Social | አድርባዮች አደጋዎች ናቸው

አድርባይ አድር ብሎ ያልሆነውን ነው የሚል የሆነውን ደግሞ የለም አልተደረግም ብሎ የሚክድ ነው። ይህን እንደ አስተዋጾ ቆጥሮም ለሞላጫ አድራጎቱ ዳረጎት ከአለቃው የሚጠብቅ መሰሪ ግን በራሱ መተማመን የማይችል ምስኪን ነው።

አድርባይነት በየትኛውም ትግል እና ግንኙነት ውስጥ ብዙ ጊዜ ችላ የሚባል ግን ውስጥ ውስጡን ሰፊ ጉዳት የሚያደርስ ምግባረ ብልሹነት ነው። የገዥ ፓርቲም ይሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አድርባዮች መሰረታዊ ባህሪያቸው ያው እና አንድ በመሆኑ የሚደቅኑት ስጋት ተመሳሳይ ነው።

አድርባዮች ሁሉንም ሥራና ግንኙነት የሚወስኑት «ለእኔ በዚህ ውሳኔ ወይም ተግባር የማገኘው አለያም የማስጠብቀው ጥቅም ምን አለ» በሚል ነው እንጂ ሌላ አገራዊ አካባቢያዊና ማህበራዊ ጥያቄ መጠየቅ ምርጫቸው አይደለም።

ለእዚህ ሁሉ የሚዳርጋቸው ግን በጥረቴ አድጋለሁ የሚል በራስ መተማመን የሌላቸው መሆኑ ነው። በራስ ጥረት መስራት ቀርፋፋነትና «ሙደኛ»አለመሆን ይሆንባቸዋል። አቋራጩ መንገድ ሁሌም ቅንጥብጣቢ የሚያገኙ ከመሰላቸው አጀንዳ እና አለቃ ጋር መንፈስ ነው።

አቋማቸው ሁሌም ዕድገቶችን እና ሹመቶችን የሚያጸድቀውን ሰው በገባቸውም ባልገባቸውም፣ በሚመለከታቸውም በማይመለከታቸውም ጉዳይ ላይ መደገፍ ነው። እነርሱ በመቶ ብሮች የሚቆጠር ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ከመሰላቸው ሌላ ሰው ያለ ጥፋቱ ወይም ትንሿን ጥፋቱን አጋነው ከሥራ ለማስባረርና ሺዎችን ሊያሳጡት ከመሥራት ወደኋላ አይሉም። ብቻ ያ ድርጊት ያሳድገናል ብለው ይመኑ፣ ተስፋ የሚያደርጉትን ሰው ያስደስታል ብለው ይገምቱ እንጂ ወደኋላ ማለት አይነካካቸ ውም።

እኚህ ሰዎች እጣ ፈንታችንን ይወስናል ብለው የሚያምኑትን ሰው ሆድ ያራራል ብለው ካሰቡ የእዚያን ሰው ጓደኞች እና ዘመድ አዝማድ ከመቅጠር፣ በጨረታ ከማሳለፍ ወይም ያለአግባብ ከመጥቀም ወደኋላ የሚሉ አይደሉም። ጅቦች ናቸው።

እንደእዚህ አይነት የሥነምግባር ልሽቀት ያለባቸው ሰዎች ሁሌም ያ «የዕጣ ፈንታቸውን ወሳኝ» የሚሉትን ኃላፊ ማሞካሸት፣ ሲሳሳትም ሳይሳሳትም ትክክል ነህ ማለት፣ እርስዎ እንዳሉት ብሎ የተገፋውን መጣል፣ የተነሳውን መስቀልና የተደነቀውን ምንተስኖት ማድረግ ሁነኛ መለያቸው ነው።

ሌላው ለማዳው ባህሪያቸው ያንን አለቃቸውንና አጋሮቹን እሺ እሺ፣ አዎ አዎ፣ ልክ ነህ ልክ ነህ ማለት፤ በተቃራኒው ያ ኃላፊ ፊት ነስቷቸዋል ብለው የሚያስቧ ቸውን የለም፣ ልክ አይደለም፣ አይሆንም፣ ተሳስተሀል፣ አቋምህ ጸረ … ነው ማለት ሱሳቸው ነው።

