Sendek| የመጅሊስ ምርጫ ውጤት እንዲታገድ ተጠየቀ [Amharic]]

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

እየተካሄደ ያለው የመጅሊስ ምርጫ ሕገ-ወጥ በሆነ አካላት እየተከናወነ ስለሆነ የምርጫው ውጤት እንዲታገድ ተጠየቀ። እገዳው የተጠየቀው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በወከሏቸው ጠበቃ በቀረበ የፍትሐብሔር ክስ ነው። የኡላማዎች ምክር ቤት በበኩሉ 7.5 ሚሊዮን ሙስሊሞች የተሳተፉበት ምርጫ አይታገድም ብሏል።

በእስር ላይ የሚገኙት የኮሚቴ አባላት የወከሏቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት እየተካሄደ ያለው ምጫ ምርጫውን ለማካሄድ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው መጅሊሱና የኡላማዎች ምክር ቤት በመሆናቸው ውጤቱ እንዲታገድ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሰባተኛ ፍትሐብሔር ችሎት ክስ መመስረቱን አስታውቀዋል።

ሁለቱ ተቋማት በ1996 ዓ.ም በወጣው የመጅሊሱ ሕገ-ደንብ መሠረት በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እንዲካሄድና መጅሊሱ በሕዝብ ተመርጠው እንደሚመሩ ቢገልፅም፤ በደንቡ መሠረት ምርጫው እየተካሄደ ባለመሆኑ ውጤቱ እንዲታገድ በፍትሐብሔር ሕግ አንቀፅ 408 እና በሕገመንግስቱ አንቀፅ 28 መሠረት ክስ መቅረቡን ገልፀዋል። የክሱ ዝርዝር እንደሚያመለክተው ምርጫው ከመስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም በማድረግ መሆኑን አስታወሰ። ይህንን ለማሳገድ አቤቱታ በ22/01/2005 ዓ.ም ቀርቦ ነበር ብሏል።

ነገር ግን ምርጫው መደረጉ መቀጠሉና መገለፁ፤ በከሳሾችና በወከላቸው ህዝብ እንዲሁም በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ላይ ሊተካና ሊካስ የማይችል ጉዳት ያስከትላል ብሏል።

በመሆኑም ይህ ክርክር የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ በተከሳሾች በኩል እየተደረገ ያለው ምርጫ እንዲቆም (እንዳይካሄድ) እና የተደረገውም ውጤቱ እንዳይገለፅ (ውጤቱ ስራ ላይ እንዳይውል) ታግዶ እንዲቆይ እንዲታዘዝልን ሲሉ ጠይቀዋል።

የኡላማ ም/ቤት አማካሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ረሺድ የምርጫው መታገድ በተመለከተ እሳቸውም የኡላማዎች ምክር ቤት እራሱን የቻለ ተቋም እንጂ ለመጅሊሱ ተጠሪ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም ምርጫውን ለማካሄድ እንደሚችል በመግለፅ 7.5 ሚሊዮን ሙስሊሞች የተሳተፉበት ምርጫ አይታገድም ብለዋል።

“የተካሄደው ምርጫ የፓርቲ ወይም የፖለቲካ ሳይሆን የሃይማኖት መሪዎች ምርጫ ነው” ያሉት አቶ መሐመድ ምርጫው ይታገድ፣ ውጤቱም አይገለፅ የሚለው ክስ ሕጋዊ መሠረት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

የኡላማዎች ምክር ቤት በሕዝበ-ሙስሊሙ የተቋቋመ፣ በዓለማዊ ትምህርት እስከ ፕሮፌሰርነት የሚደርሱ ባለሙያዎች ያሉበት ተቋም መሆኑን ያስታወሱት አቶ መሐመድ የኡላማዎች ም/ቤት የሕግ አውጪነት መጅሊሱ ደግሞ የአስፈፃሚነት ሚና ያለው በመሆኑ አንዱ ሌላኛውን ይቆጣጠራል እንጂ የተጠሪነት አሰራር የለም ብለዋል።

የምርጫ ውጤት በፍፁም ሊታገድ አይገባም ያሉት አቶ መሐመድ በ870 የምርጫ ጣቢያዎች 7 ነጥብ 5 ሙስሊሞች በቀበሌ በተካሄደው ምርጫ ተሳትፈውበታል ብለዋል። ይህም 18 ዓመት ከሞላቸውና አጠቃላይ ሙስሊሞች ቁጥር 1/3ኛውን የሙስሊም ቁጥር የሚሸፍን እንደሚሆን ጠቅሰው በቀበሌ 1/3ኛው ሙስሊም ወጥቶ የመረጠውን ምርጫ አንዋር መስጊድ ብቻ በሚደረግ ተቃውሞ ሊቀለበስ አይችልም ሲሉ አስረድተዋል።

ምርጫው የተካሄደው በ1996 ዓ.ም መጅሊሱ ባወጣው ሕገ-ደንብ ሳይሆን የኡላማዎች ም/ቤት ባሻሻለው የምርጫ ማንዋል መሠረት መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድ ማንዋሉ አራቱን የእስልምና መርሆዎች የተቀበለና ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሙሰሊም እንዲሳተፍ ያደረገ የምርጫ ማንዋል መሆኑንም አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ “ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተታሎ ነው የመረጠው” የሚለው አባባል ተቀባይነት እንደሌለው የጠቀሱት አቶ መሐመድ 7.5 ሚሊዮን ሕዝብ እንዴት ሊታለል ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል። 7.5 ሚሊዮኑም መራጭ በራሱ ፈቃድ ወጥቶ ተመዝግቦ መምረጡንም ያስታወሱት አቶ መሐመድ በአንፃሩ በየመስጊዱ የሚቀርበው ተቃውሞ አያሳስባችሁም ወይ? ለተባሉት ሲመልሱ፤ “በመጀመሪያ ተቃውሞ የሚታየው በአንዋር መስጊድ እንጂ በሌሎች መስጊዶች አልታየም። ስለሆነም የአንዋር መስጊድ የኢትዮጵያ መስጊዶች መቶ በመቶ ይወክላል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ያም ሆኖ ምርጫው ላይ ሰዎች በመሰላቸው መንገድ ሄደው ሊቃወሙ ይችላሉ ብለዋል። መቃወማቸውም ለምርጫው ሂደት ጥንካሬ ይሰጣል ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

ቀደም ባለው መጅሊስ በሙስና የተዘፈቁ ግለሰቦች በአሁኑም ምርጫ እንዲሳተፉ ተደርጓል የሚለውን ቅሬታ በተመለከተ ተጠይቀው አቶ መሐመድ ሲመልሱ በተሻሻለው የምርጫ ማንዋል ሙስሊም የሆነ ሰው በምርጫው እንዲሳተፍ ይፈቅዳል ካሉ በኋላ በሙስና መጠርጠርና በሙስና የተፈረደበት ሰው ይለያያል ብለዋል። ከዚህ ባሻገር በቀድሞ መጅሊስ በሙስና የተጠረጠሩ ካሉ ማኅበረሰቡ በቀበሌ ደረጃ የግል ጣባያቸውን መሻሻል አይቶ ቢመርጣቸውም ወደ ላይ እየተጣሩ ስለሚመጡ ከዞን ላያልፉ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

****************

*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 17, 2012, titled “የመጅሊስ ምርጫ ውጤት እንዲታገድ ተጠየቀ”, authored by Zerihu Mulugeta. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the Ethiopian Muslims archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories