Ethiopian Oil | ሚኒስትር ስንቅነሽ: በነዳጅ ፍለጋ አዲስ ነገር የለም

ሰሞኑን የተለያዩ ጋዜጦችና ድረ ገፆች «በኦሞ አካባቢ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት ክምችት ተገኝቷል» በሚል እየዘገቡ ቢሆንም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን ነዳጅ ዘይትን በተመለከተ ያለው ተጨባጭ እውነታ በአሁኑ ወቅት ጋዜጦች በሚገልፁት መልኩ የሚነገርበት ደረጃ ላይ አይደለም ብሏል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ ትናንት እንደተናገሩት፤ ቱሎ ኦይል በጋና፣ በዩጋንዳና በኬንያ ካከናወናቸው ስኬታማ ስራዎች በመነሳት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከነዳጅ ፍለጋው ጋር በተያያዘ የተዛቡ ዘገባዎች እየወጡ ናቸው፡፡

የነዳጅ ፍለጋ ስራው በጥሩ ኩባንያ እጅ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የቁፋሮ ሥራው እንደቀጠለ ነው፤ ውጤቱንም በሂደት የምናየው ይሆናል ብሎ ከሚገለፅ ውጪ አዲስ ነገር የለም ብለዋል፡፡

በኦሞ የነዳጅ ቤዚን የእንግሊዝ ኩባንያ ቱሎ ኦይል 50 በመቶ የነዳጅ ፍለጋ ድርሻ አለው፡፡ 30 በመቶው የአፍሪካ ኦይል ሲሆን፤ 20 በመቶው ደግሞ የአሜሪካው ማራቶን ኩባንያ ድርሻ ነው፡፡

ወይዘሮ ስንቅነሽ እንዳሉት ቱሎ በዘርፉ የቴክኒክ ብቃቱ የዳበረና በጥሩ ሁኔታ ስራውን የሚያከናውን ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ በኦሞ አካባቢ የጂኦ ሳይንስ ስራውን አከናውኖ እ.ኤ.አ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም በይፋ ቁፋሮ ጀምሯል፡፡

ኩባንያው ሶስት ጉድጓዶች የሚቆፍር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የአንዱ ጉድጓድ ቁፋሮ ከ1ሺ 400 ሜትር በላይ ጥልቀት ደርሷል፡፡ የቁፋሮው ውጤት የሚጠናቀቀውም አንዱ ጉድጓድ 2ሺ 600 ሜትር ጥልቀት ላይ ሲደረስ ነው፡፡ ኩባንያው አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር 50 ሚሊዮን ዶላር በራሱ ወጪ ያደርጋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የነዳጅ ቤዝን (ተፋሰስ) ተብለው በተለዩት የመቀሌ፣ የዓባይ፣ የጋምቤላ፣ የመተማ፣ የኦሞና የኦጋዴን ቤዚኖች የነዳጅ ፍለጋ እየተካሄደ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሰፊውና ከ350ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው የጋዝ ግኝት ያለው የነዳጅ ምርመራ የሚካሄደው በኦጋዴን ቤዚን ነው፡፡

ኩባንያዎቹ በእነዚህ አካባቢዎች የተለያዩ የስነ ምድርና የጂኦ ፊዚክስ ስራዎችን ካከናወኑ በኋላ ወደ ቁፋሮ ገብተዋል ያሉት ወይዘሮ ስንቅነሽ፤ ቁፋሮው ግን የፍለጋው አካል እንጂ ነዳጅ ተገኝቷል የሚያሰኝ አይደለም ብለዋል፡፡ የአንዱ ጉድጓድ ቁፋሮ እንኳን ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ምንም ማለት እንደማ ይቻልም ተናግረዋል፡፡

«ኩባንያው ሶስት ጉድጓድ ለመቆፈር ፍላጎት ማሳየቱና ወደ ተግባር መግባቱ መንግስትን አስደስቷል፡፡ ኩባንያውም ደስተኛ ሆኖ እየሠራ ነው፡፡ የቁፈራውን ውጤት አብረን እያየን ለሕብ ረተሰቡ ይፋ የምናደርገው ካለ እናደርጋለን፡፡ ዋናው ነገር ጥሩ እንቅስቃሴና ተነሳሽነት ያለው ኩባንያ መሆኑ ላይ ነው» ሲሉም አብራርተዋል፡፡

**************

* Originally published on Addis Zemen, on March 1, 2013, titled "የነዳጅ ፍለጋው ድረ ገፆች በሚዘግቡት መልኩ የሚነገርበት ደረጃ ላይ አልደረሰም".

more recommended stories