የመድረክ አመራሮች ቃለመጠይቅ | ‘ከብርሃኑ ጋር ተገናኝቻለሁ – መብቴ ነው’ መረራ ጉዲና | Medrek party leaders

የ‹መድረክ› ፓርቲ አመራር አባላት ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 22/2003 በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ማውጣታቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ‹መድረክ› – ወይም በሙሉ መጠሪያው ‹የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ› – የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ሲሆን ከዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም 5 የ‹መድረክ› አመራር አባላት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ነበራቸው፡፡

ይሁንና የጋዜጣዊ መግለጫውን ሆነ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ሙሉ ይዘት ለማግኘትና እዚህ ብሎግ ላይ ለማተም ያደረግሁት ጥረት እስከአሁን አልተሳካም፡፡ ሆኖም Addisnegeronline ‹የመድረክ ፓርቲ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ› በማለት የተመረጡ(excerpts) ክፍሎችን አትሟል፡፡ ከድረገጹ የፖለቲካ አሰላለፍ አንፃር የመድረክ አመራሮችን ሀሳብ አዛብቶ (misrepresent) ያቀርባል ብሎ የማይገመት ከመሆኑም በላይ ፤ የቃለ-ምልልሱን አንኳር ክፍሎች ለመለየትም ብቃቱ አለው፡፡ በመሆኑም ዘገባውን ሙሉ በሙሉ ከዚህ በታች አትሜዋለሁ፡፡ (on permission)

በነገራችን ላይ ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹ በጀርመን አገር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከኤርትራ የደኅንነት አማካሪ አቶ የማነ ጋራ ተገናኝተው ተወያዩ › ተብሎ ስለወጣ ዘገባ የተናገሩትን የተወሰነ የሀሳብ መፋለስ የሚታይበት ቢሆንም ‹ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ … ጋር ተገናኝቻለሁ – ይኼ ደግሞ መብቴ ነው› ያሉት ትክክል ነው፡፡ ወሬው እሳቸውን ለማሸማቀቅ ተብሎ ከሆነም አግባብ አይደለም – ዜናው ግን ዜና ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ በወንጀል የተፈረደባቸው ቢሆኑም ከሳቸው ጋር መገኛኘት ወንጀል አይደለም፡፡ ከኤርትራው አመራር ጋር መገናኘትም በራሱ አያስጠይቅም፡፡ ጠ/ሚኒስተሩም ቢሆነን ከኦነግ አመራሮች ጋር በ2005 መገናኘታቸውን ከአንድ ዓመት በኋላ ፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እርግጥ ዓላማቸው ኦነግን ወደ ሰላም ለማምጣት ነው፡፡ ታዲያ ዶ/ር መረራ ከዶ/ር ብርሀኑ ጋር ሴራ እንደዶለቱ የሚገመትበት ምክንያት የለም፡፡ የዚህ ምንጩ ‹የእኔ ሀገራዊ ስሜት ከሌላው ይበልጣል› የሚልና ሌላውን ተጠርጣሪ አድርጎ የማሰብ/የማውራት አባዜ ነው፡፡ ከዚህ ደግሞ ራሳቸው ዶ/ር መረራም የፀዱ አይደሉም፡፡ በዚያው በቃለ-ምልልሱ ጥሩ ሄደው ሲያበቁ ‹ በየትኛውም ሚዛን እኔ ወደ ሻዕቢያ አልቀርብም › የሚል የአግቦ ውንጀላ በመሰንዘር ያንኑ ስህተት አንፀባርቀል፡፡ የሻዕቢያ አጀንዳ ኢትዮጲያን ማተራመስ እንደመሆኑ ማንም ኢትዮጲያዊ ለሻዕቢያ የተለየ ቅርበት ይኖረዋል ተብሎ መገመት አይኖርበትም – ቢያንስ circumstantial evidence ከሌለ፡፡ (በሌሎቹ አመራሮች ላይ የሚወያዩ ነጥቦች ቢኖሩም፤ አስፈላጊ ከሆነ በሌላ ጽሁፍ የምመለስበት ይሆናል፡፡)

በመድረክ ስር ያሉ የፓርቲ ተወካዮች ከጋዜጠኞች ጋራ ያደረጉት ወቅታዊ ቃለ ምልልስ | Addis Neger (link)

