ለተቃዋሚዎች ውድቀት የሚታዩና የማይታዩ የራሳቸው ምክንያቶች Amharic

(ከአዲስ ምዕራፍ)

የመድረክ የአመራር አባል የሆኑት ዶክተር መረራ ጉዲና እሁድ ህዳር 9 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለምልልስ በጥሞና አነበብኩት፡፡

“ለተቃዋሚዎች ውድቀት የሚታዩና የማይታዩ የኢህአዴግ እጆች አሉበት” የሚለው ከርሳቸው አባባል የተወሰደው ጥቅስ በርእስ መልክ መቀመጡ አንባቢን የሚስብ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ እኔንም ጐትቶ ወደ ንባብ ያስገባኝ ይኸው ርእስ ነው፡፡ ርእሱ ገና ከመጀመሪያው ተጠያቂነትን ለመሸሽ ያለመ በመሆኑ ድክመትን የሚያሳይ ቢሆንም እነዚያን የሚታዩ የኢህአዴግ እጆች ከዶክተሩ ቃለምልልስ ለመፈለግ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡

በአንድ ገፅ ተኩል ላይ የሰፈረውን የዶክተሩን ቃለምልልስ አንብቤ ሳበቃ የተባሉትን የሚታዩና የማይታዩ የኢህአዴግ እጆች ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ይልቁንም ሰውየው የድርጅታቸውንም ሆነ የሌሎችን ተቃዋሚ ድርጅቶች ድክመት በኢህአዴግ ላይ ለማሳበብ መሞከራቸው በእጅጉ አሳዘነኝ፡፡ በዚሁ ሙከራቸው እርስ በርሱ የሚቃረን ሃሣብ ከማራመዳቸውም ባሻገር ዴሞክራሲን በተመለከተ እሳቸውና ድርጅታቸው ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ በመሆኑም በቃለመጠይቁ ላይ ያነሷቸውን ነጥቦች በአጭሩ ለመመርመርና በኋላም ለተቃዋሚዎች ውድቀት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች ለመዘርዘር ብዕሬን አነሳሁ፡፡

ዶክተር መረራ “የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አገርን ለመምራት የሚያስችል የአመራር አቅም፣ ግልፅ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፕሮግራም የላቸውም ይባላል እንዴት ያዩታል” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፕሮግራም እንዳላቸው ነገር ግን የሚዲያ ሽፋን ስላላገኙና ገንዘብ ስለሌላቸው በብዛት አለማስተዋወቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው በ1997 ዓ.ም ህዝቡ እነርሱን እንደመረጠ ደግሞ ገልፀዋል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ መድረክና አባላቱ የተሰባሰቡት አንድ ወጥ በሆነ ፕሮግራም ስር እንዳልሆነ ዶክተሩም ያውቃሉ፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃም አንዳንዶቹ በአገራችን ኒዮ ሊበራል አስተሳሰብን ለማስፈን አንዳንዶቹ ደግሞ ሶሻል ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ እንሰራለን ይላሉ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚደንቀው በመሬት እና በብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ላይ መድረከ አቋም የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መድረክ አንድ ወጥ አቋም ለመያዝ ባለመቻሉ ጉዳዩን በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለህዝበ ውሳኔ እንደሚያቀርበው በይፋ መግለፁ የሚታወቅ ነው፡፡ የመሬትና የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ በአገራችን ዋነኛ የፖለቲካ ጥያቄዎች መሆናቸው እየታወቀ በነዚህ ጉዳዮች ላይ አቋም ሳይወስዱ እንዴት ተደርጐ ህዝብን ማነሳሳትና ማሰለፍ እንደሚቻል ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

የመድረክ አመራሮች በአንድ በኩል ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አለን እያሉ በሌላ በኩል ፕሮግራማችንን ለማስተዋወቅ የተቸገርነው በሚዲያና በገንዘብ እጦት ነው ይላሉ፡፡ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ሊመጣ የሚችለው ፕሮግራሙ ህዝቡን የሚነሽጥና ለትግል የሚያሰባስብ ሲሆን ነው፡፡ ከትግል የተሰባሰበ ህዝብ ደግሞ መሪ ፓርቲውን በሞራልም በገንዘብና በማቴሪያልም ከማጠናከር ወደኋላ እንደማይል ገሃድ ነው፡፡ በመሆኑም መድረክ የህዝብ ድጋፍ አለኝ ካለ ይኸው ድጋፍ በተግባር መገለፅ ያልቻለበትን ምክንያት ደርቦ የማብራራት ዕዳ ያለበት ይመስለኛል፡፡