እዚህ አይነት ሰዎች ተስፋ በሚያደርጉት አለቃቸው በመተማመን ላታቸውን ደጅ የሚያሳድሩ ቢሆንም የለየላቸው ፈሪዎች ናቸው። በተለይ የዛ ተስፋ የሚያደ ርጉበት አለቃቸው ፊት የጠቆረ ቀን ፊታቸው ሲጨልምና ቀኑ ሲመሽባቸው፤ ያ ሙሉ በኩለሄ አለቃቸው ፊቱ የፈገገ ቀን ቀናቸው ሲበራ የሚኖሩ የበራስ መተማ መናቸው ማብሪያና ማጥፊያ በአለቃቸው ግንባር ላይ የተገጠመላቸው በምርጫቸው የላሸቁ የምርጫቸው ምርኮኞች ናቸው።

የአለቃቸውን ክብርና የማዘዝ ስልጣን አክብረው ሲያበቁ ይጠቅማል የሚሉትን ነፃ ሃሳብ ማራመድ የትንታግ ያክል የሚፈጃቸው፣ ደፈር ያሉ በጥረታቸው እንጂ ተሞዳሙደው በማደግ የማያምኑ፣ የተሳሳቱ ቀን ታርመው ለመሄድ ትክክልም የሆኑ ቀን ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሊረኩ የሚሹ ጎበዞች ሲናገሩ የሚያንገፈግፋቸው፣

ትግልን የሚማጸኑትን ኃላፊ አቋም መደገፍ ብቻ አድርገው የሚያዩ፣ ሃሳቡ ልክም ይሁን አይሁን ሌላ አማራጭ አለ ብሎ የሚያምን ባልደረባቸውን የሚያሳጡ፣ እንዲህ ያለ የትግል መንፈስ ያለውን ሰው ሲመቻቸው የሚያሳድዱ ሊያሸንፉት እንደማይችሉ የገመቱ ሰሞን አጋድመው እስኪያቆስሉት በደማቅ ሰላምታ ሊያዘናጉት የሚሞክሩ የትግል እንቅፋቶች ናቸው። በጥረት የማደግ ሳንካዎች።

በራስ ጥረት ማደግ በራስ እቅድ እና አቋም መመራት ያማቸዋል። ለእነሱ ነገን በራሳቸው ጥረት እንዴት እንደሚያሳምሩት ማሰብ የማይቻል ነው። ለአድርባዮች የራስን እቅድ ሳያሰልሱ ተግብሮ ማደግ እችላለሁ ማለት የዋህነት ነው።

የስም ማጥፋት ዘመቻቸው ደግሞ ሌላው ሁነኛ መሣሪያቸው ነው። አድርባዮች ልክ «ሎላ ካሬይሮ የቤላ ካላሚዳዴስ» ተከታታይ ፊልም ዋና ገጸባህሪ(የስፓኒሽ ሳጋ ፊልም ነውላይ እንደሆነው ይህን እና ያን እድገት ያገኛል የሚሉትን ጎበዝ ያለርህራሄ በማያቀው ጉዳይ ሲያጠለሹት የሚውሉ ጥቁር ቀለሞች ናቸው።

ይህንንም አስጸያፊ ተግባራቸውን ታዲያ ለመንግሥት ሥራ መሳካት፤ ለገዥው ፓርቲ እቅዶች ስኬት ካላቸው ተቆርቋሪነት አንጻር ያደረጉት ለማስመሰል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በቅጡ ለማያውቁት እና ለማያብራሩት ፖሊሲ ጠበቃም መሆን ያምራቸዋል። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አሉ– መነሻቸው የመሾም ርሀብ ሆኖ ሳለ።

