነፍ ለመንገራገጭ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡

የመድረኩ ጠንሳሽና ዋነኛ ክንፍ ነው የተባለው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መሪዎች መድረኩ የፀረ ዴሞክራሲያውያን ስብስብ ነው በሚሉና አይደለም በሚሉ አስተሳሰቦች ታምሰው ገሚሱ «በመርህ ይከበር» ተቃውሞ በመገንጠል ሰማያዊ ፓርቲን ሲያቋቁም፤ ይህንኑ የመርህን ይከበር አባላት ሲገፋ የነበረው ወገን ደግሞ የፓርቲውን ሥልጣን ተቆናጥጦ ከመድረክ ጋር ቀጠለ፡፡Merera Gudina, Gebru Asrat, Beyene Petros, Seeye Abraha, Gizachew Shiferaw, Negasso Gidada

ከመድረኩ ጋር በተቀላቀለው የመርህ ይከበር የአንድነት ቡድን አባላት ውስጥም ቢሆን በወቅቱ በተለይ በፌዴራሊዝምና በመሬት ጉዳይ ላይ ጥርት ያለ አቋምና ፕሮግራም እንደሚያስፈልግና በተጨባጭ ግን ጉዳዮቹ ከሥልጣን በኋላ ለሕዝብ ውሳኔ ይቀርባሉ በሚል የከሰረ አካሄድ ተድበስብሰው ማለፋቸው ተገቢ እንዳልነበረና የትም ሊያደርስ እንደማይችል ለመሞገት ቢሞክሩም፤ በይድረስ ይድረስ መድረኩን ያቋቋሙት የነጠላ ፓርቲዎቹ ባለቤቶች የመድረኩ መሪዎች በመሆናቸው ከአንድነቱ አካላት የተነሱ ጥያቄዎችን የኢህአዴግ ተለጣፊ አስተያየትና ፖለቲካ ያልገባቸው ግለሰቦች ጭፍን አስተያየት በማለት ዘልለውታል፡፡

ከእዚያም ነገሩ እንደ ነገረ ምርጫም አልነበረ ምና የሚያነሱበት ጊዜ አጥተው እዚያው በውስጣ ቸው ሲብላላና ሲንከባለል ቆይቶ ከአራት ዓመታት በኋላ የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ ሲደርስ በለመዱት የምርጫ ዋዜማ ግርግር መሠረት መድረኩን ወደግንባር አሸጋግረናል ዓይነት ማብሰሪያቸውን በማስቀደም ከማኒፌስቶ ጋር ብቅ አሉ፡፡

አሁንም በተመሳሳይ መድረኩ እንደመድረክ ባሳለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የሠራው አንዳች ነገር እንዳልነበረና ወደግንባርነት ሊያሸጋግረው የሚያስችል ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ምክንያት እንደሌለ ማስረጃ በማጣቀስ የመድረኩን ወደግንባር ተሸጋግሬያለሁ መግለጫ እንደ ፌዝ የቆጠሩት የፖለቲካ ተመራማሪዎች ማኒፌስቶውን በተመለ ከተም ምንም አዲስ ነገር እንደሌለውና ይልቁንም ገሚሱ ከ97ቱ ቅንጅት፤ ከፊሉ ደግሞ ከዚህም ከዚያም በተቀዱ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች መሞላቱ የመድረኩን መሪዎች ማንነት የሚያረጋግጥ እንደሆነም በማስገንዘብ ጭምር ተችተዋል፡፡ እንደተባለውም አልቀረ የመድረኩን አካሄድና አመሠራረት ሲተቹና ትክክል እንዳልሆነ ሲያመለክቱ የነበሩ ግለሰቦች«ብለን ነበር»ለማለት የሚያስችላቸው አጋጣሚ አሁን ተፈጥሯል። ይኸውም መድረኩ በመፍረስ አደጋ ላይ የመገኘቱ ተጨባጭ ሁነቶች መታየት መጀመራቸውን መሠረት ያደርጋል፡፡