የኢትዮ- ኤርትራ የድንበር ግጭት ወደ ጦርነት ይሸጋገራል ወይስ አይሸጋገርም የሚል ግምት አዘል ትንታኔ በተመለከተ :-

አቶ ገብሩ ዐሥራት
“እኛ ሻዕቢያ አዲስ አበባን ወደ ባግዳድ ለመለወጥ የሚያስችል አቅም አለው ብለን ፈጽመን አናምንም። ይኼ ነገር የሚወራው የሕዝቡን የአስተሳሰብ አቅጣጫ ለመለወጥ በሚደረግ ስልት ተመስርቶ ነው ብለን እናምናለን። ሰው በፍርኀት ድባብ እንዲዋጥ እና ሌላ ነገር እንዳያስብ ኢትዮጵያ ለካ ትፈርሳለች፤ አዲስ አበባም እንደ ባግዳድ እና ሌሎች ከተሞች ትተራመሳለች ብለው በሥጋት እንዲዋጡ በማድረግ ባሉት መሠረታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉድለቶች፣ የኑሮ ውድነት እና በዲሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ላይ እንዳያተኩር ኾነ ተብሎ አቅጣጫ ለመለወጥ የሚደረግ መግለጫ ነው ብለን ነው የምናምነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰጡት መግለጫ አለ፣ በተለይም በትግርኛ። አሰና ለተባለው የኤርትራውያኖች ሚዲያ የተሰጠው መግለጫ ደግሞ ከኤርትራ ጋራ በሰላም አብረን ለመኖር እንፈልጋለን። እንዲያውም “እኛ የወሰድነው መሬት እኔ የማውቀው አለ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኤርትራ የኾነ እኔ የማውቀው ለኢትዮጵያ ተሰጥቷል። ይኼን ከባድመ ጋራ እንለዋወጥ እና አብረን በሰላም ለምን አንኖርም የሚል ነው ጭብጡ። ይኼ ከሕግ አንጻርም የሚያስጠይቅ ነው። በዚህ አገር መጠየቅ የለም እንጂ። አንድ መንግሥት የራሱ ያውም ዳኛ የሰጠውን መሬት የእኔ አይደለም ብሎ ሲናገር እስከ ምን ድረስ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደኾነ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።

ሻቢያ የፀጥታ ችግር እየፈጠረ ነው። ነገር ግን ከፀጥታ ያለፈ ችግር፤ አገርን ለማተራመስ የሚችል እንቅስቃሴ ግን አላየንም። ይኼ የሚኾንበትንም ኹኔታ አናይም። የሕዝብን አቅጣጫ ለማስለወጥ እና እኔ ከሌለሁ እና ካልጠበቅኳችሁ ይቺ አገር አትኖርም የሚለውን ሐሳብ ለማሳለፍ የታለመለት ሐሳብ ነው። ግን እንደምንም ኾኖ ጦርነት ቢነሳ የእናንተ አቋም ምንድን ነው የሚኾነው ለሚለው ያኔ የሚታይ ይሆናል። የጦርነቱን አጀማመር እና አካሄድ በመመልከት ያኔ ነው አቋም የምንወስድበት እንጂ ከወዲሁ አቋም አንይዝም።

ዋናው ነገር ግን እኛ የአገሪቱ ጥቅም እንዲከበር ነው የምንፈልገው፡፡ ከኤርትራ ጋራ የሚደረገው ድርድርም ይኹን ጦርነት የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር አለበት። በተለይ በፕሮግራማችን ያስቀመጥነው የባህር በራችንን በሚያስከብር መልክ መቋጨት አለበት። የኾነ ድርድር፣ የኾነ ክርክር፣ የኾነ ኖርማላይዜሽን የሚሉትን ነገር የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብርበት መንገድ መሄድ አለበት ብለን እናምናለን።

ስለ ዋጋ ንረት እና በአባይ ወንዝ ላይ ይሰራል ስለተባለው ግድብ –

አቶ ገብሩ ዐሥራት፦

እኛ ባለፈው “የታመመ ፖለቲካ የታመመ ኢኮኖሚን እንጂ ሌላ ሊያመርት አይቻለውም” በሚል ባወጣነው ጋዜጣዊ መግለጫ ኹኔታውን ቀደም ሲል አሳውቀን ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በደፈናው መድረክ የዋጋ ተመኑን እና ቁጥጥሩን ተቃወመ ብሎ ፍሬ ሐሳቡን ሳያቀርብ አዛብቶ በአሉታዊ ድምፀት ዘገበ። ይህ በጣም የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነው።