እኒህ ሰዎች በጥረትና በብቃታቸው ብዙ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሰዎች ቶሎ ዕድሎችን አግኝተው የሚቻላቸ ውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ ከባድ መሰናክል ይፈጥራሉ። በእርግጥ ጀግኖች መንገዳቸው ቢረዝምም ትግላቸውን ዳር ከማድረስ ወደኋላ የማይሉ ቢሆንም።

በእርግጥ ሥራ አስኪያጅ ሲያዝ ያንን ትእዛዝ ተቀበሎ መፈጸም ይገባል። አድርባይ አለመሆን አሰሪ በተሰጠው ኃላፊነት ሥራዎችን ሊያሰራ ሲጥር እቅፋት መሆን እና መጨቃጨቅ ማለት አይደለም። ጠንካራ ሠራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በትጋት ፈጽመው ሲያበቁ ለውይይት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ግን የመሰላቸውን እና ያዋጣል ብለው የሚያምኑትን አቋም የማራመድ መብትም ኃላፊነትም እንዳለባቸው የሚያውቁ ናቸው።

በመሆኑም እንዲህ አይነቶቹ ጎበዞች በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን የማመንጨት ብቃት ያላቸው፣ በአማራጭ ሃሳቦች መቅረብ የሚያምኑ፣ ሃሳብን በተመለከተ ደግሞ ከሥራ አስኪያጃቸውም የተለየ ሃሳብ ማራመድን እንደ አንድ ማንኛውም የሃሳብ ልዩነት የሚወስዱ፣ ለኃላፊ ክብር መስጠት እንደሚገባ ያ ክብር ግን የተባለውን ሁሉ አሜን ማለትን እንደማይጨምር የሚያውቁ ናቸው።

ጨቅጫቃና ሰነፎች ግን አይደሉም ሥራን በሥራ ቦታቸው የሚረቱ የሃሳብ ትግል በሚደረግበት መድረክ ደግሞ የበሰለና መረጃጠገብ ውይይቶች መጫር የሚችሉ ናቸው።

አድርባዮች በእገሌ እንዳለው ጀምረው እገሌ እንዳለው እያሉ የሚጨርሱ የእነ እገሌን ሃሳብ መልሶ ከማብራራት እና ድጋፋቸውን ከማሳየት በዘለለ የሚጨምሩት ቁምነገር የላቸውም። አድርባዮች በአንድ ወቅት እንደማቃቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እገሌ እንዳለው ብሎ የሚጀምርን ሰው አንተ ሌላ ሃሳብ ከሌለህ በቀር የእሱን ስለሰማን እድትደግምልን እና ሰዓት እንድታባክን አይፈቀድልህም ሊባሉ የሚገባቸው ውስጠኦና ቃጭሎች ናቸው።

አድርባይ ቃሉ ራሱ ገላጭ ነው። ማደሪያውን ሊያመቻች ጥጋጥጉን የሚያስስ ጥገኛ ማለት ነው። ይበልጥ ደግሞ ሲብራራ አድርባይ የሌሎችን ችግሮች እንዲያዳምጥ እና እንዲያይ የተሰጡትን ሁለት ጆሮዎችና ዓይኖች የከደነ ውስጥ ውስጡን የሚበላውን የግል ስግብግብ መሻቱን ካልሆነ የጋራ በሆኑ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ የማይሰለፍ፤ እንዲያ ያለው ሥራ የሚጠይቀውን ብቃት ተግቶ የማይገነባና ሊገነባም የሚሻ ህሊናዊ ምርጫ የሌለው፤ ቀድሞ በአመለካከቱ ስብራት የከሰረ ሲለጥቅ በእዚህ ሰንካላ ምርጫው የተነሳ በተግባሩና በሥራዎቹ ብዙዎቹን ያለዕዳቸው የሚያቆሽሽ ነው።

የወገነለት ላስመሰለው አለቃውም ቢሆን በተባ እውቀት እና በተሳካ ተግባር ድጋፍ መሆን የማይችል ከመሆን አልፎ በምላሳቸው ውዛት ሳይሆን በህሊናዊ ብቃታቸውና በማያሰልስ ተግባራቸው የማገልገል አቅሙና ዝግጁነቱ ያላቸውን ሰዎች በተልካሻ የወሬ ፈጠራ እና አራጋቢነቱ የሚረብሽ ነው።

ታዲያ ምን ይጠበስለመሆኑ አድርባዩን እንዴት ከጨዋታ ውጪ ማድረግና ማረም ይቻላል?