መድረክ በውስጥ አውቆች ሲጠና

መድረክ ያጋጠመው የመፍረስ አደጋ መንስኤ የመድረኩ የተፈረካከሰ የርዕዮተ ዓለም ስብስብና እስረኛ መሆን ነው የሚለው የእዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ እምነት ነው፡፡ ስለሆነም በመድረኩ ፈጣሪነት ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበረውና የመድረኩ አባል ፓርቲ በመሆንና ባለመሆን አባላቱ ውዝግብ ውስጥ ገብተውበት የነበረው አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ የአንድነት ጠንሳሽ የነበሩትንና የመድረኩ አባል መሆን የለብንም ያሉትን የመርህ ይከበር አባላት የኢህአዴግ ተለጣፊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ቡድን በማለት ካባረረ በኋላ ዛሬ ደግሞ እራሱ አንድነት ራሱን እንደቻለ አንድ ፓርቲ የመድረኩ አባል መሆን አለበት ወይስ የለበትም? በሚል ለወራት የተጠናነው ከተባለው የጥናት ውጤት ጋር በማያያዝ ሃሳቤን እንደሚከ ተለው አቀርባለሁ፡፡

መድረኩ በተመሠረተበት ወቅት ብዙ ልዩነት ስላለን የመድረኩ አባል መሆን አንችልም ያሉ አባላትንና መሪዎቹን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ናችሁ በማለት አባርሮአቸው የነበሩትና አሁን አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ተመልሰው የመድረኩ አባል መሆን ይገባናል ወይስ ሌላ አማራጭ አለን? በማለት አንድ ኮሚቴ ያዋቅራሉ። ይህ ኮሚቴ መድረኩ በተመሰረተበት ወቅት የመድረኩ አባል ለመሆን ወደኋላ የሚጎትት አንዳች ነገር እንደሌለ ሲናገሩ የቆዩ አባላት ስብሰባ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ተጠና የተባለው ጥናት ግልባጩን ውጤት ይዞ መጥቷል፡፡

መድረክ ከተፈጠረ በኋላና ከመፈጠሩ በፊት የነበሩ በርካታ ሰነዶችን ለይቶ እንዳየ የሚናገረው ኮሚቴ የመድረኩ መተዳደሪያ ደንብ ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዳላገኘው ይገልጻል፡፡ ይህ ደግሞ ከመድረክ ችግሮች መካከል መሰረታዊው እንደሆነ የጥናት ውጤቱ ያብራራል፡፡ በተለይም ሌሎች ፓርቲዎችን በማሳተፍ በእውነተኛ አካሄድ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር በመፍታት በኩል ሕገ ደንቡ ችግር እንዳለበት የኮሚቴው ጥናት አጽንኦት ሰጥቷል።

ልብ በሉ ይህን የሚሉት የኮሚቴ አባላት በምርጫ 2002 ዋዜማ ላይ መድረኩን ሲያሞካሹና ከሰሞኑ ደግሞ የመድረኩን ማኒፌስቶ ሲያው ለበልቡ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እንደ አንድነት ኮሚቴ ቀደም ብለው ስላንቆለጳጰሱት የመድረኩ ፕሮግራም ሲናገሩ አሁን ባለው ሁኔታ የመድረኩ ፕሮግራም በአፋጣኝ ካልታረመ በስተቀር የአንድን ግንባር ሥርዓት/መመዘኛ የሚያሟላ ሆኖ አላገኙትም፡፡

ምክንያታቸውም ቀደም ብሎም መድረኩ ሲቋቋም በርካቶቹ የፖለቲካ ምሁራን ያሉትንና አሁን ደግሞ ብለን ነበር የሚያስብላቸውን «በፖለቲካ መርህ ደረጃ ወሳኝ በሆኑ ሁኔታዎች ጫፍ የረገጡ ፓርቲዎች ናቸው ግንባር የፈጠሩት» የሚል ነው፡፡

በማስቲሽ የተጣበቀው የመድረክ ስብስብ

ኢህአዴግ በምርጫ 2002 ዋዜማ ላይ ከመድረክ ጋር ባደረጋቸው ክርክሮች መድረኩ ጥርት ያለ ፕሮግራም እንደሌለውና ቢኖረውም አንዱ ከአንዱ የተቀየጠና በፖለቲካ መርህ በፍፁም ሊጣበቁ የማይችሉ ጉዳዮችን በማስቲሽ የማጣበቅ ያህል ነው። በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚታትር ለማሳየት ሞክሯል፡፡ አካሄዱ የማያዛልቅና ማስቲሹም የሚላቀቅ ስለመሆኑ ለተሰጠው አስተያየት መድረክ «የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንጂ እኛ አይደለንም በማስቲሽ ተያይዘን የመጣነው» የሚል ምላሽ ሰጥቷል። የመድረኩ አንዳንድ ፕሮግራሞች የተድበሰበሱና ግልፅነት የሚጎድላቸው ስለመሆናቸው በመመስከር በተለይ የመሬትና የፌዴራሊዝም ጉዳይ ወሳኝና አንገብጋቢ የፖለቲካ ጉዳዮች እንደሆኑም ይናገራል። እንዲሁም በቡድንና በግለሰብ መብቶች ቅደም ተከተል ላይ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሳይያዝ ግንባር ለመፍጠር መሞከሩን ተከትሎም ማስቲሹ በመላቀቅ ሂደት ላይ እንደሆነ የአንድነት ኮሚቴ ጥናት ያመለክታል፡፡

