ዲሞክራሲ ያለ ጋዜጣ? Newspaper Printing Cost Hike

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ጋዜጣ አነባለሁ፡፡ ማንበብ ሲባል ታዲያ ልክ እንደሥራ ሁሉንም ጋዜጦችና ሙሉ ይዘታቸውን ማጠብ ማለቴ ነው፡፡ ለዚህም የበጀት ድጋፍ ነበረኝ፡፡

እናም ልክ በፊልም እንደማያቸው ሰዎች እኔም ‹ ትልቅ ስሆን ከቁርስ ጋር የዕለቱን ጋዜጣ አነባለሁ › ብዬ አስብ ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬ ጋዜጣ ከመቼውም በላይ ሩቅ ሆኗል፡፡ 5 ብር ለአንድ ጋዜጣ!! ስለሆነም የተወሰኑትን በግዢ ሌሎቹን ከመ/ቤትና በውሰት ማንበብ ግድ ሆኗል፡፡

አሁን ደግሞ የማተሚያ ዋጋውን ተከትሎ የጋዜጣ ዋጋ ሲጨምር መ/ቤቶች ግዢ እንደሚቀንሱ፣ ገዝቶ የሚያውስ ሰው ቁጥር ይበልጥ እንደሚያሽቆለቁል አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ አሁን ህልሜን አሻሽዬአለሁ – ‹ዲቪ ከወጣልኝ ከቁርስ ጋር የዕለቱን ጋዜጣ አነባለሁ›፡፡

ዲሞክራሲ ያለ ጋዜጣ ይሏል ይህ ነው፡፡

በሳምንት እስከ 30 ጋዜጦችን በማተም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መንግስታዊው ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ቤት በጋዜጦች ማተሚያ ላይ የ50 በመቶ ጭማሪ እንደሚያደርግ  አሳውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎም መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም. በጋራ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር እና የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር አመራሮች ‹ የሕትመት ዋጋው መናር ጋዜጠኞችን ከሥራ ሊያፈናቅል የሚችልበት አጋጣሚ በመኖሩ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻዎች ሸክሙን ሊጋሩ ይገባል › ብለዋል፡፡ ቀደም ብሎም 22 አሳታሚዎች ተሰብስበው ማተሚቤቱ የሕትመት ዋጋውን ዝርዝር እና ይህንንም በባለሙያ ለማስጠናት የዋጋ ጭማሪውን በ3 ወር እንዲዘገይ ጠይቀው የነበር የነበር ሲሆን፤ ማተሚያ ቤቱ በሰጠው መረጃውን ለመስጠት ተስማምቶ፣ የ3 ወር ጊዜ ጥያቄውን በተመለከተ ግን ማተሚያ ‹ የአንድ ቶን ወረቀት ዋጋንና ቀረጥና ማጓጓዣን ለማስላት የአንድ ሰዓት ሥራ ስለሆነ ማስጠናት አያስፈልግም › በማለት ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

የጋዜጦች ማተሚያ ዋጋ ጭማሪን አስመልክቶ እንደሌላው ጊዜ ወጥ ጽሁፍ ከመፃፍ ይልቅ የሚከተሉትን የተመረጡ ጽሁፎች (excerpts) ማቅረቡን መርጫለሁ፡፡

የማተሚያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉወርቅ ገብረ ሕይወት ለሪፖርተር ጋዜጣ በመጋቢት 18/2003 በሰጡት ቃለ-ምልልስ፤ የዋጋ ጭማሪው ፖለቲካዊ አንድምታ እንደሌለውና በወረቀት ዋጋ በጨመር ሳቢያ እንደተከሰተinterview ተከራክረዋል፡፡

በፊት ለምንገዛው ወረቀት እስከ ወደብ ድረስ ያለው የጭነት ማጓጓዣ ክፍያ ጨምሯል፡፡ አሁን ግን የፎብ (ፍሬት ኦን ቦርድ) ዋጋ 42 በመቶ እንድንከፍል ተደርገናል፡፡ በፊት በቶን 490 የአሜሪካ ዶላር ነበር፡፡ አሁን ግን 696 የአሜሪካ ዶላር ሆኗል፡፡ ይህ ማለት የጭነት ማጓጓዣው በቶን 206 ዶላር ጨምሯል ማለት ነው፡፡
እኛ የጨመርነውና በትክክል በወረቀት ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ አንድ አይደለም፡፡አጠቃላይ የጨመረብን ወደ 70 በመቶ ነው፡፡ ሌላውን ወጪ እኛ ችለን የተወሰነውን ጨምረናል፡፡ የፎብ ዋጋ መጨመርና የዶላርና የብር ምጣኔ መለያየት (ዲቫሉዌሽን) በማሳተሚያ ዋጋ ላይ እንድንጨምር አስገድዶናል፡፡ ትክክለኛው የዲቫልዌሽን ለውጥ 22 በመቶ ቢሆንም፣ የጉምሩክ፣ የመርከብና ሌሎችም ተጽዕኖ ከ30 በመቶ በላይ እንዲጨምር ስለሚያደርገው ጭማሪውን ከፍ ያደርገዋል፡፡