ዶ/ር መረራ ቀጥለውም ‘ቢፈቀድልን ከኢህአዴግ በላይ አባላት ልንመለምል እንችላለን’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መቼም አንድ ድርጅት አባል የሚመለምለው ሌላው ድርጅት ሲፈቅድለት አይደለም፡፡ መድረክ የሚያታግልና የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጐት የሚያንፀባረቅ ፕሮግራም ቢኖረው ህዝቡ ያለማንም ፈቃድ ከጐኑ እንደሚሰለፍ የታመነ ነው፡፡ በትግል የሚያምንና ላመነበት መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ የሆነ ድርጅት አባላት ለመመልመል እንቅፋት ቢገጥመው እንኳ ታግሎ ራሱን ያጠናክራል እንጂ ተከለከልኩ እያለ ሰበብ እየደረደረ ሲቆዝም አይታይም፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር መረራ በዚያው ቃለምልልስ ላይ ኢህአዴግ የአባላቱን ቁጥር ማሳደጉን አውግዘውታል፡፡ የኢህአዴግ አባላትንም በጥቅማ ጥቅም ተደልለው የገቡ ናቸው ሲሉም ዘልፈዋል፡፡ በአንድ ወቅት ስንት አባል አላችሁ ሲባሉ የእኛ አባላት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ናቸው ሲሉ እንዳልነበር ዛሬ ምነው የአባል ድርቅ መታን ብለው ለመጮህ ከጀሉ? ወይስ በዚህ አገር የድርጅት አባል ሊሆን የሚችለው ኢህአዴግ የመለመለው 6 ሚሊዮን ዜጋ ብቻ ነው?

እኚህ የመድረክ አመራር በዚህ ቃለመጠይቅ ላይ ያንፀባረቁት እጅግ አደገኛና የድርጅታቸው ዋነኛ መገለጫ የሆነው አስተሳሰባቸው በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና በዴሞክራሲ ላይ ያላቸው የተዛባ አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢህአዴግ በአገራችን ውስጥ የቀበሌ ተመራጮችን ቁጥር ከ600 ሺህ ወደ 3.6 ሚሊዮን ማሳደጉ ተቃዋሚዎችን አቅም ለማሳጣት የተነደፈ ስትራቴጂ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ እጅግ በተዛባ መልክም ኢህአዴግ የውክልና ዴሞክራሲን በቀጥተኛ ዴሞክራሲ በመተካት ወደ አሪስቶትል ዘመን መልሶናል ይላሉ፡፡

ኢህአዴግ የውክልና ዴሞክራሲን አላጠፋም፡፡ ለፌደራል፣ ለክልል፣ ለዞን፣ ለወረዳና ለቀበሌ የሚካሄደው ምርጫ ከምልአተ ህዝቡ በየደረጃው ህዝቡን ለማስተዳደር የሚወከሉ ሰዎችን ለመምረጥ ወይም ለመወከል የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአንድ ወቅት እርሳቸው ተመርጠው የገቡበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላ አገሪቱ በምርጫ የተወከሉና አገሪቱን ለቀጣይ አምስት አመታት የሚያስተዳድሩ 547 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ያካተተ እንደሆነ የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ በሌሎች ደረጃዎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ በኢህአዴግ አስተሳሰብ መሰረት ስልጣን የህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ወደታችኛው የአስተዳደር እርከን ሲኬድ ህዝቡ በስፋት በምክር ቤቶች ውስጥ በመሳተፍ የአካባቢውን ጉዳይ በተመለከተ ጠንካራ የመወሰን አቅም እንዲኖረው ማድረግ በተለይ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጠቃሚ መሆኑን ያምናል፡፡ የመድረክ አመራሮች አስተሳሰብ ዴሞክራሲ ብዙሃኑን ህዝብ ከውሳኔ ሰጪነት በማግለል ጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በነርሱ አስተሳሰብ ኢህአዴግ የውክልና ዴሞክራሲንና ህዝቡ አቅም በፈቀደ መጠን በቀጥታ የሚሳተፍበትን ቀጥተኛ ዴሞክራሲ አጣምሮ መሄዱ ፀረ-ዴሞክራሲ ነው፡፡ በነርሱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲ ማለት ብዙሃኑ በየተወሰኑ አመታት ወጥቶ ጥቂቶችን እየመረጠ በተቀሩት ጊዜያት ከፖለቲካው መድረክና ከውሳኔ ሰጭነት ተገልሎ የሚቆይበት አካሄድ ነው፡፡