በመድረክ ውስጥ የቡድን መብት ማስከበርን አስቀድመው የጋራ ዓላማ በማለት የሊብራሊዝም አስተሳሰብን ያስቀመጡ ፓርቲዎች መኖራቸው በጠላቴ ጠላት የተወዳጁ ስለመሆናቸው እንደ ሚያረጋግጥ በወቅቱ ኢህአዴግም ሆነ የፖለቲካው ዘርፍ ምሁራን ቢናገሩም አላየንም አልሰማንም ሲሉ የነበሩት የመድረኩ አባል ድርጅቶች ዛሬ «ጫፍ የረገጠ የርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና እየተከተሉ ግንባር ማቋቋም ፈፅሞ አይቻልም» በማለት እየተናገሩ ነው፡፡

የአንድነት ፓርቲ ገምጋሚ ኮሚቴ ሲያሸረግ ድለት የነበረውን የመድረክ ፕሮግራም በተፈረካከሰ ርዕዮተ ዓለም ግንባር ለመፍጠር የተሄደበት ርቀት የሁኔታውን አስገራሚነት ይበልጥ እንደሚያጎላው በመጥቀስ በፕሮግራሙ ላይ ይሳለቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስብሰቡ «የግንባርነት ደረጃውን ሳይጨርስ ወደ ግንባር ማደጉ ትክክል አይደለም» የሚለው ኮሚቴ መድረኩ ከግለሰቦችና ከቡድኖች በወጣ መንገድ ላይ እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የመድረኩ አባል ድርጅቶች ከግለሰቦች የንግድ ድርጅቶች ተለይተው እንደማይ ታዩ ሲገልጹ የነበሩት የዘርፉ ምሁራንም «ብለን ነበር»ለማለት የሚገደዱት አሁን ነው፡፡

«መድረክ ስለሚባለው አንድ ስብስብ ከመጨነቅ በላይ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ እድገት መጨነቅ እንዳለብን የተረዳንበት አጋጣሚ ነው» የሚለው አጥኚ ኮሚቴ በፕሮግራምና የደንብ ችግር ላይ የተመሠረተው መድረክ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የማይፈታ በመሆኑ ስብስቡ ይህንን የመተግበርና የማለፍ እምነት ካጣ መድረክ መፍረስ ነው ያለበት በማለት አንድነት ከመድረኩ ስብስብ የመጀመሪያው ወጪና የመድረኩን መፍረስ መርዶ ነጋሪ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

መድረክ በመፍረስ ዋዜማ ላይ

«መድረክ በመፍረስ ዋዜማ ላይ እንደሚገኝ ከሚያረጋግጡት ነጥቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ምልክቶች በስብስቡ ውስጥ መታየታቸው ነው» ይላል አጥኚው። በተጨማሪም የኮሚቴው ጥናት ኮሚቴው «በብሔር መደራጀት ዴሞክራሲያዊ መብታችን ነው ብለው የሚወስዱትና መብታቸውም እንደሆነ የተቀበልንላቸው ጉምቱ የአመራር አባላት ህብረብሄራዊ ሆኖ መደራጀትን ዴሞክራሲያዊ ባለመሆን እየፈረጁት ስለመሆኑ አቶ ቡልቻ ደመቅሳና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተለያየ ጊዜ አንድነት የአማራ ፓርቲ ነው … አንድነት ጠቅላይ ነው… አንድነት የከተማ ልሂቃን ፓርቲ ነው ወዘተ» በማለት ለሚዲያ መናገራቸውን በማሳያነት አቅርቧል፡፡