አሁን በዋጋ ቁጥጥር ምክንያት በአገሪቱ ብዙ ሸቀጦች ጭራሽ እንዲጠፉ ኾነዋል። ዘወትር ማታ ማታ ትርፍ ምርት አለ፣ በበቂ አስገብተናል እየተባለ በመንግሥት ቢነገርም ስኳር፣ ዘይት እና ሌሎች ሸቀጦች ከገበያ እየጠፉ ነው ያሉት፡፡ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በርካታ ነጋዴዎችም እየታሰሩ ነው፡፡ ይሄ መፍትሄ አላመጣም፡፡ እኛ መፍትሄ ያመጣሉ ብለን የምናስባቸው ነገሮች ባለፈው መግለጫ ላይ አንስተናቸዋል፤ አሁን ይኼን መዘርዘር ጥቅም የለውም፡፡ ዋናው ነገር መንግሥት ከሕዝቡም፣ ከነጋዴውም ጋራ ተነጋግሮ የመፍትሄ ሐሳቦች በዚች አገር የፖለቲካ መግባባት እና የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎች በመቅረጽ እንጂ በአዋጅ የሚፈታ ነገር የለም የሚል ነው የመግለጫው ጥቅል ሐሳብ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፡-
ኢሕአዴግ ጋራ የተዛመወይም የኢሕአዴግ ንብረት የኾኑ የንግድ ድርጅቶች (ቢዝነስ ኢምፓየር) አሉ የሚለውን ጉዳይ ይዘን ከተንቀሳቀስን ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሕዝብም በግልጽ ያውቀዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዝርዝሩን ይዞ አንድ መጽሐፍ እንደተጻፈም አውቃለሁ፡፡ ከዛሬ 10 ዓመት በፊትም አንድ ቡክ ሌት እንደወጣ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ይኼንን ሥራ ለምርምር ጋዜጠኝነት የሚተው ይመስለኛል፡፡

ኢሕአዴግ መጀመሪያ ይኼን ሲክድ ነበር፡፡ በኋላ ግን መካዱ አላዋጣ ሲለው ኢንዳውመንት ነው አለ፡፡ በትግሉ ወቅት ብዙ ሚሊዮኖች ገንዘብ በእጃችን ገብቶ ስለነበር ያንን ምን እናድርገው ተከፋፍለን እንግባ ወይስ ምን እናድርግ ብለን በአንድ ዐይነት በሚለማበት ኹኔታ እናስቀምጠው ብለን ገባንበት ለማለት መገደዳቸውን ማውሳት እወዳለሁ፡፡ እናም ከኻያ የሚበልጡ ትልልቅ ባለ ብዙ ሚልዮን ካፒታል ያላቸው ድርጅቶች ለዚህች አገር ካዝና የማይገባ እና ለአገሪቱ ሪፖርት የማይደረግበት በጎንዮሽ የሚሄድ ሁለት ዐይነት ኢኮኖሚ እዚህ አገር እንዳለ፤ እነዚህ ኩባንያዎች ፋይናንሳቸውን ሲያሠሩም ሪፖርት የሚያደርጉት የበላይ ተቆጣጣሪያቸው ለኾነው ፓርቲያቸው ነው፡፡ ለህወሓት ወይም ለኦህዴድ ወይም የደቡቡም እንደው ለስሙ ያህል ጥቃቅን ያላቸውም ለእነዚህ ለፓርቲዎቻቸው ነው ሪፖርት የሚያደርጉት፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አካውንቲንግ ሲስተም ወይም ዋና ተቆጣጣሪ ኦዲተር አያውቃቸውም፡፡

ይህ በጎንዮሽ የሚሄድ ሁለት ዐይነት ኢኮኖሚ ነው። ይሄ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተለይ የነጻ ገበያ የሚባለውን እንዳይጎለብት ተጽዕኖ እያሳረፈበት ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲ ጋራ ግንኙነት ያለው በተዘዋዋሪም ቢኾን የገዢው ፓርቲ ንብረት የኾነ ይጠቀማል፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሕግ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ንብረት ምን ይላል ብለን ስንመለከት በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ በንግድ ሥርዐቱ ውስጥ አይገባም ነው የሚለው፡፡ ሀብት ወደ ማካበት አይገባም ነው የሚለው፡፡ ኢሕአዴግን በዚህ ጉዳይ በምርጫ ክርክር ላይ በተደጋጋሚ ቻሌንጅ አድርገነዋል፡፡ ይህ ንብረት ወይ የሕዝብ ንብረት መኾን አለበት አለበለዚያም ወደ ነጻ ገበያው መተላለፍ አለበት፡፡