ዶ/ር መረራ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከውክልና ዴሞክራሲ የሰፋ መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ ህዝቡን በአገሩና በአካባቢው ጉዳዮች ላይ ቀን ተቀን እንዲወስን የወሰነውንም ውሳኔ እንዲያስፈፅም የላቀ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ክደዋል፡፡ ችግራቸው ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ የጥቂት እናውቅልሃለን ባዮችን የስልጣን መንገድ የሚዘጋ፣ ህዝቡን ትክክለኛ የስልጣን ባለቤት የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡ ከ8ዐ ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 3.6 ሚሊዮን የሚሆነው በየቀበሌው ምክር ቤት ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲመራ መደረጉ ዶ/ር መራራን የሚያበሳጫቸው ለምንድን ነው? በአገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቃሶ አባላትን የመመልመል ዕድል ለሁሉም ድርጅቶች እኩል ነው፡፡ የአካባቢ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚከብደን ያን ያህል ዕጩ ለማቅረብ ስለማንችል ነው ብለዋል፡፡ ታዲያ በአቅማቸው ለምን አያቀርቡም? ግማሹን ወይም ሩቡን አቅርበው ለምን አይወዳደሩም? ችግሩ ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡ መድረክና አባላቱ ያን ያህል ዕጩ መመልመል ፍላጐቱም አቅሙም የላቸውም፡፡

ለዶ/ር መረራና መሰሎቻቸው ዲሞክራሲ ማለት ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ሳይሆን የእርሳቸውና የመሰሎቻቸው ተሳትፎ ነው፡፡ መሳተፋቸው ባልከፋ ነበር፡፡ ችግሩ ይህንን ተሳትፎ በምርጫ አማካኝነት ለማግኘት ያላቸው ፍላጐትና አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየሟሸሸ መሄዱ ነው፡፡ ጠንካራና አገርን ለመምራት የሚችል ነው የሚሉት ድርጅታቸው አባላትን በሰፊው መመልመልና ዕጩዎችን በብዛት ማቅረብ ካልቻለ በምኑ ነው አገርን ለመምራት የሚንቀሳቀሰው? መቼም የኢህአዴግን መዋቅር ተጠቅመን እናስፈፅማለን እንደማይሉኝ እገምታለሁ፡፡

በቃለመጠይቁ ላይ ተመስርቶ ብዙ ማለት ቢቻልም እርሱን ገታ አድርጌ ለተቃዋሚዎች ውድቀት ምክንያት የሆኑትን የሚታዩና የማይታዩ የራሳቸውን ጉዳዮች በአጭሩ በመጥቀስ ፅሁፌን ላጠቃል፡፡

መድረክና መሰሎቹን ከቀን ወደቀን እያደቀቋቸው ከሄዱት ምክንያቶች አንዱ ግልፅ የሆነ ህዝቡን ሊማርክ የሚችል አማራጭ ለማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ድርጅቱ ፕሮግራም የሚለው የተፃፈ ነገር አለኝ ይላል፤ ሊኖርም ይችላል፡፡ ይህንን ፕሮግራሙን በተለያዩ መንገዶች ማስተዋወቅና ህዝብን በዚያ ዙሪያ ለማሰባሰብ ጥረት አለማድረጉ የሚታይ ድክመት ነው፡፡ የማይታየው ድክመት አማራጭ ተብየው መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን በተመለከተ አማራጭ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ መሬትና የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በተመለከተ ቁርጥ ያለ አቋም የለውም፡፡ በመሆኑም በ97 ቅንጅት የተወሰኑ የፓርላማ ወንበሮችን በምርጫ ካሸነፈ በኋላ ተመልሶ ህዝቡን ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ ብሎ ግራ እንዳገባው ሁሉ ዛሬ ደግሞ ‘ምረጠንና አላማችንን በኋላ ትመርጥልናለህ’ የሚል አካሄድ መከተሉ የማይታየው ድክመት ነው፡፡