‹ ለዋጋ መጨመር ምክንያት የሆናችሁ የወረቀት ዋጋ ጨምሮ ሳይሆን፣ በሰሜን አፍሪካና በዓረቡ ዓለም እየታየ ያለውን ተቃውሞ በሚመለከት ጋዜጦች የሚዘግቡት ዘገባ ሕዝብን ሊያነሳሳ ይችላል በሚል ነው፡፡ በጋዜጦች ላይ የማሳተሚያ ዋጋን በመጨመር ከገበያ እንዲወጡ ለማድረግ በእጅ አዙር እናንተ ጫና እንድታደርጉ ከመንግሥት አካላት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ይሆናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡› በማለት ጋዜጣው ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-

የእኛ ድርጅት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ነው፡፡ ማንም ተጽዕኖ የሚያደርግብን አካል የለም፡፡ የምንሠራው ቢዝነስ ነው፡፡ አትራፊ እንደመሆናችን መጠን የምንሠራው ለማትረፍ ነው፡፡ ዋጋ ሲጨምርብን እንጨምራለን፤ ሲቀንስልን እንቀንሳለን፡፡ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አለን፡፡ እሱ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ አይገባም፡፡

ጋዜጣው የጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ አንድምታ አስመልክቶ ላቀረበው ‹ በዋጋ ጭማሪ ምክንያት ጋዜጦች አቅም አጥተው ቢዘጉ፣ የዜጎችን የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ማሳጣት አይሆንም?› የሚል ጥያቄ የሰጡት መልስ፡-

እኛ የምናየው ወይም የምንሠራው እንደ ነጋዴ ነው፡፡ ይህን ከመረጃ ነፃነቱ ሕግ፣ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከብሮድካስት ሕጉና ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ያለውን ሁኔታ እናንተው የምትሄዱበት ይሆናል፡፡ በዚህ ዙርያ ላይ የእኔ መልስ መሆን ያለበት ወይም ማድረግ ያለብኝ እንደ ነጋዴ በመሆኑ ሌላ የምልህ የለኝም፡፡

ይሁንና በዚያው በሪፖርተር ላይ ስለጉዳዩ የቀረበ የትንታኔ ዘገባ ጣቱን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ላይ ይቀስራል፡፡ በጽሁፉ ውስጥ የወረቀት ዋጋ መጨመር አለመጨመር አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡-

ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ የወረቀት አስመጪዎችና አንዳንድ አታሚዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የወረቀት ዋጋ የተረጋጋ ነው፡፡ ‹‹አገር ውስጥ ያለው የወረቀት ገበያ ተቀዛቅዟል፡፡ ገበያ መቀዝቀዙ እንጂ የዶላር መጨመር ዋጋው ላይ ያመጣው ለውጥ ያን ያህል ነው፤›› ይላሉ፡፡

ከላይ አስተያየታቸውን የገለጹት አንድ የወረቀት አስመጪ፣ ለዋጋው መናር አስተዋጽኦ ያደርጋል ከተባለ ዋናውን ድርሻ የሚወስደው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ዕቃዎች ከተገዙበት ዋጋ በታች በሆነ ደረሰኝ ቀረጥ እንዳይከፈልባቸው ለመከላከል በሚል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የራሱን የዋጋ ተመን አውጥቶ ገቢ ዕቃዎችን የሚቀርጥ በመሆኑ፣ ብዙ ጊዜ ከተገዙበት ዋጋ በላይ ቀረጥ ይከፈልባቸዋል ያሉት ደግሞ አንድ የሒሳብ ባለሙያ ናቸው፡፡ ባለሙያው በወረቀት አስመጪ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ በመሆናቸው ለአንድ ሜትሪክ ቶን ወረቀት (ለጋዜጣ ሕትመት የሚውል) እስከ 550 ዶላር የሚከፈልበትን አጋጣሚ አንስተዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ ኃይሌ ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበትና በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የገባው ወረቀት መጠን 1,200 ቶን ነው፡፡ ድርጅቱ ለወረቀቱ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተጠየቀው የቀረጥ መጠን ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ነው አቶ አዳሙ የገለጹት፡፡ በዚህም ለአንድ ቶን ወረቀት ድርጅቱ 2,500 ብር እንደከፈለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡

ለወረቀት ምርት ማጓጓዣ ወጪ ሲባል ለኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማኅበር በዶላር መከፈሉም ይህ ነው የሚባል ልዩነት እንዳላመጣና ለውጥ አለው ከተባለም የአንድና የሁለት ብር ያህል እንደሆነ እነዚሁ አስመጪዎች ይገልጻሉ፡፡

ለብርሃንና ሰላም የሚያመጡለትም ሆነ ራሱ ድርጅቱ አምጥቶ የሚያትምበት የወረቀር ዓይነት (በብዛት ሲነር ላይን) ኤቪያን ፐልፕ ኤንድ ፔፐር ከተባለ ኩባንያ ሲሆን፣ በዱባይ ወኪል ያለው ነው፡፡ አብዛኞቹ አስመጪዎችም ከዱባይ የሚያመጡ በመሆናቸው ዋጋው ርካሽ ነው፡፡

በቅርቡ ከኢዴፓ አመራርነት የለቀቁት አቶ ልደቱ አያሌው በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የጉዳዩን  አሳሳቢነትና ከምን አንጣር ሊጣይ እንደሚገባው በትክክል የሚያሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እንደአንድ አማራጭ የጠቆሙት የመንግስት ድጎማ ሐሳብም ቢሆን ቢያንስ እንደመጨረሻ አማራጭ ሊያዝ የሚገባው እንጂ ሙሉ በሙሉ ሊጣል አይችልም፡፡

የጉዳዩን ክብደት አቶ ልደቱ ሲያመለክቱ፡-

መንግሥት በደንብ አስቦበትና ችግሩን በልዩ ሁኔታ አይቶ መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡ ይህ የንግድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ የመብት ጉዳይ ነው፡፡ የዲሞክራሲና የሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ነው፡፡ የለውጥ ሒደትን የመግታትና ያለመግታት ጉዳይ ነው፡፡ ከጋዜጦች ጋር የተያያዘን ጉዳይ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታው ይገባል፡፡ በገበያ ሥርዓት ብቻ መታየት ያለበት ጉዳይም አይደለም፡፡ የንግድ ጉዳይ ባለመሆኑ የተደረገው ጭማሪ አስደንጋጭ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በጭላንጭል ውስጥ ያለው የማንበብና የመጻፍን ነፃነት ጭራሽ እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው፡፡ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዶ የጋዜጦችን ዋጋ ወደ ሦስትና ሁለት ብር ዝቅ እንዲሉ ያደርጋል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ አምስት ብር በጣም ከፍተኛ ዋጋ ነው፡፡ ገዝተው የሚያነቡት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ አብዛኛው ሰው ለማንበብ ቢፈልግም አቅም ስለሌለው የጋዜጦቹን ርዕስ ብቻ አይቶ፣ ሃያና ሠላሳ ሳንቲም ከፍሎ የሚሄድ ነው፡፡ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ለዚህ ሴክተር ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ ካላሳየ ‹‹ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እየገነባሁ ነው›› ማለት ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡

የመፍትሔው ሀሳብ እንዲያቀርቡ ጋዜጣው ሲጠይቃቸው፡-

በቀጥታ ይህ ነው ልልህ አልችልም፡፡ መንግሥት ግን ብዙ አማራጮች አሉት ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግሥት ዝርዝር ጥናት አድርጎ ዜጎች ያለምንም ችግር መረጃ የሚያገኙበትንና አንዱ ዘርፍ የሆነውን የጋዜጣ ዋጋ ከአምስት ብር በታች እንዲሸጥ ማድረግ አለበት፡፡
ሴክተሩን በመለየትና ቢያንስ ለፕሬስ ጥቅም የሚውለውን ከታክስ ነፃ ማድረግ አለበት፡፡ ቀረጥም ሳይቀረጥ በውጪም ዋጋው ተወዶ ከሆነ እስከ ድጎማ ድረስ መሄድ አለበት፡፡ ያንን ያህል በከፍተኛ ሁኔታ የመንግሥትን በጀት ሊያዛባ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ በሳምንት የሚታተሙትን ጋዜጦች ደምረን ብናያቸው ከማንኛውም አገር ጋር ልናወዳድራቸው የማንችል ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህን መደጎም በመንግሥት በጀት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ሊያስከትል አይችልም፡፡ መንግሥት ጉዳዩን ችላ ማለት ወይም ምን ያመጣሉ ሳይል አገራዊ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ መፍትሔ መስጠት ይችላል፡፡ ለመፍትሔው ትንሽ ጥናት ማድረግ ብቻ ይበቃዋል፡፡