ሌላው በዐባይ ተፋሰስ ላይ ግድብ ለመሥራት አቅደናል የሚል ፈረንጆቹ ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ የሚሉት (ሰበር ዜና) ዐይነት ትላንት አድምጠናል፡፡ ይህ ድሮውንም ቢኾን የኢትዮጵያ መብቷ ነው፡፡ የአገሪቱ ሀብት ለዜጎቿ ጥቅም መዋል አለበት፡፡ ይኼ ምን ሊያስነሳ ይችላል ተብሎ ዝም ብሎ በፍርኀት ተቀፍድዶ የአገር ሀብትን ሳይጠቀሙበት ቀርቶ መራብ እና መጠማት ተገቢ ነው ብዬ እኔ አላምነም፡፡ ነገር ግን የኢሕአዴግን አካሄድ ብዙ ጊዜ መተንበይ ያስቸግራል። ከዚህም አንዱ ማታ ያየኹት የዚህ ፕሮጀክት ኹኔታ ነው፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና ”በአንድ ወቅት በፓርላማ ቆይታዎ የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል ያሉት ነገር ትንቢት ነው ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ

ዶ/ር መረራ ጉዲና
እንደ ትንቢት ቢወሰደልኝ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን በአንዳንድ አገሮች የሚታየው ይኼው ስለኾነ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ከታሪክ እና ከፖለቲካ አስተውሎት በመነሳት የተናገርኩት ነው፡፡ መሪዎች እነርሱ ኬክ እና ጮማ ስለሚበሉ የሚገዙት ሰውም እንዲሁ ያንኑ የሚበላ ስለሚመስላቸው እንደ ፈረንሳይዋ ንግስት ዳቦ ተርቦ ለወጣ ሕዝብ ዳቦ ከሌለ ለምን ኬክ አይበሉም ይላሉ፡፡

ኢሕአዴግ ፓርላማ ውስጥም ይኼ የ11፣ 12፣ 13፣ 14 በመቶ ዕድገት በተደጋጋሚ ሲለፈፍ ሕዝብ እየተራበ መሆኑን የማይበላውን ባዶ ተስፋ እና መቀለድ እንደማይጠቅም ኢሕአዴግን መምከሬ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የዚያን ጊዜ ምክሬን ተቀብሎ ቢኾን ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ቢዘገይም ዛሬም ቢቀበለኝ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የተራበ ሕዝብ ብዙ አማራጮች ላይኖሩት ይችላሉ፡፡ ይኼ በሌሎች አገሮችም የታየ ነው፡፡

እስከ አሁን ድረስ ያለው የሰው ልጅ ታሪክ በተለይ ያለፉት ሁለት እና እና ሦስት መቶ ዓመታት የሚያሳየው ያንን ነው፡፡ ኢሕአዴግም ይኼን ተረድቶ ለሕዝብ ብሶቶች እና ችግሮች በፍጥነት በተለይ የዳቦ ጥያቄን ለመመለስ ቢንቀሳቀስ ጥሩ ነው፡፡ ካድሬ እና ካቢኔ ማብላቱ፣ መቀለቡ እና ማደለቡ ብዙ ላይጠቅም ይችላል የሚለውን ምክር እንዲሰሙ ነው (እዚያ ፓርላማ በብዛት ያሉት እነርሱ ስለኾኑ) እንደው ይሰሙ ይኾናል በሚል ነበር የተናገርኩት፡፡ ግን እንደ ትንቢት ቢወሰድልኝ አልጠላም (በፈገግታ)፡፡ ዋናው ጉዳይ ከታሪክ መማር መቻል እና አለመቻል ነው፡፡

“በጀርመን አገር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከኤርትራ የደኅንነት አማካሪ አቶ የማነ ጋራ ተገናኝተው ተወያዩ ተብሎ በኢትዮ ቻናል ተዘግቦ ነበር”

