Sendek | ከፒቲሽኑ ጀርባ ያለው ፖለቲካ

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በ2005 በመላ አገሪቱ የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤቶች አባላት ምርጫ ለማካሄድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ የሀገሪቱን ፖለቲካ ማሟሟቅ ጀምሯል። ቦርዱ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያመለክተው ከመጪው ሕዳር 14 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢ ምርጫዎች ላይ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማዕከል በቦርዱ ዋና ጽሕፈት ቤት ተገኝተው የመወዳደሪያ ምልክታቸውን መርጠው በመውሰድ ሂደቱን እንደሚጀምሩ ይፋ አድርጓል። ከህዳር 24 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የወረዳ የምርጫ ጽ/ቤቶች ተከፍተው ሥራ ይጀምራሉ ብሏል። በመቀጠል የመራጮችም የተመራጮችም ምዝገባ በሂደት ከተከናወነ በኋላ ሚያዚያ 6 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም ምርጫው ተካሂዶ፣ ግንቦት 2 ቀን 2005 አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ እንደሚሆንም ገልጿል።

ቦርዱ በዚህ መልኩ የምርጫ ሰሌዳውን ይፋ ቢያደርግም በተወዳዳሪ ፓርቲዎች በኩል የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና የምርጫ ውድድር ሜዳው የተስተካከለ አለመሆን፣ ከዚህ በፊት የተካሄዱ ምርጫዎች በአፈፃፀም ችግሮች የተተበተቡ መሆናቸውና እንዲሁም በየደረጃው ባሉት የምርጫ ቦርድ አመራርና አስፈፃሚ አካላት ተአማኒነትና ተቀባይነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

ጥያቄው የተነሳው ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ቦርዱ በ2005 ዓ.ም በሚካሄደው የአካባቢ (የአ.አ አስተዳደር፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ) ምርጫዎች የጊዜ ሰሌዳ ላይ እንወያይ ባለው መድረክ ላይ ነው። ቦርዱ ስለ ጊዜ ሰሌዳ ሲያወራ ፓርቲዎች ደግሞ በቅድሚያ የምርጫ ሜዳ ይስተካከላል ሲሉ ተነታርከዋል ማለት ይቻላል።

የፓርቲዎቹ ጥያቄ አዲስ ባይሆንም ጥያቄው የቀረበበት መንፈስና ትብብር ግን ለየት እንዲል አድርጎታል። በፓርቲዎቹ የቀረበው ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ ይዘት ያለውና ዋነኛው የሀገሪቱ ቁልፍ የፖለቲካ ጉዳዮችን ተብትበው የያዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ያካተተ ይመስላል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ከነበረው ልምድ አንፃር የፓርቲዎቹ ጥያቄዎች ገዥው ፓርቲ እንኳንስ ሊመልሳቸው ሊሰማቸው የሚፈልጉ አይመስሉም። ያም ሆኖ በጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ለስብሰባ ከመጡ 66 ፓርቲዎች መካከል 34ቱ በጥያቄው ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ፔቲሽን ተፈራርመዋል። ፔቲሽኑንም ከፈረሙ በኋላ ወደ 25 የሚሆኑ ፓርቲዎች በመድረክ ጽ/ቤት ተገኝተው በድጋሚ ተሰብስበው ሰባት አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰይመዋል።

ኮሚቴውን የሚመሩት የመድረክ ተወካይ በመሆን የቀረቡት አቶ አስራት ጣሴ ሲሆኑ ምክትላቸው ደግሞ የመኢአዱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ወንድማገኘሁ ደነቀ ናቸው። ለስብስቡ እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል የተባለው በቅርቡ የተመሰረተው ሰማያዊ ፓርቲ ሲሆን ከዚሁ ፓርቲ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈይሳ ተወክለዋል።

ይሄው የፓርቲዎች ስብስብ አርብ ጥቅምት 30 ቀን 2005 ዓ.ም በአንድነት ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በበተኑት አጭር ጽሁፍ ላይ ጥያቄአቸውን ይፋ አድርገዋል። በዕለቱ የፓርቲዎቹ መግለጫ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሚዲያዎችን ሳይቀር ትኩረት አግኝቶ ነበር።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ፓርቲዎቹ ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት መስተካከል አለባቸው ያሉዋቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል። ነጥቦቹ 14 ቢሆኑም ተጨምቀው ሲቀርቡ የሚከተለውን ይመስላል።

የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች፣ ታዛቢዎችና ጽ/ቤቶች በምርጫ ወቅት እንዳይሰሩ መደረጉ፣ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅትም ሆነ ከምርጫ ውጪ የመንግስትን ሀብት በተለይም ሚዲያ ለራሱ የምርጫ ማስፈፀሚያ እንዲውል ማድረጉ። ተቃዋሚዎች ከህዝቡ ጋር እንዳይገናኙ አዳራሽ መከልከሉ፣ ንቁ አባላትን ማዋከብና በሰበብ አስባቡ ማሰር፣ በእርዳታ መልክ የሚሰጡ እህልን መከልከል፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባል አርሶ አደሮች ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ እንዳያገኙ ማድረግና የነፃ ሚዲያ አባላትን በፈጠራ ወንጀል በማስር፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መታፈኑን የሚያመለክት ነው።

የፓርቲዎቹ ጥያቄ የተለመደ ቢመስልም አቀራረቡና የፓርቲዎቹ ቁጥር መበርከት ግን ሁኔታውን ለየት ያደረገው ይመስላል። የፓርቲዎቹ ስብስብ የምርጫ ቦርድን ጥሪ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተቀናጅተው ብለው ጥያቄውን እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል።

ከስብስብ ውስጥ አንዱ የሆኑትና 16 ብሔርብሔረሰቦችን በመወከል በደቡቡ ኦሞ ዞን መልካምድር የተመሰረተው የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኦሕዴሕ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ ስብስቡ በ1986 ዓ.ም ጊዮን ሆቴል ተካሂዶ በነበረው የተቃዋሚዎች የሰላምና እርቅ ኮንፈረንስ በኋላ የታየ ስብስብ እንደሆነ ነው የገለፁት።

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈይሳ የፓርቲዎቹ ስብስብ መፈጠሩ በብዙ መልኩ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ለሰንደቅ ጋዜጣ የገለፁት። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ነባራዊ ሁኔታ ባለመኖሩ ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስረዱት። ጥያቄውም ለቦርዱ የቀረበበት ምክንያት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚያስፈፅም ስለሚገደድ ነው። ነገር ግን የምርጫ ነባራዊ ሁኔታ በሌለበት ቦርዱ ምርጫ አስፈፅማለሁ ካለ የተለመደው ቴአትር ነው። ስለሆነም ጥያቄው ለቦርዱ መቅረቡ ተገቢ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ችግሮችን እያለባበሱ መጓዙ አደገኛ ውጤት ይዞ መምጣቱ ስለማይቀር ነው ብለዋል።

የጌዲዮ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አለሳ መንገሻ በበኩላቸው በዚህ ወቅት ፓርቲዎች በጋራ የመቆማቸው ጉዳይ ወቅቱን የጠበቀ እና ችግሩም ሲንከባለል ቆይቶ የመጣ ችግር ነው ብለዋል። ፓርቲዎች በተመሳሳይ በ2003 ዓም በመጋቢት ወር 50 የፖለቲካ ፓርቲዎች የ2002ቱ የድህረ ምርጫ ግምገማ የነበረውን የምርጫ ችግር ለይተው ለቦርዱ ቢያቀርቡም ተገቢ ምላሽ አለመገኘቱ ለአሁኑ ስብስብ መፈጠር ምክንያት መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች መሰባሰብ መቻላቸው የጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ምርጫ ለማካሄድ ብቻ ሳይሆን የዘወትር የፖለቲካ ስራ ለመስራት እንኳ የማያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክት በመሆኑ ስብስቡ ከዚህ በላቀ ደረጃ መንቀሳቀስ እንዳለበት ነው የጠቀሱት።

የአቶ አለሳ ፓርቲ በሽግግር ወቅት (በ1984 ዓ.ም) የቻርተር ም/ቤት አካል ከነበሩ ፓርቲዎች አንዱ የነበረና እስካሁንም በሁሉም ምርጫዎች ላይ የተሳተፉ በዋናነት በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው።

አዲሱ የፓርቲዎች ስብስብ የአካባቢ ምርጫን ምክንያት በማድረግ ነባርና ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ይዞ ብቅ ብሏል። ለ34ቱ ፓርቲዎች መሰባሰብ በቅርቡ የተመሰረተውና ለወጣቶች ቀዳሚ ሚና እሰጣለሁ የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክና መኢአድ አይነተኛውን ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ይነገራል።

ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ የሀገሪቱ ፖለቲካ የሽግግር ተቀያያሪ ባህሪ እያሳየ ባለበት በዚህ ወቅት በተቃዋሚ ካምፕ እየታየ ያለው የመሰባሰብ ፍላጎት የፈዘዘውን ፖለቲካ ሊያነቃቃው እንደሚችል እየተጠቀሰ ነው። ምንም እንኳ ፒቴሽን የፈረሙት ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ከሰርተፊኬት በስተቀር የራሳቸው ጽ/ቤት እና አባል ባይኖራቸውም ቀደም ሲል የተውትን መዋቅር እንደገና በማንቀሳቀስ በሁኔታው ሊነቃቁ እንደሚችሉ ይገመታል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ተፈጠሩት የጋራ መግባባት በቀላሉ ጥንካሬ ሊሰጣቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው።

የፓርቲዎቹ ስብስብ ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ የጋራ አቋም በመያዛቸው መድረክ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እና መኢአድ የተሻለ የፖለቲካ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ወትሮውንም ኢህአዴግ ድርድሩ መድረክ የማይፈልጋቸው መድረክና መኢአድ ሌሎች ፓርቲዎችን በማሰባሰብ በኢህአዴግ ላይ የፖለቲካ ጫና እንዲያሳድሩ ያስችላቸዋል እየተባለ ነው።

ኢህአዴግ በጋራ ምክርቤት ውስጥ የምርጫ 2002ቱን የስነ ምግባር ደንብ የፈረሙ ወደ ሰባት የሚጠጉ ፓርቲዎችን በመያዝ መቀጠል ይፈልጋል። ምንም እንኳ የስነ ምግባር ደንቡን የፈረሙት 65 ፓርቲዎች ቢሆንም ኢህአዴግ አባል በሆነበት ምክርቤት ውስጥ እንዲሳተፉ አልተደረገም። በም/ቤቱ እንዳይሳተፉ የተደረገው በዋናነት አደረጃጀታቸው ሀገር አቀፍ ባለመሆኑ ነው።

መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የስነ ምግባር ደንቡን አልፈረሙም። መኢአድ በደንዱ ላይ ቢፈርምም ከጋራ ም/ቤቱ በራሱ ፈቃድ ወጥቷል። ኢህአዴግ በ2002ቱ ምርጫ ወቅት ለፖለቲካ ጥቅም በሚመስል መልኩ 65 ፓርቲዎች በደንቡ ላይ እንዲፈርሙ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በመድረክ ላይ ሰፊ ቅስቀሳ ለማድረግ ተጠቅሞበታል። በአንፃሩ የስነ ምግባር ደንቡን የፈረሙት 65ቱ ፓርቲዎች ሰነዱን በመፈረማቸው ያገኙት የፖለቲካ ጥቅም አለመኖሩ ለአሁኑ ስብስብ መፈጠር በምክንያትነት መቅረቡ እየተነገረ ነው። ስለሆነም መድረክ፣ መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ በአንፃራዊነት የራሳቸውን ጽ/ቤት ከፍተው አባላትን አሰባስበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንደመሆናቸው ሌሎችን ፓርቲዎች በጋራ በሚያግባቡዋቸው ጉዳይ ማሰለፋቸው ሊናቅ የማይችል የፖለቲካ ጥቅም እያስገኘላቸው ነው።

አርብ ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተረጋገጠው ጉዳይ ቢኖር ፓርቲዎቹ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ወደፊት ገፍተው ለመሄድ መወሰናቸውን ነው። ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት የማያገኙ ከሆነም ከምርጫው እራሳቸውን ያገለሉ እንደሆነ በዕለቱ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ቀርቦላቸው ጥያቄዎቹ ካልተመለሱ በምርጫው አጃቢ ሆነው የመቀጠል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል።

ፓርቲዎች ያቀረቡዋቸው ጥያቄዎች የማይመለሱ ወይም መልስ ሳይሰጣቸው በዝምታ የሚታለፉ ከሆነ በምርጫው የመቀጠላቸው ነገር አጠራጣሪ መሆኑን የሚያመለክቱ ጉዳዮች አሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለዚህ ጉዳይ ሁለት ምክንያት ያቀርባሉ። የመጀመሪያው ፓርቲዎቹ በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ከምርጫው እራሳቸውን በማግለል ገዥውን ፓርቲ በፖለቲካ ለማሳጣት ይጠቀሙበታል። ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ የፓርቲዎቹን ጥያቄ ለይስሙላ ተቀብሎ ጊዜ በመግዣነት በመጠቀም የማታ ማታ አፍቃሪ ኢህአዴግ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር ምርጫውን ሊያካሂድ ይችላል የሚሉ ግምቶች ከወዲሁ እየተሰጡ ነው።
****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Nov. 14, 2012. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Daniel Berhane

more recommended stories