ስለ ግል ፕሬሱ ያላቸውን አመለካከት አስምለክቶ ሁለት ጊዜ ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፤ ከሰጧቸ ምላሾች መሀል፡-

እኔን በሚመለከት ጋዜጦች ያደረጉኝ ነገር የአደባባይ ምስጢር ይመስለኛል፡፡ ሐሳቤ ለሕዝብ እንዲቀርብ ፕሬሶች በጎ ትብብር ያደረጉልኝን ያህል፣ በዚያው መጠን ደግሞ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በስም ማጥፋት ሥራ ተሰማርተው በጎ የሆነውን የፕሬስ ተልዕኮ ለራሳቸው ግላዊ ስሜት ተጠቅመውበታል፡፡ ወይም ደግሞ የፖለቲካ መሣርያ በማድረግ የተጠቀሙበት ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚያ ሰዎች ፕሬሱን አላግባብ ስለተጠቀሙበት የፕሬስን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት አይቻልም፡፡ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ጋዜጦች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሙያውን አክብረው የሚሠሩበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የመታገል ጉዳይ ነው፡፡ ከኃላፊነት ውጪ ጋዜጦችን የሚጠቀሙ ሰዎች ስላሉ አጠቃላይ የጋዜጣን ሚና ጥያቄ ውስጥ ማስገባት አይቻልም፡፡ ……….ገና ለገና …. እኩይ ተግባር ይፈጸማል ተብሎ የፕሬስን ሚና ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ግን አይቻልም፡፡ ሙያው አድጎ፣ ዳብሮ፣ ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ በአግባቡ እንዲፈጸም ነው ጥረት መደረግ ያለበት፡፡

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ከችግር የፀዳ ነው፣ ከድክመት የፀዳ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ብዙ ችግሮች፣ ብዙ ድክመቶች የነበሩበትና አሁንም አልፎ አልፎ ያሉበት ሴክተር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡ ታዳጊ እንደመሆናችን መጠን ዲሞክራሲያችን ገና ታዳጊ የመሆኑን ያህል ያለን ልምድና ታሪክ በዛው መጠን ገና ነው፡፡ ስለዚህ ፕሬሱ ለብቻው ተለይቶ የበቃ ሆኖ ይገኛል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ልክ በተቋሚዎች፣ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት፣ በኅብረተሰቡ ውስጥና በተለያዩ ማኅበራት ላይ እንደምናያቸው ችግሮች ፕሬሱም ላይ በአጠቃላይ ከዕድገታችን ጋር በተያያዘ ችግርና ድክመት ማየታችን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በአንድ በኩል ይኼ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፍፁም ጋዜጠኛ ሊሆኑ የማይገባቸው ሰዎች፣ ችሎታውም የሌላቸው፣ ሙያውና፣ ፍቅሩም የሌላቸው፣ ነገር ግን የራሳቸውን የፖለቲካ ስሜትና አጀንዳ ብቻ ለማራመድ በየጋዜጣው ገብተው አፍራሽ የሆነ ሥራ ሲሠሩ እንደቆዩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

በብዙ ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ሲዘገቡ አይተናል፡፡ አሁን አሁን ግን እየተሻለና ወደ ጥሩ አቅጣጫ እየተገባ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ የጋዜጦቹም ቁጥር በዚያው መጠን ቀንሷል፡፡ የአንባቢውም ቁጥር ቀንሷል ማለት ነው፡፡ ጥራትን በሚመለከት ስናይ ግን ከአራትና ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረው የተሻለ ነገር እያየን ነው፡፡ ወደፊት እየተጠናከረና እየተሻሻለ ይሄዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ሚዲያው ውስጥ ችግር ነበረ ወይ? ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ እናያለን፡፡

የግርጌ ማስታወሻ፡- ከላይ እንደገለጽኩት በዚህ ጽሁፍ የቀረቡት የተመረጡ(excerpts) ናቸው፡፡ በመሆኑም ሙሉ ይዘታቸውን ለማንበብ ከእያንዳንዱ አንፃር ባለው ሊንክ በመሄድ ማግኘት ይቻላል፡፡

Daniel Berhane

more recommended stories