ወደ ጀርመን ፓርላማ የሄድኩት ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ታውቃለህ ተብዬ በኤክስፐርት ደረጃ በመጋበዜ ነው (የጥሪውን ወረቀት እያሳዩ)፡፡ ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በሰብአዊ መብት ላይ እንዳስረዳቸው ነበር እኔንም ኾነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች በጀርመን አገር የሚኖሩ ዜጎችን የጋበዙን፡፡

እዚህ ፕሮግራም ላይ ልቀር አስቤ ነበር፤ ያልቀረሁት ኢሕአዴግ በሠራው ኹኔታ ነው፡፡ አባሎቻችንን በብዛት ማሰር ሲጀምሩ እንዲህ ዐይነት መድረኮችም ላይ ሄዶ አቤት ማለት ይጠቅማል ብዬ ነው፡፡ እኔ እንደውም ፈራ ተባ እያልኩ ስቀልድ የነበረው ዐባይ ወደ ታች ይፈሳል እንጂ ወደ ላይ አይፈስም እያልኩ ነው ስቀልድ የነበረው፡፡ የግብፅን ወቅታዊ የፖለቲካ ኹኔታ እና ሕዝባዊ መነቃቃትን በተመለከተ በማነሳት ለማለፍና ለማምለጥ ስሞክር የነበረው፡፡ ግን አባሎቻችን መታሠራቸው እንደ ጀርመን ያሉ ትልቅ የአውሮፓ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ስለሚያሳርፉ ለማሳወቅ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ እዚህ መጥተው ተቃዋሚዎችን በደንብ ስላላናገሩ በፓርላማ እና በአስተዳደር መካከል ባለ የኢትዮጵያ ጥያቄ ላይ የልዩነት ሐሳብ ስለነበር እርሱን እንዳብራራላቸው ነበር፡፡

እናም የዚያኑ ቀን ማታ ውይይት ነበር፣ አንድ የጀርመን ፓርላማ አባል እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚሳተፍበት፡፡ ለምሳሌ እዚህ ውይይት ላይ አልሄድኩም፡፡ ምክንያቱም አሁን ኢሕአዴግ በኢትዮ ቻናል ጋዜጣ የሠራውን የፎቶግራፍ ቴክኒክ እንዳይሠራ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊትም በእኔ ላይ እንዲህ ዐይነት ነገር ሠርተው ነበር፡፡ በዚህ ላይ መድረክ ያላሰበበት እና ያልወሰነበትን ነገር አላደርግም ብዬ ነበር ያልሄድኩት፡፡ ግን ከዕሻቢያ መሪ ጋራ የሚያገናኘኝ ነገር ከየት እንዳመጡ ኢሕአዴግ ነው የሚያውቀው፡፡ ከዚህ በፊትም ትዝ ይለኛል ለኤ.ኤፍ.ዲ በኅብረት ሥም ደብዳቤ ጽፈኻል ብሎ ስካን የተደረገ ደብዳቤ አምጥቶ ሰጥቶን ነበር፤ ያልጻፍኩትን እና ያልፈረምኩትን ደብዳቤ ማለት ነው። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች አገር የሚመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዐይነት ድርጊት ለእነርሱም፣ በኢሕአዴግ ለሚመሩት ጋዜጠኞችም ኾነ ለአገርም አይጠቅምም፡፡

እናም በጀርመን ፓርላማ እንደኔ ከተጋበዙ ሰዎች አንዱ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነው፤ ከእርሱ ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ ይኼ ደግሞ መብቴ ነው፡፡ የጀርመን ፓርላማም ማንንም የመጋበዝ መብቱ የጀርመን ፓርላማ እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ ለማንኛውም በእኔ እውቀት ደረጃ ስላለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኹኔታ አስረድቻለሁ፡፡ የኤርትራ መሪ የሚባለው ሰው ማን ይኹን ማን ኢትዮ ቻናል ላይ ወጥቷል ሲባል አዚህ ከመጣሁ ነው የሰማሁት፡፡ ሰው ያላደረገውን አድርጓል፣ ያላሰበውን አስቧል ማለት ምን አልባትም ሰው ያላሰበውን ማሳሳብ ይኾናል፡፡ በየትኛውም ሚዛን እኔ ወደ ሻዕቢያ አልቀርብም፡፡

ሙስና ጉዳይን በተመለከተ፡-

(ዶ/ር መረራ ጉዲና)