የመድረክ ፕሮግራም ውል የሌለውና በጨበጣ ሥልጣን ላይ ለመውጣት በሚሹ ግለሰቦች የተፈበረከ እንደሆነ ሲነገራቸው አልሰማ ያሉት የኮሚቴው አባላት መድረክ ከሕዝብ ጋር ሳይሆን ከኢህአዴግ ጋር እየተወዳደረ በ«መሬትና በፌዴራሊዝም ጉዳይ ላይ ሥልጣን ከያዝን በኋላ ሕዝብ ይወስናል፤በኋላ እንፈታዋለን» ማለቱ መርህ የለሽ ፕሮግራም እንደሆነና በእርግጥም በጨበጣ ሥልጣን ላይ ከመውጣት ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ በጥናት ውጤታቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህንኑ የጨበጣ ሥልጣን መሻት የበለጠ ግልጽ የሚያደርገው ደግሞ በመስኩ ረጅም ጊዜ በቆዩ ፖለቲከኞችና የዴሞክራሲ አርበኛ ማን እንደኛ በሚሉ ኃይሎች የተነደፈ ፕሮግራም መሆኑና በእዚህም መድረክ ባለፉት አራት ዓመታት አንድ ስንዝር መሄድ ያልቻለ ስብስብ መሆኑ ነው፡፡

የመድረክ አባል ድርጅት የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ(ኦህኮ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ኦፍዴን) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ መድረክ በመፍረስ ዋዜማ ላይ ስለመሆኑና ማስቲሹም እየለቀቀ ስለመሆኑ ይፋ ያደረገውን ጥናት ፖለቲካ ባልገባቸውና በፖለቲካ መስክ ግራ በተጋቡ ግለሰቦች የተሠራ የመንገድ ሥራ አድርገው በመቁጠር አኮስሰውታል፡፡ ፕሮግራሙን ደርዝ የለሽ ስለመሆኑ ያረጋገጠውን ጥናትም ዶክተሩ እንደተለመደው«ኢህአዴግ ከሚቀልባቸው ሰዎች የሚነሳ ጥያቄ እንጂ የፖለቲካ ፕሮግራም ችግር የለብንም» በማለት በድፍረት መናገራቸው በእርግጥም በጨበጣ ሥልጣን ስለመሻታቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንዳሻው ደግሞ ግምገማውን «ሕገወጥ» በማለት የዘለፋ አስተያየት ይሰጡና እንዲያውም ግምገማው የድርጅቱ(የአንድነት) የውስጥ ትግል ነፀብራቅ እንደሆነ በመቁጠር ሊሸሹ ሞክረዋል። በእርግጥ ግምገማው የአንድነት የውስጥ ትግል ነፀብራቅ ሊሆን ቢችልም እንኳ መታየት ያለበት ስብስቡ በአጠቃላይ የጨበጣ ሥልጣን ፈላጊ ህልመኛ ፖለቲከኞች የተሰገሰጉበትና በተፈረካከሰ ርዕዮተ ዓለም የሚነዱ ፓርቲዎች ያሉበት ስለመሆኑ ያረጋግጣል። አንድነትም ግምገማውን ሲያስቀምጥ ውጤቱ እንደአባል ፓርቲ እራሱንም እንደሚመ ለከት ተቀብሎ መሆኑን ከግምት ከትተን ስንመ ለከተው የዶክተር መረራ ጉዲናና የአቶ ጥላሁን እንዳሻው አስተያየት ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ያሳየናል፡፡

ይህ ደግሞ በአንድነት ፓርቲ በራሱ የውስጥ ችግርም ሆነ በማናቸውም መነሻ ምክንያቶች የተደረሰበት የግምገማ ውጤት ብቻ ሳይሆን አንድነቶች ምንም እንኳ ዛሬ አጠናነው ቢሉም ቀድሞም ቢሆን የሚያውቁትና ብዙ የተባለበት ጉዳይ ነው፡፡

የጀብደኝነት ልጆች – በመድረክ ጥላ ስር

በህዳሴው ባቡር እንዳይሳፈር ሲታገሉት የነበሩትና ከትግል መድረኩ የሸሹት ወገኖች በሂደቱ ተስበው የወጡት «የህዳሴ ልጆች»በህዳሴው ጎዳና በድል ተረማምደው፤ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተሻግረው፤ ከምርጫ 2002 ሲደርሱ፤ በህዳሴው መባቻ በአካል የታገላቸው ኃይል መልክ ቀይሮና ቅርፅ ሰብሮ በጣዕረ መንፈስ ሲታገላቸው ነበር በማለት አሜን የተባሉ ፀሐፊ «የሁለት ምርጫዎች ወግ» የተሰኘውን የአቶ በረከት ስምኦንን መጽሐፍ በዳሰሱበት ወጋቸው ላይ አስቀምጠዋል፡፡