መፍትሔው አድርባዮቹ ወሬ በማመላለስ የሚወስዱ ትን ብልጫ በመደበኛ መድረኮች እየተገኙ እግር በእግር ማክሸፍ እና መደበቂያ ዋሻ ማሳጣት ነው። ያን ማድረግ ሲቻል በወሬ ስልቻቸው መጠን ጥቅሞች የሚያገኙበት እድል እየጠበበ ሠራተኛ በጥረቱ ልክ ብቻ የሚለካበት አግባብ እየተፈጠረ ይሄዳል።

ለአድርባዮች መፋፋት ለሙ መሬት በጥረትና በሥራ የሚያምኑቱ ሰዎች ኩሩነት ነው። ቁምነገሩ ኩሩ መሆኑ ሳይሆን በብልሀት አሸናፊ መሆን መቻሉ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል። አለመልከስከስ አንድ ነገር ነው ልክስክሶች ካሸነፉህ ግን ኩራትህ የተሟላ አይሆንም። ስለሆነም አድርባዮች ሊፈነጩ የሚችሉበትን ሜዳ በየትኛውም ሕጋዊ አማራጭና ውይይት ማሳጣት የጎበዞቹና የባለምግባር ሠናዮቹ ፈንታ ነው።

እንዲህ ባለ የተጋጋለ የትጉሀን ትግልና አሰራር ባለበት መድረክ አድርባዮችም፣ አድርባዮችን ዙሪያውን ከቦ መፋፋት የሚፈልግ አለቃም ቢኖሩ እንኳ ያሻቸውን የማድረግ ዕድላቸው ጠባብ መሆኑ አይቀሬ ነው። በእንዲህ አይነቱ አውድ በሂደት ትጉሀኑና ባለምግባሮቹ በአሸና ፊነትና በመሪነት የሚወጡበት መሆኑ አይጠረጠርም።

ዳር ቆሞ አዬ አገራችን አድርባይ ይፈንጭብሽ ማለት በቂ አይደለም። መጀመሪያም ቢሆን ችግሩ ለአድርባዮች ሜዳውን መልቀቁ ነበርና። እናም በእኔ እምነት ለአድርባዮቹ ሁነኛ አጋጣሚ የፈጠረላቸው አድርባይነትን እጸየፋለሁ የሚለው አካል ከትግሉ ሜዳ ዘወር ማለቱ ነው።

አድርባዮች የሥራውን እና የለውጡን ትግል ሜዳ እንዳይዙት ዋነኛው መላ ሜዳውን መቆጣጠር ነው። ሜዳውን ወዲያው መቆጣጠር ካልተቻለም የተጋጋለ ትግል እያደረጉ በመቆየት የአድርባዮችን የተመኙትን የማድረግ አቅም ማኮሰስ ያስፈልጋል። ፈረንጆቹ ክፋት የሚንሰራፋው ደጎች ሜዳውን ለክፉዎች ሲተውትና የሚችሉትን ደግነት መፈጸም ሳይችሉ ሲቀሩ ነው ያሉት ይህንኑ ተገንዝበው ይመስለኛል።

ለአድርባዮች የምትተው አንዲት ጋት መሬት መኖር የለባትም። እያንዳንዱ ክፍተት አድርባዮቹ የበለጠ እጃችንን እንዲጠመዝዙ የሚያስችላቸው ይሆናልና። አድርባይ ሳይሆን አገልጋይ መንፈስና ልምድ ይኑረን።

**********

* Originally published on Addis Zemen, on March 14, 2013, titled “አድርባዮች አደጋዎች ናቸው“, authored by Zerihun Kassa.

Daniel Berhane

more recommended stories