የኦሕዴድ የሙስና ጉዳይ የፖለቲካ አንድምታ ይኑረው አይኑረው ርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለመንግሥት በደንብ ካልተላኩ የፖለቲካ አንድምታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በፊትም እንደተናገርኩት እየታሠሩ ያሉት ትንሽ ዓሶች ናቸው ወይስ ትልልቆቹም ዓሶች አሉበት፡፡ እኔ እስከገባኝ ጊዜ ድረስ ትንንሾቹ ዓሶች እየታሠሩ ናቸው፤ ትልልቆቹ ዓሶች ግን የተነኩ አይመስሉም፡፡ ይነካሉ አይነኩም የሚለውን ኢሕአዴግ ነው የሚያውቀው፡፡ መሬት የቸበቸቡ፣ በድንጋይ ስም፣ በሞተ ሰው ስም፣ በእንጨት ስም በምን ስም ማኅበር ሠርተው መሬት በአዲስ አበባ አካባቢ ሲሸጡ እንደ ነበር ደኅንነቱም ያውቅ ነበር፡፡ ይኼን ፓርላማ ላይም አንስተነው ነበር፡፡ ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ ፣በዱከም መሥመር እስከ አዳማ ድረስ መሬት ላለፉት ስንት ዓመታት ይቸበቸብ ነበር፡፡ አባሎቻችን ሁሉ በዚህ በተቸበቸበ መሬት ነው ሲገዙ የነበሩት፡፡ እንግዲህ ትልልቆቹ ዓሶች እስከ አሁን አልተነኩም፣ ትልልቆቹ ዓሳዎች ሲባል እስከ የት ድረስ ነው የሚጠየቁት፣ ዋናውስ ጉዳይ ሙስና ነው? ርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ዶ/ር ሞጋ ፉሪሣ (የኦፌዴን ሊቀመንበር)፡-

በኦሮሚያ ስለታሠሩ በርካታ ሰዎች ሊስቱን ይኸው ይዘናል፡፡ ለምንድን ነው ኦሮሞዎች ዛሬ በገፍ የሚታሠሩት እስቲ እናንተ ጋዜጠኞች መርምራችሁ ድረሱበት፡፡ እስራቱ ለምንድን ነው ኦሮሞ ላይ ያተኮረው፣ በርግጥም ሌላውም እየታሰረ ነው፤ ለምን ኦሮሞ ላይ በረታ? እኛን ግራ ገብቶናል፡፡ አሁን ፓርቲያችን በኦሮሚያ በኀይለኛ ኹኔታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ብዛት ያለውን ሕዝብ ማጥቃት እና ጉዳት ማድረስ ምን ይሉታል? ምናልባት መንግሥት ቀድሞ እንደሚያደርገው አንዳንድ ልዩ ታርጋ ኦሮሞ ላይ ለመለጠፍ ስለሚቀለው ይኾናል፤ ኦነግ- የኤርትራ ተላላኪ ምናምን፡፡

እነዚህ ሰዎች ስለመብታቸው፣ ስለማንነታቸው፣ ስለ እውነት ከመነጋገራቸው ውጪ የሠሩት ወንጀል የለም። ሕዝቦቻችን፣ አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን የሰላም ሰዎች ናቸው፡፡ በተለይ አሁን እየታሰሩ ያለበት ጊዜ የዓመት እህላቸውን የሚያርሱበት የእርሻ ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ታስረው ዓመቱን ሙሉ ቤተሰባቸውን ምን ሊቀልቡ ነው፡፡ በቆሎ እና ገብስ አሁን ነው የሚዘራው፡፡ ዛሬ ታሰሩ ነገ ደግሞ ልመና ልንሄድ ነውን? የዝናም እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት እና አገሪቱ በተራበችበት ጊዜ፣ ሕዝብ በተራበበት ወቅት ሠርተው እንዳይበሉ ማሰሩ ማንን ነው የሚጠቅመው? በተለይ በአካባቢው ብዙ ተሰሚነት ያላቸውን ሽማግሌዎች ስንቅና ጠበቃ ሊያገኙበት በማይችሉት ቦታ አርቀው እያሰሯቸው ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ሊገባን አልቻለም? እኛን ቀርበው ስላናገሩ ምን የነካው እንጨት እንደሚባለው ነው ያደረጓቸው፡፡