ፀሐፊው ዳሰሳቸውን ሲቀጥሉ በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ ስህተቶቹን አርሞ እንደወጣና የተቃዋሚው ጎራ ግን የአስተሳሰብ ሳይሆን የመልክ ለውጥ ይዞ እንደመጣ የሚያወጉን አቶ በረከት «የጀብደኝነት ልጆች» እንዲህ ፈጥነው ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ «መድረክ» በተሰኘው የፓርቲዎች ስብስብ ገብተውና እርሱን ወክለው በውድድር ቢቀርቡም በውድድሩ መሸነፋቸውን ያወጉናል በማለት መድረክን የተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በምርጫ 2002 ዋዜማ ላይ ከምርጫ 97 ቅንጅት የቀለም ለውጥ አድርጎ የመጣውን መድረክ ኢህአዴግ ሲገልጸው «መድረክ የአገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ፖሊሲ የሌለው፤ አለን የሚለውም ሃሳብ የአገራችንን ሕዝቦች የፀረ ድህነት ትግል የሚቀለብስና ወደትርምስ የሚያስገባ ነው» ይለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የምርጫ ሥነ ምግባር ራሱን ለማስገዛት ያልተዘጋጀው መድረክ በጨበጣ ሥልጣን ለመያዝ የሚሻ ኃይልና አገር የመምራት ኃላፊነት ሊቀበል የማይችል እንደሆነም ኢህአዴግ በሚገባ ነግሮታል፡፡

በአገራችን የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ በመሆኑ በኃላፊነት መንፈስ ሊጠቀምበት ለሚፈልግ ሁሉ ምቹ እንደሆነ በጊዜው የገለፀው ኢህአዴግ እንደ መድረክ ያሉት ተቃዋሚዎች በእዚህ ዕድል ከመጠቀም ይልቅ ያገኙትን ዕድል ሁሉ አገርን ለማተራመስ ሊጠቀሙበት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውንም በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል፡፡ ይህንኑ ሃሳብ «መድረክ የተሰኘውና በመድረኩ ጥላ ስር የተሰባሰቡ ፓርቲዎች የሀገራችንን ወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም የዜጎችን መፈናቀል ለፖለቲካ ፍጆታና ጥቅም በማዋል ላይ ናቸው» ሲል ባለራዕይ የተሰኘ የወጣቶች ማህበር ገልፆ ፓርቲዎቹ የሀገራችንን ፖለቲካ ወደፊት ሊያራምዱ በሚችሉ አጀንዳዎች እንዲጠመዱና ይህንኑ በሚያሳኩ ፖሊሲና ፕሮግራሞች እንዲመሩ ሳያሳስባቸው አልቀረም።

አዲስ ታይምስ መጽሔትም በአንድ ወቅት መድረክ የአመራር አባላቱን በተመሳሳይ መንገድ ገልጿቸዋል። «መድረኩ ግራ በተጋቡ ፕሮግራሞችና ግራ በተጋቡ ግለሰቦች የተሞላ ሲሆን፤ ይህንኑ ግራ የተጋባ መረጃ ለማግኘትም የሚቻልበት ዕድል የለም። ድረ ገጽ እንኳ የሌለው በቀሽም አመራሮች የተሞላ ፓርቲ ነው»:: በእዚህም ምክንያት የትም መድረስ እንደማይችልና አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ የገለጸው አዲስ ታይም ምንአልባትም ቀን ቆርጦ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊፈርስ እንደሚችል ከመተንበይ ወደ ኋላ አላለም።

የመድረክን የበላይ አመራር አባላት በተመለከተ ሎሚ መጽሔት ደግሞ እንዲህ ትለናለች።«ተቃዋሚ መሪዎቻችን በረጅሙ የፖለቲካ ዘመናቸው ያመጡት ለውጥ የትአለ?» ብለን ለፍለጋ ብንነሳ የምናገኘው ውጤት ቢኖር ጠ/ር መለስ ዜናዊ «ሳስበው ሳስበው ደከመኝ» ብለው ለፓርላማቸው የጋበዙትን ቀልድ ነው።

*************

Source: Addis Zemen – May 12, 2013.

Daniel Berhane

more recommended stories