ሌላው ችግር በአላማ ዙሪያ የተሰባሰበ ቁርጠኛ አባል ለማፍራት አለመቻሉ ነው፡፡ በርግጥ ከላይ ሲታይ ጥቂት አባላትና ደጋፊዎች ይኖሩታል፡፡ የማይታየውና ጠለቅ ሲባል የሚታወቀው ብዙዎቹ አባላት ድርጅቱን የሚጠጉት በኢህአዴግ ወይም በመንግስት ላይ ቅሬታ ስላላቸው ወይም በሆነ ወንጀል የተቀጡና ስርአቱን በድፍኑ የሚጠሉ ስለሆኑ ነው፡፡ እነዚህ አባላት የመድረክ ፕሮግራም ምንድነው ቢባሉ አንድ ሁለት ብለው የሚዘረዝሩ እንዳልሆኑ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ለመድረክና ለተቃዋሚዎች ውድቀት ሌላው ምክንያት በመርህ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ትግል አለማካሄዳቸው ነው፡፡ ከላይ ሲታይ እርስ በርስ ተከፋፍለው ሲነታረኩ እንደሚውሉ ህዝቡ ይገነዘባል፡፡ አንዱ ሌላውን ሲከስ የምርጫ ቀን ይደርሳል፡፡ በዚህ ምክንያት ህዝቡ ከሩቅ እነዚህ በውስጣቸው መስማማት የተሣናቸው እንዴት ብለው ሀገር አስማምተው ሊመሩ ይችላሉ በማለት ተስፋ እንዲቆርጥ አድርገውታል፡፡ የማይታየው ምክንያት ግን የውስጣዊ ትርምሳቸው ሥር መሠረት ድርጅቶቹ በውስጣቸው የዴሞክራሲ ሽታ እና መርህ የሚባል ነገር የሌለ መሆኑ ነው፡፡ ሃሣብን በነፃ ማንሸራሸር በሃሣብ ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ አይታሰብም፡፡ ጥቂቶች እኛ ያልነው ካልተፈፀመ ብለው ድርጅቶቹን የሚያምሱበት የጨረባ ተዝካር የመሰለ ተፈጥሮ ነው ያላቸው፡፡ በቡድን ተከፋፍሎ መጠዛጠዝ፣ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ማሴር፣ ዛሬ ከአንዱ ወግኖ ሌላውን ከጣለ በኋላ ነገ ደግሞ ከሌላ ወግኖ የመጀመሪያውን ለመጣል ማድባት
— ፡፡ በውስጡ ዴሞክራሲ የሌለው ድርጅት ደግሞ በምንም መልኩ ለዴሞክራሲ ሊቆም አይችልም፡፡

ሌላው ምክንያት ድርጅቶቹ የሚፈጥሩት ህብረት ባህሪ ነው፡፡ በአገራችን ተቃዋሚዎች ያልፈጠሩት አይነት ህብረት የለም፡፡ ከላይ ሲታይ የተጣመሩ የተዋሃዱ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን የሚጣመሩበት ዋነኛ ጉዳይ የኢህአዴግ ጥላቻ በመሆኑ በመርህ ሊተሳሰሩ አይችሉም፡፡ በመሆኑም የአስተሳሰብ ጉዳያቸውን ደብቀው በፀረ-ኢህአዴግ ግንባር ለመሰለፍ አድርባይ በሆነ መንገድ ለመራመድ ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም ቢሆን ወደፊት ማራመድ አቅቷቸው ሲፍረከረኩ ይታያሉ፡፡ የማይታየው ሌላው ችግር ግን ውስጣቸው በቅራኔ የተሞላ መሆኑ ነው፡፡ አንደኛው ድርጅት የብሄሮች ጥያቄን አንግቦ ሲነሳ ሌላኛው ለአሃዳዊ አስተዳዳር እታገላለሁ ይላል፡፡ አንዱ መሬት መሸጥ መለወጥ የለበትም ሲል ሌላኛው ካልተሸጠማ ሞቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ በመሆኑም ህብረቱ እጅግ የደከመ እና ብዙ ሊጓዝ የማይችል ነው፡፡

ለማጠቃለል ዶ/ር መረራ ለድርጅታቸውና ለሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች መዳከም የኢህአዴግን የሚታዩና የማይታዩ እጆች በምናብ ስለው ከንፈር ለማስመጠጥ ከመሞከር ይልቅ በነርሱ ዙሪያ የተደረደሩትን የሚታዩና የማይታዩ ምክንያቶች ፈትሸው መፍትሄ ቢያፈላልጉ ለአገራችን ዴሞክራሲ በጐ አስተዋፅኦ ባደረጉ ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን ለማድረግ የተረጋጋ፣ ዓላማ ያለው፣ ለመስዋእት የቆረጠ አመራር ያስፈልጋል፡፡ እነዶክተር ይህንን ለማድረግ ጊዜውም ፍላጐቱም ስለሌላቸው ኢህአዴግን እየወቀሱ እድሜያቸውን ይፈጃሉ፡፡ የነ ዶ/ር መረራ የመፍትሔ ቅርጫት ያለችው የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች ደጅ እንጂ ከውስጣቸውና ከህዝባችን ጋር መቼ ሆነችና እንዲህ፣ እንዲህ፣ እያሉ፣ እንዲሁ እንዳሉም ቦታቸውን ለሌሎች ባለታሪኮች መልቀቃቸውም አይደል?
********

* Source: Addis Meraf – the twice-monthly ideological magazine of the ruling party EPRDF, Nov. – Dec. 2012 issue.

Check the archives for related posts.

more recommended stories