በዚህ ላይ እስራቸው ከገንዘብ ቅጣት ጋር ነው፡፡ 5 ሺሕ፣ 3 ሺሕ፣ እና 150 ብር የተቀጡ አሉ፡፡ ይኼ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም መሬታችንን አንለቅም በማለታቸው ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ማንም የማይጠቀምበት መሬትን ነው ለውጪ ኢንቨስትር የምሰጠው ብሏል፡፡ እስቲ አስቡት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደው የትም ቦታ ቢኾን አገሩን ጠብቆ ወገኑን አቅንቶ የጠበቀ ሕዝብ የራሱ መሬት አለው፡፡ በሶማልያ ክልልም፣ በጋምቤላም በአፋርም፣ ኾነ በሌሎቹ እነዚህ ዜጎች የአገር ድንበርን ጠብቀው የቆዩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለቤት የሌለው መሬት የለም፡፡ ለእርሻ ይውላል፣ ለከብት ርቢ ግጦሽ ይውላል፣ እያፈራረቁ በሂደት ያርሱበታል፤ ስለዚህ ነጻ የሚባል መሬት የለም፡፡ ባለቤት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ባለቤቱ፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይወያይና ሳይነጋገርበት ለውጪ ሰዎች አሳልፎ መሸጥ ምን ማለት ነው? ይኼ መሬት በኢትዮጵያውያን ሥር ከሌለና ባዕድ ከወረረን በኋላ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የለችም፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር)፡-

የሰሜን አፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ዐይነት ሕዝባዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያም ሊከሰት የሚችልባቸው ኹኔታዎች አሉ ወይስ ጥሪዎች አሉ የሚለው ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ኹኔታዎች ከእነዚህ የዐረብ አገራት የባሰ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ኹኔታ የሕዝብ እንቅስቃሴ ሊጀመር ይችላል ወይ ለሚለው ጊዜው በማን እንዴት እንደሚጀምር ባይታወቅም ሊነሳ ይችላል፡፡ መቼ እንደኾነ ግን አናውቅም፡፡

ሕዝብን ለማነሳሳት ጥሪዎች አሉ ወይ ለሚለው ወጣቱ የእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታ ማንቼን ትቶ አልጀዚራን፣ ፕረስ ቲቪንና ቢቢሲን መከታተል ጀምሯል፡፡ ይኼን ሁላችንም እየተመለከትን ነን፡፡ ወጣቱ ከማንቸስተር ኳስ ወደ አልጀዚራ ዞሯል፡፡ ይኼ ምን ዐይነት ስሜት እንደሚፈጥር እና ነፋሱ ወደ እኛ መቼ ነው የሚነፍሰውን በሰው አእምሮ ውስጥ ሊያስጀምር ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከአገር ውጪ ያሉ የዲያስፖራ ጥሪዎች አሉ፡፡ ከእነርሱም ጋር ብዙ ኮሙንኬሽን አለ፡፡ በነገራችን ላይ በ1966 ዓ.ም (1974 እ.ኤ.አ) የንጉሡን አገዛዝ ለመጣል ኅብረተሰቡ ትግል ሲያካሂድ በወቅቱ ምንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አልነበሩም፤ ሕዝቡ ነው አብዮቱን የመራው፡፡

የዚህ የሰሞኑ የገፍ እስር ጉዳይ በኦፌዴን እና በኦህኮ በኩል ቀርቧል፡፡ እኔ ትንሽ ለመጨመር የፈለኩት በኦሮሚያ፣ በወላይታ፣ በክብረ መንግሥት፣ በጋሞ ጎፋ እየተከሰቱ ያሉ የጅምላ እስሮች የታሳሪዎቹም ስሞች አሉን፡፡ በጣም የሚገርመው ዛሬ ያጣራነው ሐረር አካባቢ አቶ ሞሐመድ ሐሰን የሚባል በመጋቢት 5 ቀን 2003 ዓ.ም ታስሮ እስካሁን ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ ይህ ሰው ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲኾን የልማት ሠራተኛ ነው፡፡

ሌላው ይህ ችግር በሌሎች ቦታዎችም እየተከሰተ ስለመኾኑ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ ባህር ዳር በቀደም የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ችግር እንደነበር ሰምታችሁ ይኾናል፡፡ እዚያ የእኛ አባላት የኾኑ ሠራተኞች እናንተ ናችሁ የምትቀሰቅሱት ተብለው የማሳደድ ኹኔታዎች አሉ፡፡

Daniel Berhane

more recommended stories